ትራምፕ በመሬት ፖሊሲዋ ምክንያት ለደቡብ አፍሪካ የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያቋርጡ ዛቱ

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደቡብ አፍሪካ በቅርቡ ያጸደቀችው የመሬት ፖሊሲ በተወሰኑ "ማህበሰረሰቦች" ላይ ያነጣጠረ ነው በሚል ለአገሪቱ የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያቋርጡ ዛቱ።

ደቡብ አፍሪካ ከጨቋኙ የአፓርታድ ስርዓት ከ30 ዓመታት ብትላቀቅም አሁንም አብዛኛው የአገሪቱ የእርሻ መሬቶች አነስተኛ በሆኑት ነጮች እንደተያዘ ነው።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የመሬት ባለቤትነት በአገሪቱ አከራካሪ እና አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኖ የቆየ ሲሆን በቅርብ ጊዜ የጸደቀው የመሬት ፖሊሲ ይህንን ኢፍትሃዊነት ለማስተካከል ያለመ ነው ተብሏል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአንዳንድ ሁኔታዎች ያለ ካሳ መሬት መውረስ የሚያስችል ረቂቅ ህግ እንዲሆን ፈርመዋል።

መንግሥት በመሬት ባለቤትነት ላይ የሚታየው ታሪካዊ ኢፍትሃዊነት እና ዘረኝነት እንዲስተካከል ጥሪዎች እየቀረቡለት ይገኛሉ።

ትራምፕ ድጋፉን አቋርጣለሁ ሲሉ የዛቱት "የመሬት ነጠቃ እየተፈጸመ" ነው የሚሉ ውንጀላ መቅረባቸውን ተከትሎ ነው።

"ደቡብ አፍሪካ በህግ፣ በፍትህ እና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ህገ መንግሥታዊ ዲሞክራያዊት አገር ናት። የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ምንም አይነት ነጠቃ አላካሄደም" ሲሉ ራማፎሳ በኤክስ ገጽ ምላሽ ሰጥተዋል።

ራማፎሳ አገራቸው ያጸደቀችው አዲሱ ህግ "የነጠቃ መሳሪያ ሳይሆን የህገ መንግሥቱ ድጋፍ ያለው ህጋዊ ሂደት ነው። ይህ ሂደት ፍትሃዊ እና ሁሉንም ባማከለ መልኩ የህዝብን የመሬት ተደራሽነት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው" ብለዋል።

ራማፎሳ ደቡብ አፍሪካ ከአሜሪካ የምታገኘው የገንዘብ ድጋፍ የኤድስ የአደጋ ጊዜ ዕቅድ በሆነው ፔፕፋር ውጭ ሌላ እንደሌለ ጠቅሰዋል። ይህም ገንዘብ አገሪቱ ኤችአይቪ/ኤድስን ለመከላከል ከያዘችው 17 በመቶ ነው ብለዋል።

አሜሪካ በአውሮፓውያኑ 2023፣ 440 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለደቡብ አፍሪካ መመደቧን ከአሜሪካ መንግሥት የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በደቡብ አፍሪካ የተወለደው እና በአሁኑ ወቅት የትራምፕ አማካሪ የሆነው ኤሎን መስክ በዚህ ጉዳይ አቋሙን አንጸባርቋል።

"በግልጽ ዘረኛ የሆነ የባለቤትነት ህግ አወጣችሁ?" ሲል ኤለን መስክ በሚቆጣጠረው የኤክስ ገጹ አስፍሯል።

ትራምፕ በበኩላቸው ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማህበራዊ ሚዲያቸው በለጠፉት ጽሁፍ ላይ "የዚህ ሁኔታ ሙሉ ምርመራ ተጠናቆ እስኪያልቅ ድረስ ለደቡብ አፍሪካ የሚሰጠውን የገንዘብ ልገሳ አቋርጣለሁ" ብለዋል።

ትራምፕ ከዚያ በኋላ ለጋዜጠኞች ባደረጉት ገለጻ የደቡብ አፍሪካ መሪዎች "አንዳንድ መጥፎ እና አሰቃቂ ድርጊቶችን እየፈጸሙ ነው" ሲሉ ወንጀለዋቸዋል።

"ይህ አሁን በምርመራ ላይ ነው። ምርመራው ከተጠናቀቀ በኋላ ውሳኔ ላይ እንደርሳለን። መሬት እየነጠቁ ከሆነ ከዚህም የከፋ ነገር እየፈጸሙ ከሆነ እንደርስበታለን" ብለዋል።

የደቡብ አፍሪካ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር ሮናልድ ላሞላ በበኩላቸው የትራምፕ አማካሪዎች ይህን የምርመራ ወቅት "የደቡብ አፍሪካ ፖሊሲዎችን እንዲሁም ህገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሚጠቀሙበት ተስፋ አለኝ" ሲሉ በኤክስ ገጻቸው ምላሽ ሰጥተዋል።