ተመልካቾች፣ ደራሲው እንዲሁም ተዋንያኑ ክብረ ወሰን የያዙበት ተውኔት “ባቢሎን በሳሎን”

የፎቶው ባለመብት, SocialMedia
“በባቢሎን በሳሎን” ባለ ትዳሮቹ መካከል ንፋስ ገብቷል።
ባለትዳሮቹ ውብሸት እና ትዝታ ነው የሚባሉት። በአለማየሁ ታደሰ እና በሉሌ አሻጋሪ ተወክለዋል።
በመካከላቸው ያለውን የጠብ ግድግዳ ለማፍረስ ያልቻሉት ባልና ሚስት፣ ውብሸት እና ትዝታ፣ አንዳቸው ሌላኛቸውን ለማስቀናት የማይፈነቅሉት የነገር ቋጥኝ የለም።
የገፀ ባህሪያቱ የትዳር ቋንቋቸው ሲደበላለቅ፣ የተመልካቾች ግን ኅብር ሰርቶ በአንድ ሳንባ ይተነፍሳል።
የመድረኩ መጋረጃ ሲከፈት የምንመለከተው ቤት በጠብ ምክንያት የተከፈለ ሳሎን ነው።
የተውኔቱ ታሪክ ስስ ነው። ግን በሁሉም ተመልካች የዕለት ተዕለት አጋጣሚ ውስጥ ያለ ይመስላል።
የአለማየሁ ታደሰ እና የሉሌ አሻጋሪ [ውብሸት እና ትዝታ] ትዳር ያሳዝናል፤ ግን የሚለቀስለት ዓይነት አይደለም፤ የሚሳቅበት እንጂ።
በራስ ቁስል እንደመሳቅ ነው።
ሁለቱም ሠራተኞቻቸውን እና የግድግዳ ጥቅሳቸውን ተካፍለዋል።
ተመልካቹ ግን አንዱን አምርሮ አይደግፉም፤ ወይንም ደግሞ ሌላኛውን አይጠላም፤ ለምን ተጣሉ ብሎም አይሞግትም።
እንዲሁ በውብሸት እና ትዝታ ትዳር እንደሳቀ 22 ዓመት እንደዘበት ነጎዱ።
የቴአትሩ ደራሲ ውድነህ ክፍሌ ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ወቅት እንዳለው፣ ከሌሎች ተውኔቶች ሁሉ በተለየ መልኩ በተመልካች ብዛት ቀዳሚው ነው።
ሁሌም እንደ አዲስ ቴአትር ተመልካቾች በግፊያ የሚያዩት ቴአትር መሆኑ፣ ለእርሱ ለራሱም ይገርመዋል።
በዛሬው ዕለት [ዕሁድ መስከረም 29/2015 ዓ.ም.] የዕይታ ዘመኑን ጨርሶ ከመድረክ ሊወርድ መሆኑን ሰምተን ስንደውልለት ፈገግ ብሎ “ይወርዳል ተብሏል፤ የወደፊቱን አናውቀውም” ሲል መልሷል።
ፀሐፌ ተውኔት ውድነህ ለዚህ መልሱ እውነት አለው። ባቢሎን በሳሎን በተለያየ ጊዜ ከመድረክ ቢወርድም ዳግም ወደ ዕይታ ተመልሷል።
በዚህ ጊዜ ሁሉ ከተመልካቹ ጋር አፍላ ፍቅር ውስጥ ነው።

የፎቶው ባለመብት, sileTheatre
ቅርስ የሆነው ባቢሎን በሳሎን
ባቢሎን በሳሎን ለመድረክ ሲበቃ የተጋቡ ወልደው ልጃቸውን ወደ ዩኒቨርስቲ ልከዋል።
ታዳጊ የነበሩ ወጣትነታቸውን እያጣጣሙ ነው። ትምህርት ቤት የነበሩ ተመርቀው ሥራ ይዘዋል።
በ22 ዓመት ውስጥ ከ76 ጊዜ በላይ ያዩ ተመልካችም አሉ።
አቶ አለማየሁ ግርማ የተባሉት ተመልካች፣ ባቢሎን በሳሎንን ለ43ኛ ጊዜ ሲመለከቱ፣ ብሔራዊ ቴአትር እስከ እነ ባለቤታቸው ጠርቶ ዳቦ እንዲቆርሱ በማድረግ፣ “እንዳከበሩን እና እንደወደዱን ክብረት ይስጥልን፣ የፍቅር ሸማ ያልብስልን” ብሏቸዋል።
እኚህ ተመልካች ከዚህ በኋላም ቴአትሩን ማየታቸውን ቀጥለው 76 ጊዜ መመልከታቸውን በአንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ቀርበው መስክረዋል።
ሌሎች ተውኔቶች በተመልካች ጠኔ ሲያዛጉ፣ በገቢ ማጣት መቅኔያቸው ሲፈስ፣ ባቢሎን በሳሎን ግን ደረቱን ነፍቶ የሚመሰክርላቸው ተመልካቾች አሉት።
በየሳምንቱ ከ900 ተመልካቾች በላይ አዳራሹን ሞልተው በሳቅ ያወካሉ።
ከተዋንያኑ ጋር እኩል ቃለ ተውኔቱን የሚያነበንቡ ተመልካቾችም ተገኝተዋል።
ደራሲው በስም የሚጠቅሳቸው እንደ ታገል ሠይፉ እና ጌጡ ተመስገን ያሉ ደራሲያን እና ጋዜጠኞች ጭምር ደጋግመው አይተውታል።
የኢትዮጵያ ቴአትር ታሪክ ሲነሳ ረዥም ጊዜ በመታየት ስሙ በቀዳሚነት የሚነሳው ባቢሎን በሳሎን ነው።
ይህም ባቢሎን በሳሎንን በአገር ደረጃ ቅርስ ያደርገዋል ሲል ይናገራል ውድነህ።
ቴአትሩ ከተጻፈበት እስከ ለመድረክ አስከበቃበት ዓመት ድረስ ቢታይ በአገሪቱ ውስጥ በርካታ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ተከናውነዋል።
በእነዚህ ሁሉ ጊዜያት በአንድ ልብ የቴአትር አፍቃሪያንንን አግባብቶ፣ እግሮችን ሁሉ ወደ ቴአትር ቤት የመራው ባቢሎን በሳሎን ነው።
“ባቢሎን የቴአትር ቅርሳችን ነው ብዬ ነው የማስበው” ይላል ውድነህ።
ይህ ተመልካቾች፣ ደራሲው እንዲሁም ተዋንያኑ ክብረ ወሰን የያዙበት ተውኔት በምሁራን ዘንድ “ከቴአትር በላይ ተቋም የሆነ” እስከመባል የደረሰው ለዚህ ይሆናል።
በ100 ዓመት የኢትዮጵያ ቴአትር ታሪክ ውስጥ በበርካታ ጉዳዮች ቀዳሚ በመሆን ስሙ ይነሳል።
ከአዲስ አበባ ተነስቶ የተለያዩ የክፍለ ሀገር ከተሞች ታይቷል።
ሉሌ አሻጋሪ፣ አለማየሁ ታደሰ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ ፍቃዱ ከበደ፣ ህንጸተ ታደሰ እንዲሁም ሌሎቹ የኢትዮጵያ ቴአትር ታሪክ ውስጥ ረዥም ጊዜ አንድን ቴአትር በመተወን ስማቸውን ተክለዋል።
ባቢሎን በሳሎን በ22 ዓመት የመድረክ ቆይታው ተዋንያኖቹ ተቀያይረዋል።
ውድነህ ሉሌ አሻጋሪ ከምትሰራው ገፀ ባህሪ ውጪ፣ ሁሉም ገፀ ባህሪያትን በመወከል የተለያዩ ተዋንያን ተጫውተዋል ሲል ይናገራል።
በተለይ የደለለኝ ግን ይለያል።
ደለለኝ የተሰኘውን ገፀ ባህሪ ሰሞን ቦጋለ፣ ዳንኤል ተገኝ፣ ጌታሁን ሰለሞን፣ ያረጋል አጥናፉ፣ ሳምሶን ታደሰ፣ ሰለሞን ሙላትን ጨምሮ ዘጠኝ ተዋንያን ተቀያይረው ሰርተውታል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጥናታቸውን እየሰሩ የሚገኙ ሰዎች ባቢሎን በሳሎን በኢትዮጵያ ቴአትር ውስጥ ረዥም ጊዜ መድረክ ላይ በመቆየት የክብረ ወሰን ባለቤት ነው ይላሉ።
ከዚህ አለፍ ሲል ለመሆኑ በአፍሪካስ ይህን ያህል ጊዜ መድረክ ላይ የቆየ ተውኔት ይኖር ይሆን? ሲሉ ይጠይቃሉ።
በእርግጥ ይህ ጥያቄያቸው ገና በጥናት ላይ ያለ በመሆኑ እርግጡን መናገር ያስቸግራል።
ባቢሎን በሳሎን በኦሮምኛ ተተርጉሞ ተመድርኳል። በአዲስ አበባ እና በጅማ ዩኒቨርስቲ የትያትር ጥበባት ተማሪዎችም ተጫውተውታል።
ውድነህም አዳዲስ ተዋንያን፣ በአዲስ ጉልበት ከዘመን ዘመን እየተቀባበሉት ቢሰሩት ደስተኛ መሆኑን ይናገራል።
“ይሰራልም. . .ስክሪፕቱ ላይም አዲስ መነካካት የምፈልገው ነገር አለኝ። አንዳንድ ገፀ ባህሪያት ላይ ያኔ በልጅነትም የተጻፈ በመሆኑ ያየኋቸው ክፍተቶችም አሉ። ይህ ገፀ ባህሪ እንዲህ ቢሆንስ? የሚል ሃሳብ አለኝ ስለዚህ ደግሜ ማየት እፈልጋለሁ።”

የፎቶው ባለመብት, socialMedia
የባቢሎን በሳሎን የመወደድ ምስጢሮች
ውድነህ ክፍሌ“እኔ ከባቢሎን በሳሎን በኋላ ዘጠኝ ቴአትሮችን ለመድረክ አብቅቻለሁ” ይላል።
ስለ እነዚህ ሥራዎቹ ሲናገር “በሐሳብ፣ በርዕሰ ጉዳይም ከባቢሎን በሳሎን በጣም የተሻሉ” መሆናቸውን ይገልጻል።
እነዚህ ቴአትሮች ግን ረዘመ ከተባለ፣ ሦስት ዓመት የመድረክ ቆይታ ብቻ ነው የነበራቸው።
ባቢሎን በሳሎን ዕለት በዕለት እያማረበት፣ ወዳጆች እያበዛ፣ እድሜውን ሲቀጥል የእነርሱ ዕጣ ፈንታ ለአዲስ መጤ ተውኔት መድረካቸውን መልቀቅ ሆነ።
ለምን?. . .
ይህንን ደፍሮ ለመናገር ጥናት ይጠይቃል። ግን ደራሲውን እንዲገምት ዕድል እንስጥ።
ኮሜዲ መሆኑ፣ አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይጠረጥራል።
ታድያ ሳቅን ስንቅ ያደረገው በሐሳቦች ላይ ሳይሆን በገፀ ባህሪያቱ ላይ መሆኑ ዘመንን እንዲሻገር አድርጎታል።
ባልና ሚስቱ በመካከላቸው የገባው ንፋስ ሳሎናቸውን እስከ መካፈል አድርሷቸዋል።
በእርግጥ አልወለዱም፤ የሚያገናኛቸው ቀጭን ገመድ ፍቅር ነው።
ዝግጅቱ እና ትወናውም ለመወደዱ ሰበብ ሊሆን እንደሚችል ሌላኛው ግምቱ ነው።
ድንገቴ ፈጠራዎች፣ የመወደድ ምክንያቱ ሊሆን እንደሚችልም ጠቅሷል።
ባቢሎን በሳሎንን፣ ወደ ፈለግነው የመተርጎም ዕድል አለን ይላል ፀሐፌ ተውኔት ውድነህ።
የመተርጎም ነጻነቱን የተደራሲው ነው።
እንደ ባቢሎናውያን ቋንቋቸው የተደበላለቀባቸው ጓደኛሞች፣ ቤተሰቦች፣ ሕዝቦች ራሳቸውን መታዘቢያ ሊያደርጉት ይችላሉ።
ከዚህ በተረፈ ግን፣ ተመልካቾች ለባቢሎን በሳሎን የተለየ ፍቅር እንዴት ኖራቸው? ለሚለው ባለሙያ ጥናት ቢሰራበት ሲል ሐሳብ ያቀርባል ውድነህ ክፍሌ።
ደራሲው ራሱ ምን ያህል ጊዜ ቴአትሩን አይቶታል?
ባቢሎን በሳሎን ይህን ያህል ዓመት ሲቆይ በርካታ ማኅበራዊ ሕይወቶችን መመስረቱን ውድነህ ይናገራል።
እቁብ እንጥላለን፣ ቡና እንጠራራለን፣ ከመድረክ ጀርባ ሌላ ዓለም ነው ያለው ይላል በሳቅ ታጅቦ።
ባቢሎን በሳሎንን ተመልካቾች በትኩስ ፍቅር ለ22 ዓመት ካዩት ደራሲው ምን ያህል ጊዜ ተመልክቶታል? የእኛ ጥያቄ ነበር።
ውድነህ ቴአትሩ በሚታይበት ወቅት “ልክ እንደ አንድ ተዋናይ በየዕለቱ በቴአትር ቤት የመገኘት ልምድ አለኝ” ይላል።
ከተመልካች መካከል ሆኖ ሂሳቸውን የመስማት፣ ተዋናዮችን ከመድረክ ጀርባ ሄዶ የማናገር ልማድ አለው።
“ቴአትሩን ለማየት ብዬ ብቻ ሳይሆን ልክ እንደ አንድ ባለሙያ ስገኝ ደስ የሚል ስሜት ይሰጠኛል” ይላል።
በዚህ የተነሳ ቴአትሩን ላለፉት 22 ዓመታት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ደጋግሞ ለማየት ዘወትር ቴአትሩ ቤት ተገኝቷል።
ታድያ አንተ የየትኛውን ገፀ ባህሪ ቃለ ተውኔት በቃልህ ይዘሃል? ቀጣይ ጥያቄያችን ነበር።
“በጣም የሚገርመው ይህንን ሁሉ ቴአትር ጽፌ፣ የቴአትር ተማሪ ሆኜ፣ ቃለ ተውኔት በቃሌ መያዝ አልችልም” ይላል ውድነህ።
“ብዙ ጊዜ ትኩረቴ ድርሰቱ ላይ ነው። ገፀ ባህርያቱ የሚሉትን፣ አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር ያላቸውን መስተጋብር እንጂ ቃለ ተውኔት ለመሸምደድ ብዙም የምጨነቅ አይደለሁም። መጻፉ ብቻ ለእኔ ከባድ ስለሆነ፣ ቃለ ተውኔቱን ለመያዝ ብዬ ተጨማሪ ሥራ በራሴ ላይ አልጫንኩም።”

የፎቶው ባለመብት, SocialMedia
ባቢሎን በሳሎን እንዴት ተጻፈ?
የውድነህ ልጅነት ሜክሲኮ፤ ዲአፍሪክ አካባቢ፤ 50 ቀበሌ ውስጥ የተተከለ ነው።
ታድያ ዲአፍሪካ አቅራቢያው አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ይገኛል።
ውድነህ በኖረበት ሰፈር ዘወትር ምሽት ተጣልተው፣ ለገላጋይ አስቸግረው ፖሊስ ጣቢያ የሚሄዱ የትዳር አጋሮች ነበሩ።
ለውድነህ ባቢሎን በሳሎን መነሻ የሆነው እነዚህ አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ የሚመላለሱ ባልና ሚስቶች ናቸው።
እነዚህ ባልና ሚስቶች በተጣሉ ቁጥር ጎራ ከፍለው፣ የሴት ወገን የወንድ ወገን በማለት፣ ለድጋፍ የሚሰለፉ መንደርተኞም ነበሩ።
እነዚህ መንደርተኞች በየጎራቸው ባልን ደግ አደረግክ፣ ሚስትን አይዞሽ እያሉ ፖሊስ ጣቢያ ሲያደርሱ ነገሩ መልኩን ይቀይራል።
የእነዚህ ባለትዳሮች ጠብ ፖሊስ ጋር ደርሶ፣ የሕግ ሰው ሲገባበት በዕርቅ ይደመደማል።
ያኔ እነዚህ የጠብ ጥንስስ አስክሯቸው የነበሩ፣ የጎራ ሚና ሊያቃቅራቸው ንቃቃት ይፈልግ የነበረው ትዳራቸውን መልሰው በእጃቸው በማስገባት፣ በሁለት እግሩ አቁመው ተቃቅፈው “የሰደቧቸውን እየሰደቡ” ወደ ቤት ይመለሳሉ።
ለዚህ ተውኔት መነሻ የሆነኝ “እነዚሀ መለያየት የማይችሉ አብረው ለመኖርም የሚቸገሩ ባልና ሚስቶች ናቸው” ይላል ውድነህ።
ውድነህ “በተውኔቴ ውስጥ ያሉት ገፀ ባህሪያት በሙሉ በዙሪያዬ የማውቃቸው፣ ቤቴ ውስጥ፣ የምኖርበት ግቢ ውስጥ የነበሩ አብሬ የዋልኳቸው፣ ቅርቤ የሆኑ ሰዎች ናቸው” ይላል።
ለውድነህ ቴአትር ለመጻፍ የሚያተጋህ ምንድን ነው? ሲባል “ተውኔትን ስለምወደው ነው። ስሜቴን በደንብ የሚገልጽልኝ ተውኔት ስለሆነ ነው። ተውኔት ሰትጽፍ ትንሽ ትንሽ ያሳብዳል፤ እብደቷንም ስለምወዳት ነው” ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Social Media
ውድነህ ክፍሌ በመጋረጃ ቀዳዳ ያያት ቴአትር
ፀሐፌ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ መጀመሪያ ለመድረክ የበቃለት “ሞተ ሞተ” ሲል የሰየመው ቴአትር ነው።
በሳምሶን ወርቁ የተዘጋጀው ይህ ተውኔት በአዲስ አበባ ከተማ ባህል አዳራሽ (ማዘጋጃ) ቴአትር ቤት፣ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን እና ሌሎች አንጋፋ የጥበብ ሰዎች በተገኙበት ሲታይ፣ ውድነህ መግባት አልቻለም።
በወቅቱ ለሰዎች ዐይን አልሞላም፤ የሚለብሰውም ቢሆን በሰዎች ፊት የሚያቆመው እንዳልነበር ያስታውሳል።
“ሞተ ሞተን፣ ሞቼ ሞቼ ነው ያየሁት” የሚለው ውድነህ ደጋግሞ እየተሹለከለከ ሲገባ፣ የጥበቃ ጓዱ ሲያገኘው ኮሌታውን ጨምድዶ ያስወጣዋል።
“ደራሲው እኔ ነኝ ለማለት ራሱ አፍር ነበር” ያለው ውድነህ “በመጋረጃ ቀዳዳ ያየኋት” ቴአትሬ ናት ይላል።
ውድነህ ከዚያ በኋላ 14 ተውኔቶችን ለመድረክ አብቅቷል።
ሞጋቾች፣ ግማሽ ጨረቃ፣ የሌሊት ጧፍ የተሰኙ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎችን ጽፏል።
ላማ ሰበቅተኒ የተሰኘ እና 174 ገጽ ያለው ረዥም ልብወለድ ለንባብ አብቅቷል።
በዚህ ዓመትም በእርሱ የተጻፉ አምስት ተውኔቶች በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት እየተዘጋጁ ናቸው።
የሌሊት ሙሽሮች (በዕይታ ላይ ያለ)፣ የደፈረሱ ዓይኖች (ከ15 ቀን በኋላ ለዕይታ የሚበቃ)፣ በዓሉ ግርማ (በዝግጅት ላይ ያለ)፣ ዱልዱም ካራ፣ እና ሌሎችም በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ከሚቀርቡት መካከል ናቸው።
ከ20 ያላነሱ አጫጭር የቴሌቪዥን ድራማዎች፣ ከ60 ያላነሱ የሬድዮ ድራማዎች ጽፏል።
ለውድነህ፣ ባቢሎን በሳሎንን ከመድረክ ሲያጡ፣ ሳቅ ከፊታቸው ላይ የሚነጥፍ ለሚመስላቸው ታዳሚዎች ምን አስበሃል? የመሰናበቻ ጥያቄያችን ነበር።
“ባቢሎን በሳሎንን፣ ከታፈነ ጩኸት እና ከበዓሉ ግርማ ተውኔቶች ጋር የማሳተም ዕቅድ አለኝ” የእርሱ መልስ ነው።
ባቢሎን በሳሎን ከመድረክ ሲወርድ ልባቸው በሐዘን የሚሰበረው ግን ተመልካቾች ብቻ አይመስሉም።
ደራሲው እና ተዋንያኑም ክብረ ወሰናቸውን ለማሻሻል ተጨማሪ ዕድል ባለማግኘታቸው ማዘናቸው አይቀርም።
ውድነህ እንደሚለው 'ማን ያውቃል ጊዜ ጠብቆ ባቢሎን በሳሎን ዳግም ለዕይታ ይበቃ' ይሆናል።
እስከዛው ግን 'ባይ ባይ ባቢሎን በሳሎን' ለማለት ዛሬ መስከረም 29 2015 ዓ.ም አፍቃሪዎቹ ይገኛሉ።












