መስከረም አበራ ለቀረበባት ክስ ጄነራል አበባውን እና ዶ/ር ይልቃልን በመከላከያ ምስክርነት ቆጠረች

መስከረም አበራ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በፊት ለቀረበባት ክስ የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ እና የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፋለን በመከላከያ ምስክርነት ቆጠረች።
ዐቃቤ ሕግ በመስከረም አበራ ላይ ክስ የመሠረተው ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በፊት በታኅሣሥ 2015 ዓ.ም. ነበር።
ጉዳይዋን የሚመለከተው ችሎት ከሦስት ወራት በፊት፣ ዐቃቤ ሕግ የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ እና የወንጀል ሕጉን ድንጋጌዎች ጠቅሶ ያቀረበባትን ክስ እንድትከላከል በይኖ ነበር።
ይህን ብይን ተከትሎ መስከረም አበራ የመከላከያ ማስረጃ ዝርዝር መግለጫ ባለፈው ሰኔ ወር ለፍርድ ቤቱ ባቀረበችበት ወቅት፣ ሁለቱን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በመከላከያ ምስክርነት ቆጥራለች።
ችሎቱም በዚሁ ቀን ለጄነራል አበባው እና ለዶ/ር ይልቃል በፌደራል ፖሊስ በኩል መጥሪያ እንዲደርሳቸው አዝዞ ነበር።
ይህን ትዕዛዝ የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ከባድ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት “ሁለቱ ምስክሮች የፖሊስ መጥሪያ ደርሷቸው ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ” ለዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 18/2016 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።
በዛሬው የችሎት ውሎ መጥሪያውን እንዲያደርስ የታዘዘው የፌደራል ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ ምላሽ መስጠቱን የመስከረም ጠበቃ አቶ ሄኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ በሰጠው ምላሽ፤ “ለጄነራል አበባው ታደሰ ለመሥሪያ ቤታቸው መዝገብ ቤት መጥሪያውን ማድረሱን ዶ/ር ይልቃል ከፋለን በተመለከተ አድራሻቸውን ለማግኘት ስለተቸገረ መጥሪያ አላደረስኩም እና መጥሪያ እንዳደርሳቸው አድራሻቸውን ያሳወቁኝ” ማለቱን ጠበቃ ሄኖክ ገልጸዋል።
የፌደራል ፖሊስን ምላሽ ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የተከሳሽን ጠበቆች አስተያየት ጠይቋል።
በዚህም መሠረት የተከሳሽ ጠበቆች፤ “ለጄነራል አበባው ታደሰ በሚመሩት መሥሪያ ቤት መዝገብ ቤት ደርሷል መዝገብ ቤት የገባ ደብዳቤ ደግሞ ኃላፊ ጋር ይደርሳል እና መጥሪያው እንደደረሰ የሚያስቆጥር ነው።
“መጥሪያው እሳቸው ጋር ከደረሰ ደግሞ ቀጠሮውን ያውቃሉ ነገር ግን በቀጠሮው ቀን ስላልቀረቡ ሕጉ አንድ የፍርድ ቤት መጥሪያ የደረሰው ሰው ካልቀረበ ፖሊስ አስገድዶ እንዲያመጣው ሕጉ ያስቀመጠው ሥርዓት ስላለ በዚያ መሠረት በቀጣይ ቀጠሮ እሳቸው በፌደራል ፖሊስ በኩል ተገድው እንዲመጡ እና የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ” ትዕዛዝ እንዲሰጥ ለፍርድ ቤቱ መጠየቃቸውን አቶ ሄኖክ አስረድተዋል።
በሁለተኛ ምስክርነት የተቆጠሩትን ዶ/ር ይልቃል ከፋለን በተመለከተ፤ “እሳቸው አሁንም የብልጽግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ አባል ናቸው፤ ትልቅ የፓርቲ ሹመት ላይ ነው ያሉት። ፖሊስ መጥሪያ ሊያደርሳቸው ይችላልና ፖሊስ በአድራሻቸው መጥሪያውን ያድርስ” የሚል አስተያየት ማቅረባቸውን አቶ ሄኖክ አክለዋል።
ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ፤ “ጄነራል አበባው ታደሰን በተመለከተ መዝገብ ቤት እንጂ ለእሳቸው ስላልደረሰ ተገደው ይቅረቡ የሚለው አስተያየት ተገቢነት ያለው አይደለም” ብሏል።
ዶ/ር ይልቃልን በተመለከተ ደግሞ “አድራሻ ማቅረብ ያለባቸው የተከሳሽ ጠበቆች ናቸው እንጂ፤ የእነሱን [ምስክሮች] አድራሻ ፖሊስ አፈላልጎ መጥሪያ ማደርስ ያለበት ስላልሆነ ይኼም ተገቢነት የሌለው ነው” የሚል አስተያየት ማቅረቡን ጠበቃ ሄኖክ አስረድተዋል።
ይህን የዐቃቤ ሕግ አስተያየት ተከትሎ የተቃውሞ አስተያየት ማቅረባቸውን ጠበቃ ሄኖክ ተናግረዋል።
ዐቃቤ ሕግ ምስክሮች አቀራረብ ላይ የተከሳሽ ጠበቆች አስተያየት አለመስጠታቸውን ያስታወሱት ጠበቃ ሄኖክ፤ “ዐቃቤ ሕግ የተከሳሽ ምስክሮች በምን ዓይነት መልኩ መምጣት እንዳለባቸው አስተያየት ሊሰጥ አይገባም። በእኛ ምስክር አቀራረብ ላይም አስተያየት መስጠቱ ተገቢነት ያለው አይደለም” ሲሉ ተቃውሟቸውን አቅርበዋል።
የምስክሮችን አቀራረብ በተመለከተም “የጄነራል አበባው [መጥሪያ] መዝገብ ቤት ደርሷል ከተባለ በሕጉ መሰረት መዝገብ ቤት የገባ ደብዳቤ ኃላፊዎች ጋር ይሄዳል። ስለዚህ አሠራሩን መሠረት አድርገን ነው እኛ እየተናገርን ያለነው” ማለታቸውን አቶ ሄኖክ ገልጸዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱ ችሎቱ ዳኞች አለመሟላታቸውን በመጥቀስ መጥሪያው በምን አግባብ ይድረስ፣ ምስክሮች እንዴት ይቅረቡ የሚለው ጉዳይ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለሐምሌ 23/2016 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።












