ከውድ ሽቶዎች ምርት ጀርባ በግብፅ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ መኖሩን የቢቢሲ ምርመራ አጋለጠ

የ10 ዓመቷ ባስማላ
የምስሉ መግለጫ, የ10 ዓመቷ ባስማላ

ለሁለት የውብት መጠበቂያ ኩባንያዎች የሚደርሱ ግብአቶች ማሰባሰብ ላይ ህጻናት እንደሚሳተፉ የቢቢሲ ምርመራ አጋለጠ።

እንደ ምርምራው ውጤት ከሆነ ላንኮም እና ኤሪን የተሰኙት ኩባንያዎች የሚጠቀሟቸው የጃስሚን አበቦች የሚሰበሰቡት በህጻናት ነው።

ሁሉም የቅንጦት ሽቶ አምራቾች ለህጻናት ጉልበት ብዝበዛ ፈጽሞ እንደማይታገሱ እና እንደማይተባበሩ ይገልጻሉ።

የላንኮሜ ባለቤት የሆነው ሎሪያል ሰብአዊ መብቶችን ለማክበር ቁርጠኛ ነኝ ብሏል። የኤሪን ባለቤት ሆነው ኤስቲ ላውደር በበኩሉ አቅራቢዎቹን እንደሚያነጋግር ቃል ገብቷል።

ኩባንያዎቹ የሚጠቀሙትን የጃስሚን አበቦችን የሚያገኙት ከግብፅ ነው።

በርካታ ኩባንያዎች ገንዘብ እጥረት ስላለባቸው ክፍያቸውን ዝቅ ማድረጋቸውን ውስጥ አዋቂዎች እየገለጹ ነው። ይህ ደግሞ በግብፅ የሚገኙ የጃስሚን አቅራቢዎች ህጻናትን እንዲጠቀሙ እያስገደዳቸው ነው።

የሽቶ አምራቾች የአቅርቦት ሰንሰለቶችን ለመፈተሽ የሚጠቀምባቸው የኦዲት ሥርዓቶች በስህተት የተሞሉ መሆናቸውም ተደርሶበታል።

የተባበሩት መንግሥታት የዘመናዊ ባርነት ልዩ ኃላፊ ቶሞያ ኦቦካታ ባለፈው ዓመት በድብቅ በግብፅ የጃስሚን ማሳዎች የተደረገውን ቀረጻን ጨምሮ ቢቢሲ ባቀረባቸው ማስረጃዎች መረበሻቸውን አስታውቀዋል።

“[ኢንዱስትሪው] በወረቀት ላይ እንደ የአቅርቦት ሰንሰለት ግልጽነት እና የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን መዋጋትን በመሳሰሉ ጉዳዮች ዙሪያ መልካም ነገሮችን ያስቀምጣሉ። በቀረጻው እንደሚታየው ግን የገቡትን ቃል እየፈጸሙ አለመሆኑን ነው።"

በግብፅ ጋሪቢያ አውራጃ የምትኖረው ሄባ ፀሐይ አበባዎቹን ከመጉዳቱ በፊት ለቀማውን ለማናወን ቤተሰቦቿን ሌሊት 9፡00 ሰዓት ትቀሰቅሳቸዋለች።

ሂባ እና ቤተሰቦቿ በሊሊት ለለቀማ ይወጣሉ
የምስሉ መግለጫ, ሂባ እና ቤተሰቦቿ በሌሊት ለለቀማ ይወጣሉ

ሄባ አራት ልጆቿ [ዕድሜያቸው ከ 5 እስከ 15] ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት ትናግራለች። በግብፅ ውስጥ እንዳሉት አብዛኞቹ የጃስሚን ለቃሚዎች እሷም “በግሏ የምትሠራ” በትንሽ ይዞታ እርሻ ላይ የተሠማራች ናት። ብዙ በሰበሰቡ ቁጥር የበለጠ ገቢ ያገኛሉ።

ቢቢሲ ባናገራት ዕለት እሷና ልጆቿ 1.5 ኪሎ ግራም ጃስሚን ሰብስበዋል። ከገቢዋ አንድ ሦስተኛውን ለመሬቱ ባለቤት ከከፈለች በኋላ፣ 1.5 የአሜሪካ ዶላር ይቀራታል። ይህ ገቢ ከመቼውም ጊዜ ያነሰ ነው፣ በግብፅ ካለው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት አንጻር ገቢው አነስተኛ ነው። ብዙዎቹ የአበባ ለቃሚዎችም ከድህነት ወለል በታች ይኖራሉ።

የ10 ዓመት ሴት ልጇ ባስማላ ከፍተኛ የዐይን አለርጂ እንዳለባት በሕክምና ተረጋግጧል። በሽታውን ሳትታከም ጃስሚን መልቀሟን ከቀጠለች የዐይን ብርሃኗ እንደሚጎዳ ተነግሯታል።

የጃስሚን አበባው ተለቅሞ ከተመዘነ በኋላ በመሰብሰቢያ ጣቢያዎች በኩል ወደ ዘይት መጭመቂያዎች ይተላለፋል። ፋርኪ እና አጋሮቹ፣ ሃስም ብራዘርስ እና ማካሊኮ የሚባሉ ትልልቅ መጨመቂያዎች አሉ። እንደሄባ ያሉ ሰዎች የሚያገኙትን ዋጋ የሚወስኑት እነዚህ ፋብሪካዎች ናቸው።

ግብፅ ውስጥ በጃስሚን ኢንደስትሪ ውስጥ ከሚሳተፉት 30 ሺህ ሰዎች ውስጥ ምን ያህሉ ህጻናት እንደሆኑ በትክክል መናገር ከባድ ነው። ቢቢሲ ባደረገው ቀረጻ እና ከአካባቢው ነዋሪዎች ባገኘው መረጃ መሠረት የገቢው መቀነስ ብዙዎች ልጆቻቸውን ወደ ጃስሚን ለቀማ እንዲያስገቡ ገፍቷቸዋል።

ቢቢሲ በሥራ ላይ ያገኛቸው ህጻናት
የምስሉ መግለጫ, ቢቢሲ በሥራ ላይ ያገኛቸው ህጻናት

በአራት የተለያዩ ቦታዎች ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት በለቀማ ሥራ ላይ ተሠማርተዋል።

በርካታ ምንጮችም ደግሞ የማቻሊኮ እርሻዎች ላይ ተቀጥረው የሚሠሩ ህጻናት መኖራቸውን ገልጸዋል። ቢቢሲ በድብቅ ባደረገው ቀረጻ ዕድሜያቸው ከ12 እስከ 14 ዓመት የሆኑ ህጻናትን አግኝቷል።

በግብፅ ሕግ መሠረት ከ15 ዓመት በታች የሆነ ማንኛውም ሰው በግብፅ ከምሽቱ 1፡00 ሰዓት እስከ ጠዋት 1፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ መሥራት አይፈቀድለትም።

ፋብሪካዎቹ የጃስሚኑን ዘይት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሽቶ ሚያመርቱ ኩባንያዎች ይላካሉ። ከትላልቆቹ አንዱ መቀመጫውን ስዊትዘርላንድ ያደረገው ጊቫውዳን አንዱ ሲሆን፣ ከኤ ፋክሪ እና አጋሮቹ ጋር ለዓመታት የዘለቀ ግንኙነትም አለው።

ህጻናት በለቀማ ላይ
የምስሉ መግለጫ, ህጻናት በለቀማ ላይ

እንደሎሬል እና ኤስቲ ላውደርን የመሳሰሉ ከእነሱ በላይ ያሉ የሽቶ ኩባንያዎች ናቸው ሥልጣኑ ያላቸው ሲሉ ገለልተኛው የሽቶ ባለሙያ ክሪስቶፍ ላውዳሚየል እና ሌሎች በርካታ የኢንዱስትሪው የውስጥ አዋቂዎች ይገልጻሉ።

“ጌቶቹ” በመባል የሚታወቁት ኩባንያዎች አነስተኛ በጀት ያዘጋጁላቸዋል ብለዋል።

“የጌቶቹ ፍላጎት በጣም ርካሽ ዘይት በመግዛት ሽቶ በማምረት” በተቻለ መጠን በከፍተኛ ዋጋ መሸጥ ነው ብለዋል ስለኩባንያዎቹ በቅርበት የሚያውቁት ላውዳሚየል።

“በእርግጥ ደሞዝን ወይም የለቃሚዎችን ክፍያን ወይም የጃስሚኑን ትክክለኛ ዋጋ አይቆጣጠሩም” ብለዋል።

ነገር ግን በሚያወጡት አነስተኛ በጀት ምክንያት የደመወዝ ጫናው ፋብሪካዎች እና ጃስሚን ለቃሚዎች ላይ ያርፋል ብለዋል።

“በገበያ ላይ በሚነገረው ውድነት እና ለለቃሚዎቹ በሚሰጠው ክፍያ መካከል ትልቅ ልዩነት አለ” ሲሉ አክለዋል።

ክሪስቶፍ በሥራ ላይ
የምስሉ መግለጫ, ክሪስቶፍ በሥራ ላይ

ኩባንያዎቹ በተለያየ መንገድም ሥነ ምግባሩን ጠብቀው እንደሚሠሩ ይገልጻሉ። በአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ያለ ማንኛውም ቀጣሪ ደኅንነቱ የተጠበቀ የሥራ ሁኔታ ለመፍጠር እና የህጻናት ጉልበት ብዝበዛን ለማስወገድ ቃል በመግባት የተባበሩት መንግሥታትን ሕግ ፈርሟል።

የጊቫውዳን ከፍተኛ ሥራ አስፈፃሚ እንደሚሉት ከሆነ ዋነኛው ችግር የሽቶ ኩባንያዎቹ የአቅርቦት ሰንሰለታቸውን መቆጣጠር አለመቻላቸው ነው።

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት ሥራ አስፈፃሚው እንዳሉት እነዚህ ኩባንያዎች ቁጥጥር የሚያደርጉት የሦስተኛ ወገን ኩባንያዎችን በመቅጠር ነው።

ኩባንያዎቹ ኦዲት እንደሚያደርጉላቸው የሚገልጻቸው ድርጅቶች ሴዴክስ እና ዩኢቢቲ የተሰኙትን ነው። የኦዲት ሪፖርታቸውም በይፋ ባይገኝም፤ የጃስሚን ገዥ በመምሰል ኤ ፋክሪ እና አጋሮቹ ሁለቱንም ለቢቢሲ እንዲልኩ ተደረገ።

ባለፈው ዓመት ፋብሪካውን በመጎብኘት ላይ የተመሠረተው የዩኢቢቲ ዘገባ የሰብአዊ መብት ጥሰት መኖሩን ቢያሳይም በዝርዝር አልገለጸውም። ኩባንያው ግን “ማረጋገጫ” ተሰጥቶታል። ይህ ማለት ደግሞ “ኃላፊነት በተሞላው መንገድ የተገኘ የጃስሚን ዘይት” አቅርቧል ማለት ነው።

ሴዴክስ ለፋብሪካው አመርቂ ግምገማ ቢሰጥም ጉብኝቱ አስቀድሞ መነገሩ እና የፋብሪካውን ቦታ ብቻ መገምገሙ ታውቋል። ጃስሚን የሚገኝባቸው አነስተኛ ማሳዎች ግን አልተካተቱም።

ባስማላ ለህክምና ቀጠሮዋ ስትሄድ
የምስሉ መግለጫ, ባስማላ ለህክምና ቀጠሮዋ ስትሄድ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ከየትኛውም ዓይነት የሠራተኛ መብት ረገጣዎች ጋር አልቆምም። ነገር ግን ሁሉንም የአካባቢ እና የሰብአዊ መብት ስጋቶች ወይም ተጽእኖዎችን ለመለየት እና ለማስተካከል አንድ አካል ብቻ በቂ ሊሆን አይችልም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

በዓለምአቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ያሉ ሰብአዊ መብቶችን ለማሻሻል በሚሠራ ኩባንያ ውስጥ የሚካሄዱ ፕሮጀክቶች የሕግ ባለሙያዋ ሳራ ዳዱሽ የቢቢሲ ምርመራ “እነዚህ ሥርዓቶች ውጤታማ እንዳልሆኑ ያሳያል” ብለዋል።

“ኦዲተሮች ኦዲት ለማድረግ የተከፈላቸው ላይ ብቻ ነው እያተኮሩ ያሉት” ይህ ደግሞ ለሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ዋና ምክንያት የሆነውን የሠራተኛው ክፍያን ላያጠቃልል ይችላል።

ኤ ፋክሪ እና አጋሮቹ የህፃናት ጉልበት ብዝበዛ የተከለከለ መሆኑን ቢያሳውቅም አብዛኛው ጃስሚን የሚገኘው ከገለልተኛ ሰብሳቢዎች ነው ብሏል።

ማቻሊኮ በበኩሉ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ለቃሚዎችን እንደማይቀጥር እና ላለፉት ሁለት ዓመታት ለጃስሚን ለቃሚዎች የሚከፍለውን ዋጋ እንደጨመረ አስታውቋል።

ጊቫውዳን በበኩሉ የምርመራውን ውጤት “በጣም አስደንጋጭ” ሲል ገልጾ፤ “የህፃናት ጉልበት ብዝበዛን ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ እርምጃ መወሰድ መቀጠል የሁላችንም ግዴታ ነው” ብሏል።

ፊርሜኒች ጃስሚን የሚያገኘው ከማቻሊኮ እንደነበር እና አሁን አዲስ አቅራቢ እየተጠቀመ መሆኑን ተናግሯል። ይህንን ችግር ለመቅረፍ ከኢንዱስትሪው ባለድርሻዎች ጋር በጋራ ለመፍታት የሚደረጉ ጅምሮችን እንደሚደግፍም አክሏል።

የምርመራውን ውጤት ለሽቶ ጌቶቹም ተሰጥቷል።

ሎሪል “በዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸውን የሰብአዊ መብቶች ለማክበር ቁርጠኛ ነኝ” ብሏል።

“አንድ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር ሎሪል የችግሩ መንስኤ የሆኑትን ነገሮች በመለየት መፍትሄ የሚመጣበት መንገድ ላይ በትኩረት ይሠራል። በጥር ወር በልጆች ጉልበት ብዝበዛ ላይ በማተኮር የሰብአዊ መብት ረገጣዎችን በመለየት ገምግሟል።”

ኤስቲ ላውደር በበኩሉ “የሁሉም ህጻናት መብቶች ሊጠበቅ እንደሚገባ እናምናለን። ይህን በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ለመመርመር አቅራቢዎቻችንን አግኝተናል። በአካባቢው በጃስሚን አቅርቦት ሰንሰለት ዙሪያ ያለውን ውስብስብ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሂደት ስለምንገነዘብ የተሻለ ግልጽነት ለመፍጠር እና የማኅበረሰቦችን ኑሮ ለማሻሻል እርምጃዎችን እየወሰድን ነው” ብሏል።

ወደ ጋርቢያ ተመልሰን ከጃስሚን ሚዘጋጀው ሽቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሸጥበትን ዋጋ ለሄባ ስንነግራት ደነገጠች።

“እዚህ ያሉ ሰዎች ምንም የላቸውም” አለች።

“ሰዎች ሽቶ በመጠቀማቸው አይከፋኝም። ነገር ግን ይህንን ሽቶ የሚጠቀሙ ሰዎች በውስጡ ያለውን የህጻናት ህመም እንዲመለከቱ እና እንዲናገሩ እፈልጋለሁ።”

የሕግ ባለሙያ የሆኑት ሳራ ዳዱሽ ግን ኃላፊነቱ በሸማቹ ላይ አይወድቅም ይላሉ።

“ይህ እኛ ልንፈታው የሚገባን ችግር አይደለም። ሕግ እንፈልጋለን... የድርጅቶችን ተጠያቂነት እንፈልጋለን። ይህ ደግሞ በተጠቃሚዎች ላይ ብቻ ሊሆን አይችልም” ብለዋል።