ኤሪክ ቴን ሃግ ከማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝነታቸው ተባረሩ

አሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ደካማ ብቃት ማሳየታቸውን ተከትሎ መባረራቸውን ማንቸስተር ዩናይትድ አስታወቀ።
እሑድ የመጨረሻ ጨዋታቸውን ያደረጉት ቴን ሃገር በዌስት ሃም 2-1 ተሸንፈዋል። ዩናይትድ በደረጃ ሰንጠረዡ 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ ከዘጠኝ ጨዋታዎች ሦስቱን ብቻ ነው ያሸነፈው።
በአውሮፓ ሊግ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ጨዋታዎች አቻ የተለያየው ዩናይትድ በደረጃ ሰንጠረዡ ከ36 ክለቦች 21ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባለፈው ክረምት የኤሪክ ቴን ሃግ ምክትል ሆኖ ወደ ክለቡ የመጣው ሩድ ቫን ኒስትልሮይ ጊዜያዊ አሠልጣኝ ሆኖ እንደሚቀጥል ክለቡ ገልጿል።
ማንቸስተር ዩናይት ባወጣው መግለጫ “ቋሚ አሠልጣኝ እስከሚቀጠር” ቫን ኒስትልሮይ ጊዜያዊ አሠልጣኝ ሆኖ ይቀጥላል ብሏል።
በለንደን ስታድየም በዌስት ሃም የተረቱት አሠልጣኝ ቴን ሃግ ከሥራቸው መባረራቸው የተነገራቸው ሰኞ ማለዳ ነው።
ባለፈው ግንቦት ማንቸስተር ሲቲን በመርታት የኤፌ ኤ ዋንጫ ማንሳታቸውን ተከትሎ ኮንትራታቸው መራዘሙ ይታወሳል። ነገር ግን ከሦስት ወራት በኋላ ከአሠልጣኝነታቸው ተባረዋል።
ዩናይትድ በዚህ የውድድር ዘመን በፕሪሚዬር ሊግ ታሪኩ ለሁለተኛ ጊዜ በጣም ደካማ የሚባል አጀማመር ነው ያደረገው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በአውሮፓውያኑ 2013 ክለቡን ከለቀቁ በኋላ ዩናይትድ ስድስተኛ አሠልጣኝ ለመቅጠር ተነስቷል።
በአውሮፓውያኑ 2022 ክረምት ከኔዘርላንድሱ አያክስ የመጡት የ54 ዓመቱ ቴን ሃግ በመጀመሪያው የውድድር ዘመናቸው ዩናይትድ ሦስተኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ አድርገዋል።
ቴን ሃግ በ2023 በካራባዎ ዋንጫ ፍፃሜ ኒውካስልን በመርታት ለክለቡ በስድስት ዓመታት ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫ አስገኝተው፤ በኤፍ ኤ ፍፃሜ በሲቲ መሸነፋቸው ይታወሳል።
በሁለተኛ ዓመታቸው ደካማ የሚባል አጀማመር የነበራቸው ቴን ሃግ ከአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ በጊዜ ቢሰናበቱም በመጨረሻ ሲቲን በመርታት የኤፍ ኤ ዋንጫ አንስተዋል።
የሰር ጂም ራትክሊፍ ንብረት የሆነው ኢኒዮስ ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ የዩናይትድን 23 በመቶ ድርሻ ገዝቷል። ብሪታኒያዊው ቢሊየነር ራትክሊፍ ባለፈው የካቲት የክለቡ ችግር ከአሠልጣኝ አቅም በላይ ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
በዘንድሮው የውድድር ዓመት ደካማ የሚባል አቋም ያሳዩት ቴን ሃግ በሁሉም ውድድሮች ካለፉት ስምንት ጨዋታዎች አንድ ብቻ ነው ማሸነፍ የቻሉት።
የቴን ሃግን መባረር ተከትሎ የዩናይትድ ተጫዋቾች ለአሠልጣኙ ያላቸውን ክብር በማኅበራዊ ሚድያ ገፆቻቸው ገልፀዋል።
የዩናይትዱ አምበል ብሩኖ ፈርናንዴዝ በኢንስታግራም ገፁ “አለቃ፤ ለሁሉም ነገር አመሰግናለሁ። በእኔ ላይ ላሳደርከው እምነት እና ላሳለፍናቸው ጊዜያት ሁሉ ምስጋና ይግባህ። መልካሙን እመኝልሀለው” ብሏል።












