ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ሠራተኞቹ "ሆነ ተብሎ እና ዒላማ ተደርገው" መገደላቸውን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, MSF
ከአራት ዓመታት በፊት በትግራይ ጦርነት ወቅት በክልሉ የሰብዓዊ ተልዕኮ ላይ የነበሩ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) ሦስት ሠራተኞች "ሆን ተብሎ እና በግልጽ ተለይተው" በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት "ያነጣጠረ ግድያ" እንደተፈጸመባቸው ድርጅቱ አስታወቀ።
የረድዔት ድርጅቱ ሠራተኞቹ በተገደሉበት መንገድ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት 'ኮንቮይ' [ተሽከርካሪዎች] እንደነበር ማረጋገጡን እንዲሁም አንድ የጦሩ አዛዥ "ተኩስ" እና "አስወግዳቸው" የሚል ትዕዛዝ መስጠታቸውን ጠቁሟል።
አንድ የኤም.ኤስ.ኤፍ ከፍተኛ ኃላፊ ራኬል አዮራ "ሆን ተብሎ ነው የተገደሉት፤ ከአጥቂዎቻቸው ጋር ፊት ለፊት እየተያዩ ነበር እና በጣም በቅርብ ርቀት ብዙ ጊዜ በጥይት ተመተዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ድርጅቱ ይህን ያስታወቀው ከአራት ዓመታት በፊት፣ ሰኔ 2013 ዓ.ም. በትግራይ ክልል በሦስት ሠራተኞቹ ላይ "ሆን ተብሎ ያነጣጠረ" ግድያ መፈጸሙን አስመልክቶ በውስጣዊ ምርመራ የደረሰባቸውን ግኝቶች ይፋ ባደረገበት ወቅት ነው።
ሦስቱ የኤምኤስኤፍ ሠራተኞች የተገደሉት የትግራይ ጦርነት እየተካሄደ በነበረበት ወቅት በክልሉ ማዕከላዊ ዞን ነው።
ሦስቱ ሠራተኞች የ35 ዓመቷ ስፔናዊቷ ማሪያ ሄርናንዴዝ ማታስ እንዲሁም ሁለቱ ኢትዮጵያውያን የ31 ዓመቱ ቴዎድሮስ ገብረማርያም እና የ32 ዓመቱ ዮሐንስ ሃለፎም ረዳ ናቸው።
ዮሐንስ እና ቴዎድሮስ ድርጅቱን የተቀላቀሉት ከመገደላቸው ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ሲሆን፣ ማርያ ሄርናንዴዝ ደግሞ ለዓመታት የድርጅቱ የድንገተኛ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ሆኖ ሠርታለች።
የሦስቱ ሠራተኞች አስክሬን ግድያው በተፈጸመ ማግስት ይጓዙበት ከነበረበው ተሽከርካሪ በ400 ሜትሮች ርቀት ላይ የተገኘ ሲሆን፤ ተሽከርካሪያቸው ደግሞ በተደጋጋሚ በጥይት ተመትቶ እንዲሁም ተቃጥሎ ነበር።
ማሪያ እና ዮሐንሰ በተተኮሰባቸው ወቅት በእግራቸው እየተራመዱ እንደነበር የተናገሩት አዮራ "ለጥያቄ ተጠርተው ይሁን ወይም ከወታደሮቹ ጋር እንነገጋር ብለው የምናውቀው ነገር የለም" ብለዋል።
ኤምኤስኤፍ ባካሄደው ምርመራ "ጥቃቱ ሆን ተብሎ እና በግልጽ በሚታወቁ ሦስት የረድኤት ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ ግድያ መሆኑን" እንዲሁም "የኤምኤስኤፍ ሠራተኞች በተገደሉበት በዚሁ መንገድ ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት ኮንቮይ እንደነበረም" ማረጋገጡን ገልጿል።
በጊዜው ጦርነቱ እየተካሄደ በነበረበት የትግራይ ክልል የህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የነበሩት ሶስቱ ሰራተኞች በወቅቱ በነበረው ግጭት ቆሰሉ ህሙማንን ለመርዳት እየተጓዙ እንደነበር ድርጅቱ አስታውቋል።
ሰራተኞች በማዕከላዊ ትግራይ ዓቢ አዲ ከተማ አቅራቢያ ወደሚገኝ መንደር በግልጽ ምልክት በተደረገበት የኤም.ኤስ.ኤፍ መኪና እየተጓዙ እንደነበር አክሏል።
"[ሰራተኞቹ] በጉዟቸው ወቅት የተሽከርካሪያቸው ጉዞ ተቆርጦ ተገድለዋል" ሲል ድርጅቱ የግድያውን አፈጻጸም አስታውቋል።
ኤም.ኤስ.ኤፍ ሰራተኞቹን ግድያ በተመለከተ ከፌደራል መንግስት እና ከህወሓት ጋር ለመነጋገር ጥረት ቢያደርግም "ለአራት ዓመታት በኋላም ሰራተኞቹ ላይ ስለደረሰው ነገር አስተማመኝ መልስ አላገኘም" ብሏል።
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ምርመራ እየተካሄደ እንደሆነ ማረጋገጫ መስጠታቸውን የጠቆመው ድርጅቱ "ከአራት ዓመታት በኋላ ኤም.ኤስ.ኤፍም ሆነ የተጎጂ ቤተሰቦች ምንም አይነት ተዓማኒነት ያለው መልስ አላገኙም" ሲል አክሏል።
የድርጅቱ ፕሬዝዳንት ፓውላ ጊል "የተጠናቀቀውን የምርመራ ውጤቶችን ለማጋራት በቂ የፖለቲካ ፍቃደኝነት እንደሌለ ብቻ መገመት እንችላለን" ማለታቸው በውስጣው የምርመራ ሪፖርቱ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።
ፕሬዝዳንቷ "ምንም ይፋዊ የመንግሥት መግለጫ ከሌለ ለሰራተኞቻችን እና ለሟች ባልደረቦቻችን ቤተሰቦች የደረስንባቸው ግኝቶች ለሕዝብ የማሳወቅ ሥነ ምግባር ግዴታ አለብን ይህ ችላ ሊባል ወይም ተቀብሮ ሊቀር በማይገባው አሰቃቂ ግድያ ላይ የተወሰነ ብርሃን ሊሰጥ የሚችል አስፈላጊ እርምጃ ነው" ሲሉ ውስጣዊ ምርመራውን ገልጸውታል።
ሁሉም የኤም.ኤስ.ኤፍ አርማ ያለበት እና የኤምኤስኤፍ አርማ እና ባንዲራ በሚያሳይ ተሽከርካሪ፤ ነጭ ካባ ለብሰው በመጓዝ ላይ የነበሩት ሶስት ሰራተኞች "አጥቂዎቻቸውን እየተመለከቱ ከቅርብ ርቀት በተደጋጋሚ በጥይት ተደብደበዋል" ሲል ድርጅቱ ገልጿል።
"እነሱ [የኢትዮጵያ ሰራዊት] የሰብዓዊ ረድኤት ሰራተኞችን እንደሚገድሉ ያውቁ ነበር" ሲሉ የኤምኤስኤፍ ስፔን ጄኔራል ዳይሬክተር ራኬል አዮራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኤምኤስኤፍ እንዲህ አይነት ድምዳሜ ላይ ለመድረስ የሳተላይት ምስሎች፣ የዓይን እማኞችን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወታደሮች እንቅስቃሴን አስመልከቶ በይፋ የታወቁ መረጃዎችን መመርኮዙን አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ግድያው በተፈጸመበት "ትክክለኛው ቦታ" ላይ እንደነበሩ የረድኤት ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።
ኃላፊዋ ለቢቢሲ የኢትዮጵያ የፍትህ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ባደረጉት ቅድመ ምርመራ የመከላከያ ወታደሮች ግድያው በተፈጸመበት ቦታ አልነበሩም ሲሉ በቃል በአውሮፓውያኑ 2022 አጋማሽ ለኤምስኤፍ አሳውቀዋል ብለዋል።
ሆኖም ባለስልጣናቱ ይህንን ቃላቸውን በጽሁፍ ለማስፈር ፈቃደኛ አልነበሩም ያሉት አዮራ የረድዔት ሰራተኞቹ ግድያን የፈጸሙ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ በተደጋጋሚ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለመነጋገር መሞከራቸውን ገልጸዋል።
የኤም.ኤስ.ኤፍ ፕሬዝዳንት ፓውላ ጊል "ይህ በተኩስ ልውውጥ የተከሰተ ነገር አይደለም ወይም አሳዛኝ ስህተት አልነበረም። ባልደረቦቻችን የተገደሉት ሆን ተብሎ በተፈጸመ ጥቃት ነው" ሲል ክስተቱን ገልጸውታል።
ድርጅቱ እማኞችን ጠቅሶ በሪፖርቱ እንዳሰፈረው የኢትዮጵያ መከላከያ ጦር በአካባቢው ከመኖሩ ባሻገር "በጥቃቱ ውስጥ የተሳተፉበትን መጠን እና ባህሪ" አብራርቷል።
በዚህም "የኢትዮጵያ የመከላከያ ወታደሮች [በግድያው] ቀጥተኛ ተሳትፎ እንደነበራቸው" ከመከላከያ ጦሩ ኮንቮይ ጋር ሲጓዙ ከነበሩ ምስክሮች መረጃዎችን መቀበሉን ገልጿል።
አንድ ወታደር ለአካባቢው የኢትዮጵያ መከላከያ ጦር አዛዥ ወደ አካባቢው ነጭ [የኤም.ኤስ.ኤፍ] መኪና እየተቃረበ እንደሆነ ተኩሱ ትዕዛዝ እንደሰጠ ሪፖርቱ የዓይን እማኞችን ዋቢ አድርጎ ጠቅሷል።
ከአፍታ በኋላም ወታደሮቹ ለመተኮስ ሞክረው መኪናዋ አቢ አዲ ደርሳ እንደቆመች መናገራቸውን ተከትሎ የጦር አዛዡ "ሂዱና ያዟቸው" እንዲሁም "አስወግዷቸው" የሚል ትዕዛዝ መስጠቱን ሪፖርቱ አመላክቷል።
ድርጅቱ ከግድያው በኋላ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ጋር ከ20 በላይ ስብሰባዎች ማድረጉን ጠቁሟል።
በተለያዩ ጊዜ የውስጥ ምርመራ ግኝቶችን ከደጋፊ ቁሳቁሶች ጋር ለፍትህ ሚኒስትር ማካፈላቸውን የሚያነሱት ፕሬዝዳንቷ ፓውላ፤ "የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ተአማኒነት ያለው ምርመራ አጠናቅቀው ውጤቶቹን ለማጋራት ያለማቋረጥ ቢጠየቁም ሊያቀርቡ አልቻሉም፣ ይህም የማያጠያይቅ እና ተቀባይነት የሌለው ነው'' ብለዋል።
ድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን ከሶስት ዓመታት በፊትም ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ድርጅቱ ጥያቄውን ያቀረበው ግድያውን በተመለከተ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ የምርመራ ዘገባ ካወጣ በኋላ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት ለሪፖርቱ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቆ ነበር።
በጊዜው የኤም.ኤስ.ኤፍ ፕሬዝዳንት ፓውላ ድርጅቱ በራሱ ኣካሄደው ምርመራ በቀጥታ ገዳዮቹ እንደማን እንደሆኑ እና ምክንያታቸው ምን እንደሆነ ማወቅ አልቻለም ብለው ነበር።
ነገር ግን የዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘገባ ሶስት ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ሰራተኞች የተገደሉት በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት መሆኑን ማመላከቱ ይታወሳል።
ጋዜጣው የመከላከያ ሠራዊት አባላት፤ የእርዳታ ሠራተኞች እና ግድያውን የሚመረምሩ ሰዎችን ዋቢ አድርጎ በሰራው ዝርዝር ዘገባ፤ ሦስቱ ሠራተኞች እያፈገፈጉ በነበሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት መገደላቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።
የረድዔት ሰራተኞቹ ግድያ የተከሰተው ጦርነቱ በተፋፋመበት ወቅት እና የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል በተሰማሩ የእርዳታ ሰራተኞች ላይ ያላቸው ጠበኝነት እየጨመረ ባለበት ወቅት ነው ተብሏል።
ማሪያ በክልሉ ከጦርነቱ በፊትም ትሰራ እንደነበር የገለጹት አዮራ "በማህበረሰቡ ዘንድ የተወደደች ነበረች" ብለዋል።
ቴዎድሮስ የተገደለው ባለቤቱ ሴት ልጅ እንደተገላገለች ብዙም ሳይቆይ እንደሆነ የገለጹት አዮራ፤ ልጃቸውንም በሞተችው የኤምኤስኤፍ ሰራተኛ ስም ማሪያ ተሰይማለች።
የትግራይ ኃይሎች በአንድ ወገን እንዲሁም በሌላ ወገን የኢትዮጵያ መከላከያ እና የኤርትራ ኃይል በጋራ ሆነው በተደረገው ደም አፋሳሽ ጦርነት 600 ሺህ ዜጎች ማለቃቸውን የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት እና ግጭቱ እንዲቋጭ ያደራደሩት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ መግለጻቸው ይታወሳል።
ተመራማሪዎች በትግራይ የተከሰተው ሞት በውጊያ፣ ረሃብ እና የጤና አገልግሎት ማጣት እንደሆነ ገልጸዋል።















