የኬንያ ፍርድ ቤት በአገሪቱ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቀልበስ ጦሩ እንዲሰማራ ወሰነ

የኬንያ ጦር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአገሪቱ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቀልበስ እና የተነሳውም ሁከት እንዲረጋጋ በሚል ጦሩ እንዲሰማራ ውሳኔ አሳለፈ።

ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው ማክሰኞ ሰኔ 18/ 2016 ዓ.ም በነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ወጣቶች ፓርላማውን ከተቆጣጠሩ በኋላ ነው።

የግብር ጭማሬዎችን ያካተተው የፋይናንስ ህግን ለመቃወም አደባባይ በወጡ ተቃዋሚዎች ላይ በተተኮሰ ጥይት ከ20 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

በመላ አገሪቷ ከተከሰተው እና የበርካቶችን ሕይወት ከቀጠፈው ተቃውሞ በኋላ ረቂቁ በፓርላማው ቢጸድቅም ፕሬዚዳንቱ ሕግ ሆኖ እንዲያልፍ የመጨረሻ ፊርማዬን አላስቀምጥም ብለዋል።

በሥራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነት፣ ተደራራቢ ግብር በቃን እንዲሁም ከሰሞኑ በተነሳው ተቃውሞ ሰልፈኞች በፖሊስ መገደላቸው ከፍተኛ ቁጣ የፈጠረበት ኬንያውያን የተቃውሞ መልካቸውን ቀይረው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከሥልጣን እንዲወርዱ እየጠየቁ ነው።

በዛሬው ዕለት በመዲናዋ ናይሮቢ የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት ዘልቀው ሊገቡ በሞከሩ ተቃዋሚዎችን ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ በመርጨት ሊበትን ሞክሯል።

በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎችም የታጠቁ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችም ታይተዋል።

የፍርድ ቤቱ አንደኛው ዳኛ የአገሪቱን ጦር ማሰማራቱ የመንግሥት ተቋማትን ለመጠበቅ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ነገር ግን ባለስልጣናቱ ለምን ያህል ጊዜ ጦሩ እንደሚቆይ እና በምን መንገድ እንደሚሳተፍም ለማብራራት ሁለት ቀናትን ሰጥተዋል።

“የጦሩን የኃላፊነት ወሰን እና የሚቆይበትን ጊዜ ሳይገለጽ ዝም ብሎ በጠቅላላው ማሰማራት አገሪቱን ወደ ወታደራዊ ዞን ሊቀይራት የሚችል አደገኛ አዝማሚያ ነው” ሲሉ ዳኛ ላውለንስ ሙጋምቢ ገልጸዋል።

የአገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት ወደ ጦር ሰፈሩ እንዲመለስ ለፍርድ ቤት አቤቱታ ያቀረበው የኬንያ የህግ ማህበር ውሳኔውን “ቢያከብርም ነገር ግን አልስማማበትም” ብሏል።

የመንግስት ቃል አቀባይ አይዛክ ምዋውራ የፋይናንስ ህጉ ውድቅ መደረግ በበጀቱ ላይ ትልቅ ክፍተት እንደሚፈጥር ጠቅሰው ለመንግሥት “ትልቅ ሽንፈት ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፋይናንስ ህጉን እየተቃወሙ ያሉትንም “በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመስርተው ነው” ሲሉም ወቅሰዋል።

“በርካቶች ለአመጽ እንዲነሱ በአገር አቀፍ እና በአለም አቀፍ ደረጃ የተሳሳቱ መረጃዎችን የማዛመት የተቀነባበረ ዘመቻ ነበር” ብለዋል።

መንግሥት በእነዚህ የቀረጥ ጭማሪዎች 2.7 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ እና አገሪቷ ያለባትን የዕዳ ጫና ለማቃለል ይውላል ሲል እየተሟገተ ቆይቷል።

ኬንያ በአሁኑ ጊዜ ያለባትን 80 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብሔራዊ ዕዳን ለመቀነስ የተለያዩ ግብሮችን መጣል አንዱ እርምጃ ነው ይላል መንግሥት።

ተቃውሞው በዛሬው ዕለት የቀጠለ ሲሆን የመንግሥት የደህንነት ሰዎች ከተቃውሞው ጋር የተገናኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አፍነው በመውሰድ ተከሰዋል።

በመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት የኬንያ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በህገወጥ መንገድ የታሰሩ ከ300 በላይ ሰዎች እንዲፈቱ ማድረጉን ገልጿል።

ቃለ አቀባዩ ይህንን አስተባብለው “መፈንቅለ መንግሥት የሚፈልጉ ወንጀለኞች” ሰላማዊ ሰልፉን ለመጠቀም ሞክረዋል ብለዋል።