የአሜሪካ ሴኔት ለውጭ እርዳታ እና ብሔራዊ ሬድዮዎች ይውል የነበረ 9 ቢሊዮን ዶላር ቅነሳን አጸደቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ሴኔት ለውጭ እርዳታ እና ለብሔራዊ ሬድዮዎች ይውል የነበረውን 9 ቢሊዮን ዶላር እንዲቀነስ የቀረበውን ረቂቅ ህግ አጸደቀ።
ረቂቅ ህጉ የጸደቀው ሐሙስ ምሽት ለረጅም ሰዓት ከወሰደ ክርክር በኋላ 51 ለ48 በሆነ ጠባብ ድምጽ ነው። በሪፐብሊካን የሚመራው ሴኔት ማሻሻያዎችን ለማድረግ ስምምነት ላይ ከደረሰ በኋላም ነው መጽደቅ የቻለው።
ረቂቅ ህጉ ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ያጸደቃቸውን የገንዘብ ድጋፎች እንዲቀነሱ "የሚሻር ፓኬጅ" ተብለው ከተካተቱት ውስጥ አንዱ ነው።
ይህ የፈንድ ቅነሳ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፌደራል ወጪን ለመቀነስ የሚያደርጉት ጥረት አካል ነው።
ከዚህ ቀደም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 9.4 ቢሊዮን ዶላር መቀነስ የሚያስችለውን አሁን በሴኔቱ ማሻሻያ የተደረገበትን ረቂቅ ህግ አጽድቆ ነበር።
አሁን በሴኔቱ ማሻሻያ ተደርጎበት የጸደቀው ይህ ረቂቅ ህግ ተመልሶ ወደዚሁ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመጣ ይሆናል።
"ከመንግሥት ገቢ ጋር በተገናኘ ሁላችንንም ልንስማማበት ወደምንችለው ደረጃ ለመድረስ አስፈላጊው እርምጃ ነው" ሲሉ የሴኔቱ ኃላፊ ጆን ቱኑ ድምጽ ከመሰጠቱ በፊት ተናግረዋል።
ሴናተሮቹ ቀደም ሲል በአሜሪካ የሚደገፈው የኤችአይቪ/ ኤድስ ፕሮግራም፣ ፔፐፋር ወደ 400 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለመቀነስ በምክር ቤቱ በቀረበው ሃሳብ ላይ አልተስማሙም።
በዚህም የተነሳ ሪፐብሊካኖች የተወሰነ ማሻሻያ ካደረጉ በኋላ አብላጫውን ድምጽ ለማግኘት ችለዋል።
ሐሙስ ዕለት የጸደቀው ረቂቅ ህግ በዩኤስኤይድ ያሉ የዓለም አቀፍ ጤና ፕሮግራሞችን ጨምሮ ከበርካታ የውጪ የእርዳታ ፕሮግራሞች 8 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የሚቀንስ ነው።
ረቂቅ ህጉ በተጨማሪ በበርካታ የገጠሪቱ አሜሪካውያን ተደማጭነት ያላቸውን የሬድዮ ስርጭቶችን ጨምሮ ኤንፒአር (ናሺናል ፐብሊክ ሬድዮ) እና ፒቢኤስ (ፐብሊክ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ) የመሳሳሰሉ የሬድዮ ስርጭቶችን በገንዘብ የሚደግፈው የህዝብ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን 1 ቢሊዮን ዶላር ይቀነስበታል።
ከአላስካ የመጡት ሴናተር ሊሳ ሙርኮቭስኪ ከብሔራዊ ሬድዮዎች ገንዘብ ይቆረጣል የሚለውን ባለመቀበል ረቂቅ ህጉን ከዲሞክራቶች ጋር ተቃውመው ከቆሙት ሁለቱ ሪፐብሊካኖች መካከል አንዷ ናቸው።
ሴኔቱ ረቂቅ ህጉን ማጽደቁን ተከትሎ የኤንፒአር ፕሬዚዳንት ካትሪን ማሄር "የገንዘቡ ድጋፍ ቀጣይነት መሰረታዊ ነው" ብለዋል።
ረቡዕ ዕለት የአላስካ ነዋሪዎች የባህር ዳርቻው በርዕደ መሬት መመታቱን ተከትሎ የሱናሚ ማስጠንቀቂያዎችን ለማግኘት የኤንፒአር ፕሮግራሞችን ያካተቱ የሬድዮ ጣቢያዎችን እንዲፈልጉ እንደተነገራቸው ካትሪን ገልጸዋል።
"ይህንን ለህዝብ ሚዲያዎች የሚደረግን የገንዘብ ድጋፍን ማስቀረትን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውድቅ እንዲያደርገው እንጠይቃለን፤ ይህም ማህበረሰባቸውን እንዲሁም የወከላቸውን በቀጥታ የሚጎዳ እና ህይወታቸውን ለአደጋ የሚያጋልጥ ነው" ብለዋል።
ህጉ በቀጣዩ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድምጽ ተሰጥቶበት እንዲጸድቅ የሚመራ ይሆናል።
ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም እንዲቀነስ ያቀረበው ተጨማሪ 400 ሚሊዮን ዶላር በሴኔቱ ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ረቂቅ ህጉ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
ስለ ማሻሻያዎቹ የተጠየቁት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃል አቀባይ ማይክ ጆንሰን "እኛ እንዳደረግነው ያለ ምንም ማሻሻያ እንዲያሳልፉት እንፈልግ ነበር" ብለዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 'የሚሻር ፓኬጅ' የተሰጠው ቀነ ገደብ አርብ ከመጠናቀቁ በፊት ፍጹም አንድ በሆነ ረቂቅ ህግ መስመማት አለባቸው፤ ያለበለዚያ ሪፐብሊካኖች ለመቁረጥ የፈለጉትን ፈንድ ዕድሉን ሳያገኙ ይቀራሉ።















