በጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 229 በላይ መሆኑ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Gofa Communication
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በተከሰተ የመሬት መንሸራተት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ229 በላይ መሆኑ ቢቢሲ ከጎፋ ዞኑ የተለያዩ ኃላፊዎች ያገኘው መረጃ አመለከተ።
ሰኞ ሐምሌ 15/ 2016 ዓ.ም. በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት የሞቱት ሰዎች አሃዝ ከ229 በላይ መድረሱን እና ከአደጋው ሰለባዎች መካከልም በርካታ ሴቶች እና ሕጻናት ይገኙበታል ተብሏል።
የዞኑ የአደጋ ስጋት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማርቆስ መለሰ እና ገዜ ጎፋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ምስክር ምትኩ እንዳረጋገጡት እስአሁን ድረስ በአደጋው ከ229 ሰዎች በላይ ሕይወት ጠፍቷል።
በመሬት መንሸራተቱ ተቀብረው ሕይወታቸው ካለፈው የወረዳዋ ነዋሪዎች መካከል ወንዶች 148 እና ሴቶች ደግሞ 81 መሆናቸውን አቶ ምስክር ገልጸዋል።
በዞኑ እሁድ ሌሊት የጣለው ከባድ ዝናብ ተከትሎ እሁድ እና ሰኞ ማለዳ ሁለት የመሬት መንሸራተት አደጋዎች እንደተከሰቱ የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ካሳሁን አባይነህ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እሁድ ሌሊት በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በመኖሪያ ቤቶች ላይ የተጫነውን ናዳ ለማንሳት ሰኞ ረፋድ ላይ ርብርብ እየተደረገ በነበረበት ወቅት መሬቱ ተደርምሶ ተጨማሪ ናዳ በማስከተሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ላይ ማረፉን ገልጸዋል።
ሰኞ አራት ሰዓት ገደማ የአካባቢው ቀበሌ ሊቀመንበርን ጨምሮ፣ የፖሊስ አባላት እና በርካታ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች በነፍስ አድን ጥረት ላይ እያሉ ነው ተጨማሪ ድንገተኛ ናዳ ተከስቶ የበርካቶች ሕይወት የተቀጠፈው።
የወረዳዋ አስተዳዳሪ አቶ ምስክር ምትኩ እንዳሉት አስክሬን የማፈላለጉ ሥራ አሁንም የቀጠለ ሲሆን፣ በአደጋው የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ቢቢሲ አቶ ካሳሁንን ሰኞ ምሽት ባናገረበት ወቅት የቀበሌውን ሊቀመንበር ጨምሮ፣ አንድ ፖሊስ እና 30ዎቹ በስም የተለዩ ነዋሪዎች መሞታቸው መታወቁን እና በአጠቃላይም የ55 ሰዎች ሕይወት መቀጠፉን ገልጸው ነበር።
የአካባቢው ባለሥልጣናት የነፍስ አድን እና የአስከሬን ፍለጋቸውን አጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል አቶ ሃብታሙ መናገራቸውን መምሪያው ባወጣው መግለጫ ላይ ሰፍሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አደጋውን በተመለከተ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ “ጥልቅ ሐዘን” እንደተሰማቸው ገልጸው፤ የፌዴራል የአደጋ መከላከል ግብረ ኃይል የአደጋውን ጉዳት ለመቀነስ ወደ አካባቢው መሰማራቱን አስፍረዋል።
ቀደም ሲልም የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት በመሬት መንሸራተት አደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ሐዘናቸውን ገልጸው፤ የጠፉትን በመፈለግ እና የተጎዱትን በመርዳት ኅብረቱ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን እንደሚቆም አሳውቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከባዱ አደጋው የደረሰው ከከባድ ዝናብ በኋላ ባጋጠመ የመሬት መንሸራተት የተቀበሩ ቤቶች ውስጥ የነበሩ ሰዎችን ለማትረፍ የአካባቢው ነዋሪ የነፍስ አድን ጥረት በሚያደርግበት ጊዜ ለሁለተኛ ጊዜ በተፈጠረ መንሸራተት መሆኑ ተገልጿል።
ቢቢሲ የዞኑ ኮምዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ ካሳሁንን ባነጋገረበት ሰኞ ምሽት የቁፋሮ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ እና ሌሊቱን እና በማክሰኞ ቀንም የጠፉ ሰዎችን ከናዳው የማውጣት ሥራ ይቀጥላል ብለው ነበር።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በስፍራው ተሰብስበው እንዲሁም ሌሎች ከናዳው ውስጥ ተቀብረው ያሉ ሰዎችን ለማውጣት ሲቆፍሩ የሚያሳይ ቪዲዮ ወጥቷል።
ነፍስ ከማዳን ርብርብ በተጨማሪ ከዛሬ ጀምሮ ጊዜያዊ ድንኳኖችን (መጠለያዎች) ተዘጋጅተው አስፈላጊው ቁሳቁስ እና እርዳታ እንደሚደረግም አቶ አባይነህ ገልጸዋል።
ስፍራው ተዳፋታማ በመሆኑ አልፎ አልፎ ናዳ ቢከሰትም ይህንን ያህል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ አደጋ ሲከሰት የአሁኑ የመጀመሪያው እንደሆነም አቶ ካሳሁን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት፣ ዩኤንኦቻ መረጃ ከሆነ ደቡብ ኢትዮጵያ ባለፉት ወራት በከባድ ዝናብ እና በጎርፍ ከተጠቁ የአገሪቱ አካባቢዎች መካከል አንዱ ነው።
በደቡብ ኢትዮጵያ የመሬት መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋዎች የሚከሰቱ ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 2016 ከባድ ዝናብ ባሰከተለው የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት ቢያንስ 50 ሰዎች ሞተዋል።












