‘ጭምብል ባጠለቁ’ ሰዎች ታፍኖ የተወሰደው ኬንያዊው የማኅበረሰብ አንቂ ተለቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጭምብል በለበሱ ስድስት ግለሰቦች ከመኖሪያ ቤቱ ታፍኖ የተወሰደው ታዋቂው የኬንያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቦኒፌስ ምዋንጊ መለቀቁን ባለቤቱ ለቢቢሲ ተናገረች።
ቦኒፌስ በኃይል ከተወሰደ በኋላ ሁከት በማነሳሳት በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበረ ቢሆንም ክስ ሳይመሰረትበት እንደተፈታ ንጄሪ ምዋንጊ ገልጻለች።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ጠበቃ የደንበኛቸውን እስር ስልጣንን ያላአግባብ መጠቀም ነው ሲሉ ተችተዋል።
ቦኒፌስ ለእስር የተዳረገው እሑድ በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በተካሄደው የማራቶን ውድድር ላይ ፀረ-መንግሥት ተቃውሞ እንዲደረግ ጥሪ ካቀረበ በኋላ ነው።
የፖሊስ ቃል አቀባይ ሬሲላ ኦኒያንጎ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ምዋንጊ በቁጥጥር ስር መዋሉን አረጋግጠው ተጨማሪ ዝርዝር መረጃዎችን ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ መታሰር ያስቆጣቸው ደጋፊዎቹ ከእስር እንዲፈታ ሲጠይቁ ነበር።
ምዋንጊ ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ሥልጣን እንዲለቁ ሕዝቡን በኤክስ (በቀድሞው ትዊተር) እያነሳሳ #RutoMustGo እና #OccupyStanChart የሚሉ ሃሽታጎችን በመጠቀም ይታወቃል።
እሁድ ዕለት በናይሮቢ የተካሄደው ሩጫ ስታንዳርድ ቻርተርድ ማራቶን ተብሎ ይጠራል።
ተሳታፊዎች የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ ያሏቸውን ቀለማት እንዲለብሱ፣ ‘ሩቶ ሥልጣን ይልቀቁ’ የሚል መልዕክት ያለው ጽሑፍ እና የተቃውሞ ዝማሬዎችን በበይነ መረብ እንዲያጋሩ ጥሪ ሲያርብ ነበር።
የሩጫው ተሳታፊዎችን ‘ተረጋጉ፣ ሰላማዊ ሁኑ እና ተዝናና!’ በማለት አክሏል።
ቦኒፌስ በመንግሥት ላይ በሚያካሂደው የተቃውሞ ቅስቀሳ ምክንያት በተደጋጋሚ በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ ታስሯል።
አሁን ያቀረበው የተቃውሞ ጥሪ እየተባባሰ በመጣው የኑሮ ውድነት እና በፖሊስ ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ምክንያት ከወራት በፊት ሕዝባዊ ቁጣ በተነሳባቸው ፕሬዝዳንት ሩቶ ላይ ጫና ለመፍጠር እንደሞከረ ታይቷል።
ባለቤቱ ንጄሪ ምዋንጊ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ከሆነ እሑድ ንጋት ላይ ከናይሮቢ በስተምሥራቅ አቅጣጫ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ማቻኮስ አውራጃ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር ውሏል።
አምስት ጭንብል ያጠለቁ ወንዶች እና አንዲት ጭንብል ያጠለቀች ሴት (ሁሉም ምንም ዓይነት የመለዮ ልብስ አልለበሱም) ባሏን ከደበደቡት በኋላ ወስደውታል።
“ቢያንስ ልብሱን እንዲለብስ ከፈቀዱለት በኋላ ወስደውታል” ስትል ንጄሪ ምዋንጊ ለቢቢሲ ተናግራለች።
ቦኒፌስ በናይሮቢ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ መታሰሩን ከሰዓታት በኋላ ፖሊስ አረጋግጧል።
የቦኒፌስ ጠበቆች እና ባለቤቱ ሁከትን በማነሳሳት ክስ እንደተመሠረተበት ተናግረው እሱ ግን አለመቀበሉን ጨምረው ገልጸው ነበር።
ሩቶ እአአ በ2022 ፕሬዝዳንት ሆነው ሲመረጡ “ሀስለር ኔሽን” ሲሉ በሰየሙት ዕቅድ ድሆችን እንዲሁም ሥራ አጦችን በተለይም ወጣቶችን ለማገዝ ቃል ገብተው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ ሰፋ ባሉ ዘርፎች ግብሮችን ለመጨመር ማቀዳቸውን ካወጁ በኋላ በሰኔ እና በሐምሌ ወራት ላይ ሕዝባዊ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር።
ዕቅዶቹን ውድቅ በማድረግ ዋነኛውን የተቃዋሚ ፓርቲ የመንግሥታቸው አካል በማድረግ የሕዝብን ቁጣ ለማብረድ ሞክረዋል።
የኬንያ ፓርላማም ምክትላቸውን ሪጋቲ ጋሻጉዋን ከሳምንታት በፊት ከሥልጣን እንዲነሱ በመወሰን ለሩቶ ድጋፉን አሳይቷል።
ጋሻጉዋ በጎሳ መከፋፈልን በማባባስ እና ኃላፊነትን ባለመወጣት ወንጀል ተከሰዋል።
ክሱን ውድቅ በማድረግ የቀረበባቸውን ክስ በሙሉ “ፖለቲካዊ ደባ” ሲሉ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ሩቶ በበኩላቸው የሁሉንም ኬንያውያን ጥቅም ለማስጠበቅ እና የኢኮኖሚ መሻሻልን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ ነኝ ብለዋል።












