በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት ተቀብረው የሚገኙትን ለማውጣት የቀጠለው እልህ አስጨራሽ ቁፋሮ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ከሰሞኑ በተከሰተው መሬት መንሸራተት አደጋ በናዳ ስር ተቀብረው ያሉ ነዋሪዎችን ለማውጣት እልህ አስጨራሽ ቁፋሮ ቀጥሏል።
ባለፈው ሳምንት እሁድ እና በማግስቱ ሰኞ በተከሰቱ ሁለት የመሬት መንሸራተቶች ምክንያት ህይወታቸው የተቀጠፈ 229 ነዋሪዎችን አስክሬን ከናዳው ስር ማውጣት ተችሏል።
የጎፋ ዞን ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ ነፍስ ለማዳን እንዲሁም አስክሬኖችን ፍለጋ በሚራወጡ ሰዎች ተሞልታለች።
በናዳው ስር ተቀብረው የሚገኙትን ለማውጣት ወንዶች በመቆፈሪያ፣ በአካፋ፣ እንዲሁም በእጃቸው ጭምር የጭቃውን ክምር ያለማሰለስ ያወጣሉ። ከቁፋሮው ጎን ለጎንም የተሰበሰቡት እናቶች እና ህጻናት ከሰሞኑ በአሰቃቂ ሁኔታ የታጡትን እያሰቡ ዋይታቸውን ያሰማሉ።
እናቶች እና ህጻናቶች ጭምር የሰሞኑ የተፈጥሮ ጭካኔ ሰለባ ሆነዋል። በጎፋ ዞን ተራራማ አካባቢ በምትገኘው ቀበሌ እሁድ ሐምሌ 14/ 2016 ዓ.ም ከፍተኛ ዝናብ ጥሎ የመጀመሪያውን የመሬት መንሸራተት ተከሰተ ይህም አራት ሰዎች እንዲቀበሩ አደረገ።
በዚህ የመሬት መንሸራተት ናዳ ስር ተቀብረው የሚገኙ እነዚህን ነዋሪዎች በህይወት ለመታደግ በማግስቱ ሰኞ ረፋድ ላይ የቀበሌው ሊቀመንበር እና የፖሊስ አባላት እና በርካታ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች በቁፋሮ ርብርብ ማድረግ ጀመሩ።
ነዋሪዎቹን ከናዳው ስር በህይወት ለማውጣት የወጣው የአካባቢው ህዝብ ከፍተኛ የነበረ ሲሆን በዚህም ፍለጋ ላይ በነበሩ ሰዎችም ነው ለሁለተኛ ጊዜ መሬቱ ተደርምሶ ድንገተኛ ናዳ የወረደባቸው።
በናዳው ስር በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ተቀብረው ቢገኙም ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሆኑ በትክክል የሚያውቅ የለም።

የቢቢሲ ጋዜጠኞች በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በምትገኘው ጎፋ ዞን ረቡዕ ከረፈደ በደረሱበት ወቅት ከ100 እስከ 200 የሚደርሱ አብዛኞቹ ወጣቶች በቁፋሯቸው እንደቀጠሉ ተመልክተዋል።
ዘመዶቻቸው በናዳ ስር ተቀብረው የሚገኙ ነዋሪዎች ደግሞ በህይወት ይገኛሉ በሚል ተስፋ በጉጉት ተቀምጠው ይጠብቃሉ።
የሚቆፍሩት ወጣቶች ምንም አይነት ዘመናዊ ወይም መሬት የሚቆፍሩ በቴክኖሎጂ የላቁ መሳሪያዎች የላቸውም።
ወደ መንደሯ የሚያቀና መንገድ ባለመኖሩም መሳሪያዎችን ከሌሎች ስፍራዎች ለማምጣት አዳጋች አድርጎታል።
በአንድ ገደላማ ስፍራ ጠባብ እና በአሁኑ ወቅት ደግሞ ጭቃማ የሆነ የእግር መንገድ አለ። በመንገዱ ወደ ላይ ለመውጣትም ሆነ ወደታች ለመራመድ አደገኛ ነው።
በቁፋሮው አስከሬኖች ሲገኙ ቤተሰብ፣ ዘመድ እና ወዳጅ በዚህ የእግረኛ መንገድ ተጉዘው ለቀብር ለመውሰድም ተገድደዋል።
ወጣቶቹ በዚህ አሰቃቂ አደጋ ለታጡ ሰዎች መቃብሮችን እያዘጋጁ ሲሆን ይህች የአርሶ አደር መንደር አሁንም በለቅሶ እና በዋይታ እንደተሞላች ነው።
የአደጋ ስጋት ባለስልጣናት በነፍስ አድን ስራው ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) አገልግሎት ላይ እንደዋሉ መናገራቸው ተዘግቧል። ቢቢሲ ያናገራቸው አንድ ግለሰብም ማክሰኞ እለት እነዚህን ድሮኖች እንዳዩዋቸው ገልጸው ከዚያን በኋላ ግን አላየሁዋቸውም ብለዋል።
ለመንደሪቷ ነዋሪዎች አማራጮቻቸው ያሏቸውን መሳሪያዎች መጠቀም ብቻ ነው። ከናዳው ስር ተቀብረው ያሉትን በህይወት ለማውጣት ተስፋን ሰንቀው በመቆፈሪያ፣ በአካፋ እንዲሁም በእጃቸው ጭምር የጭቃውን ክምር ያነሳሉ።
እንደ እድል ሆኖ የቢቢሲ ጋዜጠኞች በስፍራው በነበሩበት ረቡዕ ዕለት አየሩ መልካም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ፍለጋውን ትንሽ ቀለል ያደርገዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የምትገኘው የጎፋ ዞን ከመዲናዋ አዲስ አበባ በስተደቡብ ምዕራብ 320 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
ስፍራው ተዳፋታማ በመሆኑ አልፎ አልፎ ናዳ ቢከሰትም ይህንን ያህል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ አደጋ ሲከሰት የአሁኑ የመጀመሪያው እንደሆነ የዞኑ ኮምዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ ካሳሁን አባይነህ ከሰሞኑ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት፣ ዩኤንኦቻ መረጃ ከሆነ ደቡብ ኢትዮጵያ ባለፉት ወራት በከባድ ዝናብ እና በጎርፍ ከተጠቁ የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው።
በደቡብ ኢትዮጵያ የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋዎች የሚከሰቱ ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 2016 ከባድ ዝናብ ባሰከተለው የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ቢያንስ 50 ሰዎች ሞተዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ድርቅ እና ጎርፍ ባስከተለው ኤልኒኖ እንዲሁም በጦርነት ምክንያት የተጎዱ ህዝቦችን ለመታደግ 3 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ገልጿል።
ሆኖም እነዚህን ማህበረሰቦች ለመታደግ የሚያስፈልገው ገንዘብ “በሚያሳዝን ሁኔታ” ማሰባሰብ አልተቻለም ብሏል።
“ከባድ ዝናብ እየጣለ ባለበት ወቅትም እንደነዚህ አይነት ድንገተኛ አደጋዎች እንደሚቀጥሉ እንጠብቃለን” ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት የኢትዮጵያ ኃላፊ ፖል ሃንድሌይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በመሬት መንሸራተቱ ምክንያት በተጠቃው በዚህ የጎፋ ዞን አካባቢ የደፋታማው መሬት ሁኔታ ስጋት የፈጠረ ሲሆን በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ 10 ሺህ ሰዎችንም “ከጉዳት ለመታደግ” ስፍራውን እንዲለቁ መደረጉን ኃላፊው አክለዋል።














