የወንጀለኞችን የፊት ገጽታ ለመቀየር ፕላስቲክ ሰርጀሪ የሚሠሩት ምሥጢራዊ ሆስፒታሎች

ፕላስቲክ ሰርጀሪ የሚሰሩ ሆስፒታሎች አልጋ

የፎቶው ባለመብት, Presidential Anti-Organised Crime Commission

በፊሊፒንስ የሚገኙ ሆስፒታሎች በሕግ የሚፈለጉ እና በማጭበርበር ድርጊት ተሰማርተው የሚገኙ ወንጀለኞች የፊት ገጽታቸውን የሚቀይር ቀዶ ህክምና (ፕላስቲክ ሰርጀሪ) እያደረጉከሕግ እንዲያመልጡ እየረዱ ነው ተባለ።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት በዚህ ተግባር የተሰማሩ ናቸው ያሏቸው ሁለት ሆስፒታሎች “በመጪዎቹ ሳምንታት” ሊዘጉ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ፖሊስ በቅርቡ በመዲናዋ ማኒላ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ላይ ድንገተኛ ብርበራ አካሂዶ የሰዎችን ገጽታ ለመቀየር በሚደረግ ቀዶ ጥገና ላይ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፀጉር ንቅለ ተከላ እና የጥርስ ማስተካከያ መሳሪዎች እንዲሁም ቆዳ የሚያነጡ ፈሳሾችን ይዟል።

የአገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች ኮሚሽን ቃል አቀባይ ዊንስተን ጆን ካሲዮ በሆስፒታሉ የተያዙትን የቀዶ ህክምና መሳሪዎችን እና ግብዓቶችን በመጠቀም “ጨርሶ የተለየ ሰው መፍጠር ይቻላል” ሲሉ ይናገራሉ።

ከሆስፒታሎቹ ደንበኞች መካከል በፊሊፒንስ በሕገ-ወጥ መንገድ እየኖሩ በበይነ መረብ በኩል (ኦላይን) ቁማር የሚያጫውቱ ድርጅቶች የሚያንቀሳቅሱ ሰዎች ይገኙበታል ተብሏል።

እነዚህ ኦላይን ካሲኖ (ቁማር መጫወቻ ቦታዎች) አብዛኞቹ ደንበኞቻቸው የሚገኙት ቁማር መጫወት ወንጀል በሆነባት ቻይና ነው።

የፊሊፒንስ ፖሊስ ግን እነዚህ ቁማር የሚያጫውቱ ቡድኖች ከቁማር ውጪ በሌሎች ሕገ-ወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተዋል ይላል።

እንደ ፖሊስ ከሆነ ቁማር ከማጫወት በተጨማሪ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲሁም በስልክ በሚደረጉ የማጭበርበር ወንጀሎች ጭምር ይሳተፋሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እነዚህ የወንጀለኞችን የፊት ገጽታ በቀዶ ህክምና በሚቀይሩ ሆስፒታሎች ውስጥ ይሠሩ ነበሩ የተባሉ የቻይና እና ቪዬትናም ዜግነት ያላቸው ሦስት ዶክተሮች፣ ነርስ እና የፋርማሲ ባለሙያ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ፖሊስ የያዛቸው እነዚህን የውጭ አገር ዜጎች የሆኑት የጤና ባለሙያዎች በአገሪቱ የሥራ ፍቃድ የላቸውም ተብሏል።

“ከውጪ ሲታይ የተለመደ ዓይነት የጤና ማዕከል ነው የሚመስለው። ወደ ውስጥ ሲገባ ግን ያላቸውን ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችን መመልከት በጣም ያስገርማል” ብለዋል የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች ኮሚሽን ቃል አቀባዩ።

ካሲዮ እንደሚሉት የህክምና ተቋማቱ የታካሚዎችን ማንነት ጨርሶ ስለማይጠይቁ ወንጀለኛም ይሁን በአገሪቱ የመኖሪያ ፍቃድ የሌለው ሰው የሚፈልገውን አገልግሎት አግኝቶ ይሄዳል።

መሰል ተቋማት መበራከት የጀመሩት በቀድሞ መሪ ሮድሪጎ ዱተርቴ የሥልጣን ዘመን እንደሆነ ይታመናል። ዱተርቴ እአአ 2022 ላይ የሥልጣን ዘመናቸው ከማብቃቱ በፊት አገራቸው ከቻይና ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ሲሠሩ ነበር።

ይሁን እንጂ በዱተርቴ የተተኩት ፈርዲናንድ ማርቆስ መሰል ተቋማት ከወንጀል ጋር ትስስር አላቸው በሚል እርምጃ እየወሰዱባቸው ይገኛል።

“ፕሬዝዳንቱ ፊሊፒንስ በስልክ ሰዎችን የሚያጨበረብሩ ሰዎች መገኛ ተደርጋ እንድትታይ አይፈልጉም። በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎችን ዒላማ የሚያደርጉ አጭበርባሪዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ትዕዛዝ ሰጥተዋል” ይላሉ ካሲዮ።

ኅዳር 2014 ላይ የፊሊፒንስ የኢሚግሬሽን ኃላፊዎች ማንነቱን ለመደበቅ የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ያደረገ ቻይናዊ የማፊያ ቡድን አባልን በቁጥጥር ስር አውለው ነበር።

ካሲዮ መሰል አጋጣሚዎች በአገሪቱ ካሉ ገጽታን የሚቀይሩ ፕላስቲክ ሰርጀሪ ከሚሠሩ ተቋማት ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል ብለዋል።