ማርኮ ሩቢዮ በሦስት ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ተወያዩ

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር መነጋገራቸውን መሥሪያ ቤታቸው ባወጣው መግለጫ አመለከተ።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ኃላፊው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ባደረጉት ውይይት አገሮቻቸው በቀጣናዊ መረጋጋት ዙሪያ ባላቸው የጋራ አቋም እና በፀረ ሽብር እንቅስቃሴ በሚያደርጉት ትብብር ዙሪያ ተነጋግረዋል።
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ በኩል በወጣው አጭር መግለጫ ላይ እንደተመለከተው ሁለቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተጨማሪም በምጣኔ ሀብታዊ ትብብር፣ እንዲሁም ለአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ደኅንነት መሠረት በመጣል ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ባወጣው አጭር መግለጫ በማርኮ ሩቢዮ እና በዐቢይ ዐሕመድ መካከል የተደረገው ውይይት ላይ የተነሱ ጥቅል ጉዳዮችን ከመጥቀስ ባሻገር ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ ተቆጥቧል።
ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር የተደረገውን ንግግር በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽሕፈት ቤት በኩል እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም።
መጋቢት 2/2018 ዓ.ም. በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከል ውይይት የተደገረው አሜሪካ ከእስራኤል ጋር በመሆን በኢራን ላይ እያካሄደችው ያለው ጦርነት ሁለተኛ ሳምንቱን ሊይዝ ጥቂት ቀናት በቀሩት ጊዜ ነው።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በተለያዩ ጊዜያት ውይይት ያደርጉ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ ውይይት ነው።
በዚህ ዓመት ኅዳር 24/2018 ዓ.ም. በተመሳሳይ ሁለቱ ባለሥልጣናት ተመሳሳይ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጾ የነበረ ሲሆን፣ በውይይቱ ላይ በተመሳሳይ ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ መረጋጋት ያላቸውን ቁርጠኝነት እና ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም መሠረት በመጣል ዙሪያ መነጋገራቸውን ተዘግቧል።
ኢትዮጵያ እና አሜሪካ የጠበቀ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፣ በተለያዩ መስኮች ላይ በትብብር እንደሚሠሩ ሲያሳውቁ ቆይቷል። በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰውን አልሻብብ ታጣቂ ቡድንን ለመቆጣጠር በጋራ እንደሚሠሩ ይታወቃል።
በቅርቡም የአሜሪካ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መገናኘታቸው ይታሳል።
በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያ ከገነባቸው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ግብፅ እና ኢትዮጵያን ለማደራደር ፈቃደኛ መሆናቸውን ከአንድ ወር በፊት ለግብፁ ፕሬዝዳንት በጻፉት ደብዳቤ ገልጸው ነበር። ነገር ግን አስካሁን የተጀመረ ነገር ስለመኖሩ የሚታወቅ ነገር የለም።















