ኬንያ ውስጥ በፖሊስ ለተገደለው የፓኪስታን ጋዜጠኛ ባለቤት 78 ሺህ ዶላር ካሣ እንዲከፈል ተወሰነ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኬንያ ፍርድ ቤት ከሁለት ዓመት በፊት መንገድ ላይ በፖሊስ በጥይት ለተገደለው ታዋቂው የፓኪስታን ጋዜጠኛ ባለቤት 78 ሺህ ዶላር ካሣ እንዲከፈላት ወሰነ።
አርሻድ ሸሪፍ በፓኪስታን የጦር መሪዎች ላይ እና በፖለቲካው ውስጥ ባለው ሙስና ዙሪያ ጠንካራ ትችት በመስጠት የሚታወቅ ጋዜጠኛ ነበር።
የአምስት ልጆች አባት የሆነው ጋዜጠኛ አገሩን ጥሎ ከመሸሹ በፊት ለፓኪስታን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የግድያ ዛቻ እንደደረሰበት አሳውቆ ነበር።
ሸሪፍ አገሪን ለቅቆ ኬንያ ከደረሰ ከሁለት ወራት በኋላ በኬንያዋ ካጂያዶ ከተማ በፖሊስ መገደሉ ቁጣን ከመቀስቀስ ባለፈ ባለሥልጣናት የሰጡት ምላሽ የዘገየ ነው በሚል የተባበሩት መንግስታት ባለሙያዎች ኬንያን እና ፓኪስታንን እንዲተቹ አድርጓቸዋል።
የኬንያ ፖሊስ በተሳሳተ ማንንት ህይወቱ ማለፉን በመግለጽ ቢከራከርም የሸሪፍ ባለቤት ጃቬሪያ ሲዲቅ በበኩሏ ፓኪስታን ካለ እና ስሙ ባልተገለጸ ሰው ስም በክፍያ የተፈፀመ ግድያ ነው ስትል ተናግራለች።
"ለእኔ እና ለቤተሰቦቼ እረፍት ነው"
ሰኞ ዕለት የካጂያዶ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የኬንያ ባለስልጣናት ህገወጥ እርምጃ ከመውሰድ ባለፈ የሸሪፍን በህይወት የመኖር መብት ጥሰዋል ሲል ውሳኔ አስተላልፏል።
በዚህም ለሳዲቅ ካሣ እና ገንዘቡ ሙሉ በሙሉ እስኪከፈል ድረስ ወለድ እንዲታሰበ ሲል ወስኗል።
ዳኛ ስቴላ ሙቱኩ ብያኔውን ሲያስተላልፉ "የህይወት መጥፋት በገንዘብ ወይም ቤተሰብ የደረሰበት ስቃይ እና መከራ ሊካስ አይችልም። ነገር ግን ካሣ መሰረታዊ መብቶች ሲጣሱ ተገቢው መፍትሄ እንደሚሆን መግባባት አለ" ብለዋል።
የኬንያ ዓቃቤ ህግ እና የገለልተኛው የፖሊስ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን በጉዳዩ ላይ የተሳተፉ ሁለቱ የፖሊስ አባላት ክስ ባለመክፈታቸው የሸሪፍን መብት ጥሰዋል ሲሉ ዳኛዋ ብይን ሰጥተዋል።
ሁለቱም አካላት ምርመራውን አጠናቀው በመኮንኖቹ ላይ እንዲከሰሱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
"ይህ ለቤተሰቡ እና የፖሊስ ተጠያቂነትን እንዲኖር ለሚፈልጉ ኬንያውያን ይህ ድል ነው" ሲሉ የፍርድ ውሳኔውን አስመልክቶ የሳዲቅ ተወካይ የሆኑት ጠበቃ ኦቺኤል ዱድሊ ተናግረዋል።
ሲዲቅ ለኬንያ የፍትህ አካላት አድናቆቷን ገልጻ ብዙ ሥራ እንደሚቀር ተናግራለች።
"ይህ ውሳኔ ለእኔ እና ለቤተሰቦቼ እፎይታ ሰጥቶናል። ነገር ግን ለባለቤቴ ከፍተኛ ፍትሕ ከማግኘት ወደ ኋላ አልልም" ስትል አክላለች።
ቢቢሲ በውሳኔው ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጡት የኬንያ ባለስልጣናትን ምላሽ ጠይቋል።
ፖሊስ በሻሪፍ አሟሟት ዙሪያ የሚጋጩ ዘገባዎችን ሰጥቷል።
አንደኛው የ49 ዓመቱ ጋዜጠኛ በቶዮታ ላንድ ክሩዘር መኪና እየተጓዘ እንደነበር ገልጿል።
ፖሊስ እርምጃ የወሰደው ተመሳሳይ ተሽከርካሪ ተሰርቋል በመባሉ ነው ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፖሊስ ሌላኛው ሪፖርት ደግሞ ከመኪናው ተሳፋሪዎች አንዱ ተኩስ እንደከፈተ እና አባላቱ ምላሽ መስጠታቸውን ገልጿል።
የሟቹ ባለቤቷ ጋዜጠኛዋ ሲዲቅ ባለፈው ጥቅምት ወር ነበር ከኬንያ ጋዜጠኞች ህብረት እና የኬንያ ዘጋቢዎች ማህበር ጋር ክስ የመሠረተችው።
እሷ እና አጋሮቿ ሻሪፍን “ዒላማ ተደርጓል” ብለው ለጠሩት ግድያ ግልጽነት፣ ይቅርታ እና ከኬንያ ባለስልጣናት ተጠያቂነትን ይፈልጋሉ።
በፓኪስታን ለባለቤቷ ፍትህ ማግኘት እንዳልቻለች ለቢቢሲ ተናግራለች።
ለጋዜጠኞች የምታደርገው የጥበቃ ዘመቻዋን እንደምትቀጥል እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ሲፒጄን እርዳታ እንደምትፈልግ ተናግራለች።












