በቆዳችን ላይ ያሉ ጥቃቅን ባክቴሪያዎች ለጤናችን ምን ይጠቅማሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቆዳችን ላይ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ባክቴሪያዎች፣ ቫይረሶች እና ፈንገሶች ይኖራሉ።
ቆዳችንን በማጉያ መነፅር ብንመለከት ከ10 ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን ባክቴሪያዎችን እናገኛለን።
እነዚህ በዐይን የማይታዩ ባክቴሪያዎች ጤናችንን የመጠበቅ ሚና ይጫወታሉ። ስለዚህም ማስወገድ ላይኖርብን ይችላል።
በአንጀታችን ውስጥም በዐይን የማይታዩ ባክቴሪያዎች ይገኛሉ። ባክቴሪያ፣ ቫይረስ፣ ፈንገሶች እና ሌሎችም አነስተኛ ነፍሳት ከስኳር፣ አስም፣ ድባቴ እና ሌሎችም ህመሞችን የመከላከል ድርሻ አላቸው።
ቆዳችን ላይ ያሉት ባክቴሪያዎችም ጠቀሜታቸው የጎላ ነው።
ለምሳሌ አንዳንድ ኬሚካል ሰውነታችንን ሲነካን ኬሚካሉን በመሰባበር የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ከፍ ያደርጋሉ።
ከአንጀት ቀጥሎ ባክቴሪያ በብዛት ያለው በቆዳችን ነው።
በዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሁል የምታስተምረው ሆሊ ዊንክሰን “ቆዳ ከሌሎች የሰውነት አካሎች ጋር ሲነጻጸር ደረቅ ከመሆኑ በተጨማሪ በሚሊዮኖች ዓመታት በዝግመተ ለውጥ ላለፉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ባክቴሪያዎች የተጋለጠ ነው” ትላለች።
ይህ ዝግመተ ለውጥ ጠቃሚ እንደሆነ ታስረዳለች።
ባክቴሪያ ከቆዳ ክፍሎች የሚኖርበትን ይመርጣል።
ግንባር፣ አፍንጫ፣ ጀርባ ላይ በብዛት ኩቲባክቴርየም የሚባለው የባክቴሪያ ዓይነት ይገኝባቸዋል።
ከብብት ሥር ስታፋሎከስ እና ኮሪባክቴርየም ይኖራሉ። በእግር ጣት መካከል ፕሮፒኒባክቴርየም ይገኛል።
እንደ ክንድ እና እግር ያሉት አካባቢዎች ግን ደረቅ ስለሆኑ ለባክቴሪያ አይመቹም።
ለዘመናት እነዚህ ጥቃቅን ባክቴሪያዎች ከሰው ጋር በጥገኝነት መኖር ለምደዋል። ምግብም ያገኛሉ።
ሰውነትን ለመውረር የሚመጡና ዕድገታቸውን የሚገቱ ኬሚካሎችን እንደሚያስቆሙ መምህርቷ ታስረዳለች።
በሌሎች እንስሳት ላይ በጥገኛነት የሚኖሩ ባክቴሪያዎችም አሉ።
አንጀት ውስጥ እንደሚገኙት ባክቴሪያዎች በቆዳ ላይ ያሉትም የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም በመገንባት ወይም ሰውነትን በማሠልጠን እንደሚረዱ ሳይንቲስቶች ይናገራሉ።
ሰውነትን ከልጅነት ዕድሜ ጀምሮ የትኞቹን ባክቴሪያዎች መከላከል እንዳለበት እና የትኞቹን መቀበል እንዳለበት ያለማምዳሉ።
ይህም ለአለርጂ የመጋለጥ ዕድልን ይቀንሳል።
ሰውነት ውስጥ ያለውን ፈሳሽ ጠብቆ በማቆየት የቆዳ ማርጀትን የመከላከል ሚናም ይጫወታሉ።
እነዚህ ጥቃቅን ቆዳ ላይ የሚኖሩ ባክቴሪያዎች ቆዳ ለስላሳ ሆኖ እንዲቀጥል ያስችሉታል።
መርዛማ ኬሚካሎች ከቆዳ ሰርገው እንዳይገቡ እና ውሃ እንዳይወጣ ይከላከላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቆዳ ላይኛው ክፍል ስትራተም ኮርነም ይባላል። ኮርኒሳይትስ ከተባሙ የሞቱ ሕዋሳት ነው የሚሠራው።
በማንቸስተር ዩኒቨርስቲ የቆዳ ምርምር ባለሙያ ፕሮፌሰር ካትሪን ኦኒል “በጣም ጠንካራ እና ውሃ የማይገባው የቆዳ ክፍል ነው። ዝናብ ሲመታን ቆዳችን የማይሟሟው በዚህ የቆዳ ክፍል ምክንያት ነው” ትላለች።
ቀጥለው የሚገኙት ተደራራቢ የቆዳ ክፍሎች ካራቲንሳይትስ ይባላሉ። በቆዳ ሕዋሳት መካከል ያሉ አነስተኛ ክፍተቶች ውሃን ያስተላልፋሉ።
“ይህ ክፍል ሁሉም ነገር አንድ ላይ ይዞ የሚያኖር ነው” ስትል ፕሮፌሰር ካትሪን ትገልጸዋለች።
በውሃ የማይሟሟ ሊፒድ የተባለ ሕዋስ እንዲመረት አነስተኛ የቆዳ ባክቴሪያዎች ለቆዳ መልዕክት ያስተላልፋሉ። እራሳቸውም ሊፒድን ያመርታሉ።
ኩቲባክቴርየም የተባለው የባክቴሪያ ዓይነት የላቀ የሊፒድ መጠን ያለውን ሴቡም ንጥረ ነገር እንዲመረት ያደርጋል።
ይህም ቆዳ ውሃ እንዲይዝ እና እንዳይደርቅ ያስችላል። ቆዳ ጤናማ ሆኖ የሚቀጥልበት መንገድ ነው።
ቆዳ ላይ ያለው የጥቃቅን ባክቴሪያዎች መጠን ያልተመጣጠነ ሲሆን ግን ለጉዳት ያጋልጣል። አቶፒክ ደርምታይተስ የተባለውን የቆዳ ህመም ጨምሮ የቆዳ መለብለብ፣ ማበጥ፣ ማቃጠል፣ መላላጥ፣ መድረቅ፣ መሰነጣጠቅ እና ሌሎችም ምልክቶች ያሏቸው የቆዳ በሽታዎች ይገጥማሉ።
በቀጥታ ህመሙን የሚያስከትለው የቆዳ ባክቴሪያ ነው ማለት አይቻልም። ህመሞቹ የቆዳ ባክቴሪያ ባሕሪን ቀይረው ስለመሆኑም ግልጽ አይደለም።
በቀጥታ ከባክቴሪያዎቹ ጋር ሊተሳሰር የሚችለው የቆዳ ማርጀት ነው።
ዕድሜ ሲጨምር ቆዳ ላይ የሚኖሩ ባክቴሪያዎች ዓይነት ይለወጣል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቆዳ ላይ የሚኖሩና ጠቃሚ ባክቴሪያዎች መጠን እየቀነሰ በጎጂ ባክቴሪያዎች ይተካል። ጠቃሚ ባክቴሪያዎች ኢንፌክሽንን የሚከላከሉ እና ቆዳ እንዳይደርቅ የሚረዱ ናቸው።
ሆሊ እንደምትለው የሊፒድ ምርትን የሚያበረታቱ የባክቴሪያ ዓይነቶች ሲቀንሱ፣ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ቆዳቸው እየደረቀ ይሄዳል።
“ይህም ለቆዳ ኢንፌክሽን የመጋለጥ ዕድልን ይጨምራል። ዕድሜ ሲጨምር ቆዳ ላይ በቶሎ ጉዳት የሚከሰተውም ለዚህ ነው” ስትል ታስረዳለች።
መጥፎ የባክቴሪያ ዓይነቶች ህመም ቶሎ እንዳይድንም ያደርጋሉ።
የቆዳ ህመም አጥኚ ኤልዛቤት ግሪስ በሠራችው ጥናት መሠረት፣ የቆዳ ባክቴሪያ ጎጂ ሲሆን ከህመም የማገገሚያ ጊዜ ይረዝማል።
ቆዳ ላይ ያለ የባክቴሪያ ዓይነትን በማየት ከህመም የማገገም ፍጥነትን ለመለካት ምርምር ተደርጓል።
የማይድኑ የቆዳ ህመሞች ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ከሆነ 20 የስኳር ህሙማን አራቱን ይይዛሉ።
“ለማይድን ህመም የሚጋለጡት ሰዎች የትኞቹ እንደሆኑ በቅርብ ዓመታት ውስጥ እንደርስበታለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ቀድመን ካወቅን ቀድመን ሕክምና መስጠት እንችላለን። ኢንፌክሽኑ ያለበትን ቦታ ማስወገድ ወይም እግርን መቁረጥ ሊሆን ይችላል” በማለት ባለሙያዋ ታስረዳለች።
አንዳንድ የሳፊሎኮከስ አውረስ ዝርያዎች በሽታ በቶሎ እንዳይድን በማድረግ ይታወቃሉ።
“የሚያመነጩት ኢንዛይም በአካባቢያቸው ያለውን ሕዋስ ጥሰው እንዲሄዱ የሚያደርግ ነው። ሰውነት በሽታን የሚከላከልበትን አቅም ያሳጣሉ። የሰዎች የሰውነት ሥርዓት መልሶ እንዲጎዳቸው ማድረግ ይችላሉ” በማለት ባለሙያዋ ትገልጻለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለሙያዋ እንደምትለው፣ ባክቴሪያው ህመም በቶሎ እንዳያገግም ያደርጋል።
“በጣም ጽኑ ህመም ሲሆን፣ በሽታው በፍጥነት እንዳይድን ያደርጋል” ትላለች።
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ አንዳንድ ጥናቶች የቆዳ ጥቃቅን ባክቴሪያዎች ከበሽታ በፍጥነት ለመዳን እንደሚያግዙ ይጠቁማሉ።
ዘረ መል ላይ ጉዳት ከሚያደርስ ጨረር (አልትራቫዮሌት ሬድየሽን) እነዚህ የቆዳ ጥቃቅን ባክቴሪያዎች እንደሚከላሉ ጥናቶች ያሳያሉ።
ቆዳ በተፈጥሮው ከጨረር ራሱን መከላከል ይችላል።
ፕሮፌሰር ካትሪን እንደምትለው፣ ባክቴሪያዎቹ መባዛት ሲያቆሙ የሰውነት ዘረ መል ራሱን በራሱ ያክማል።
“ማዳን የማይችሉ ከሆነ ሕዋሳቱ ራሳቸውን ይገድላሉ” ስትል ታክላለች።
ገና ለኅትመት ያልበቃ የፕሮፌሰር ካትሪን ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ ደግሞ፣ የቆዳ ጥቃቅን ባክቴሪያዎች ባይኖሩም የተጎዳ የዘረ መል ክፍል ቢኖርም የሰውነት ቆዳ ሕዋሳት በመባዛት ይቀጥላሉ።
“ከዕጢ መከላከል የሚቻልበት ዋነኛ እና ጠቃሚ መንገድ ነው። የቆዳ ጥቃቅን ባክቴሪያዎች በዚህ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ” ትላለች።
በአይጦች ላይ የተሠራ ምርምር እንደሚጠቁመው፣ ባክቴሪያዎች የጨረር ተጋላጭነትን ለመከላከል ይረዳሉ።
የሰውነት ቆዳ ሲጎዳም በሽታ የመከላከል አቅምን ያዳብራሉ።
ቆዳ ለጨረር ሲጋለጥ የሚፈጠረውን መለብለብ በማከም ሰውነት ኢንፌክሽንን እንዲከላከል የማስቻል አቅም አላቸው።
ቆዳ ላይ የሚፈጠር ጉዳት የሰውነትን ምግብ የማብላላት ሂደት ሊለውጥ እንደሚችል በቅርብ የተሠሩ ጥናቶች ይጠቁማሉ።
የኤስ-ባዮሜትሪክ የሳይንስ ኃላፊ በርናንድ ፓዞልድ እንደሚለው፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ቆዳ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።
“ቆዳችን ላይ ችግር ሲኖር ተቅማጥ ሊይዘን ይችላል። ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ቆዳ ላይ ጉዳት ያመጣል። እርስ በእርስ ተመጋጋቢ ናቸው” ይላል።
ቆዳ ላይ የሚከሰት ህመምን ለማከም ጥቃቅን የቆዳ ባክቴሪያዎችን የሚጠቀም ተቋም ውስጥ ነው በርናንድ የሚሠራው።
የሰውነት ቆዳ ባክቴሪያዎች ከአንጎል አሠራር ጋር ያላቸውን ትስስር ለማወቅ ጥናት እየተደረገ ነው።
በቅርቡ 20 ሰዎች አእምሯቸውን የሚፈትን የቤት ሥራ ተሰጥቷቸው ከቆዳ ባክቴሪያ ጋር ያለውን ትስስር ለመረዳት ጥረት ተደርጓል።
ግንባር ላይ ያለ ባክቴሪያ መጠንን መቀነስ የአእምሮን ትኩረት እንደሚጨምር በጥናቱ ታይቷል።
ስለዚህም ነው ጠቃሚ የቆዳ ባክቴሪያ እና ጎጂ የቆዳ ባክቴሪያን መለየት የሚያስፈልገው።
ጎጂ የቆዳ ባክቴሪያን ለማስወገድ ጥረት ሲደረግ ጠቃሚ የቆዳ ባክቴሪያም አብሮ ሊወገድ የሚችልበት ዕድል አለ።
በአካባቢያችን ያሉ ነገሮች የቆዳችን የባክቴሪያ ዓይነት ላይ ተጽዕኖም ያሳድራሉ። የቆዳ መዋቢያዎችም እንዲሁ።
ቆዳን በጤናማ ባክቴሪያ በማከም ከጎጂ ባክቴሪያ መላቀቅ እንደሚቻል መላ ምቶች ቢኖሩም እርግጠኛ ውጤት የያዙ የሳይንስ ኅትመቶች ውስን ናቸው።
መምርቷ ሆሊ እንደምትለው፣ ጎጂ ባክቴሪያን አስወግዶ ተፈጥሯዊ ጥቅም ያላቸው ባክቴሪያዎችን ለማብዛት መሞከር ከጉዳት ለማገገም የሚወስደውን ሂደት ሊያፋጥን ይችላል።
“ይህ በጣም አስደሳች ነው። ለኢንፌክሽን ሕክምና የሚደረግበትን መንገድ የሚለውጥ እንደሚሆን ተስፋ አለን” ትላለች።












