በሕንድ በሐሰት “ታግቻለሁ” ያለችው አሜሪካዊት ለእስር ተዳረገች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሕንድ ዋና መዲና፣ ዴልሂ ፖሊስ በራሷ ላይ እገታ ፈፅማለች ያላትን አሜሪካዊት በቁጥጥር ሥር አዋለ።
ፖሊስ እንዳለው የ27 ዓመቷ አሜሪካዊት ያላትን ገንዘብ ከጨረሰች በኋላ ቤተሰቦቿን ገንዘብ ለማስላክ በሐሰት እንደታገተች ተናግራለች።
እንደ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ከሆነ፣ ግለሰቧ ሕንድ የገባችው በአውሮፓውያኑ ግንቦት 3 ቀን 2022 ሲሆን ለእናቷ ሐምሌ 7 ቀን ደውላ በአንድ ግለሰብ ጥቃት እንደደረሰባት ተናግራለች።
የአሜሪካ ኤምባሲም ከቤተሰቦቿ የደረሰውን ጥቆማ ለፖሊስ ካሳወቀ በኋላ ግለሰቧ ያለችበትን ለማወቅ ፖሊስ ምርመራ ጀመረ።
ፖሊስም ግለሰቧ ለአሜሪካ የዜጎች አገልግሎት ኢሜይል የላከችበትንና ለእናቷ በቪዲዮ የደወለችበትን የስልክ መለያ አድራሻ [አይፒ] በመፈለግ ክትትል ማድረግ መቀጠሉን 'ኢንዲያን ኤክስፕረስ' ጋዜጣ ዘግቧል።
በዚህ አሰሳ መሠረትም ፖሊስ የ31 ዓመቱን ናይጄሪያዊ ግለሰብ ተከታትሎ በቁጥጥር ሥር ማዋል ቻለ።
በፖሊስ ምርመራ ወቅትም ናይጄሪያዊው ግለሰብ አሜሪካዊቷ ከዴልሂ ወጣ ብሎ በሚገኘው ኖይዳ አፓርታማ ውስጥ እንደምትገኝ ተናግሯል።
ግለሰቧ ከተገኘች በኋላም “ወላጆቿን ለማታለል ድርጊቱን መፈፀሟ” መረጋገጡን የኒው ዴልሂ ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር አምሩታ ጉጉሎዝ፣ ለኢንዲያን ኤክስፕረስ አስረድተዋል።
ፖሊስ እንዳለው ከአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ወደ ሕንድ ያመራችው ግለሰቧ፣ ሕንድ ከገባችበት ጊዜ አንስቶ በፌስቡክ ከተዋወቀችው ናይጄሪያዊው ጋር ነበር የቆየችው።
ከዚህም በተጨማሪ የግለሰቧ ቪዛ እና የግለሰቡ ፓስፖርት ጊዜው እንዳለፈበት ፖሊስ ገልጿል።
በመሆኑም ሕጋዊ ሰነዶች ሳይኖራቸው ሕንድ ውስጥ በመቆየታቸው በሁለቱ ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንደሚወስድም ፖሊስ አስታውቋል።












