ስምረት ፓርቲ በአወዛጋቢ ቦታዎች ላይ የሚካሄድ ምርጫን በተመለከተ ያቀረበውን ክስ ለምን አነሳ?

አቶ ጌታቸው ረዳ

የፎቶው ባለመብት, PM Office

የምስሉ መግለጫ, አቶ ጌታቸው ረዳ
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ "አወዛጋቢ" ቦታዎችን በተመለከተ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ በመቃወም ምርጫ ቦርድ ላይ ያቀረበውን ክስ ማንሳቱን አስታውቋል።

ፓርቲው ረቡዕ መጋቢት 2/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ "የሕግ መሠረት በሌለው ሰነድ ላይ ተመሥርቶ ክርክሩን መቀጠል የክቡር ፍርድ ቤቱን ውድ ጊዜ እና የሕዝብን ሀብት ያለአግባብ ማባከን ሆኖ አግኝተነዋል" ብሏል።

ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ሲመለከት የቆየበት ገለልተኛ እና ሕጋዊ አካሄድ በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለውን "እምነት የሚያጠናክር" መሆኑን የገለጸው ፓርቲው፣ "በአሁኑ ወቅት ክሳችንን መቀጠል አስፈላጊ ሆኖ ስላላገኘነው በፍትሃ ብሔር ሥርዓት ሕግ ቁጥር 278(1) መሠረት ክሳችንን ሙሉ በሙሉ አንስተናል" ሲል ገልጿል።

ስለጉዳዩ ለቢቢሲ ምላሽ የሰጡት የፓርቲው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ነጋ አሰፋ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ "አጠቃላይ የፌዴሬሽን ም/ቤቱን ምልዓተ ጉባዔ ሳያሟላ አፈ ጉባዔው ብቻ የወሰኑት ነው" በሚል ክሳቸውን ማንሳታቸውን እና "ጉዳዩ ፖለቲካዊ ውሳኔ ስለሆነ ፖለቲካዊ መፍትሄ" እንደሚፈልጉለት ተናግረዋል።

ቢቢሲ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ለጊዜው ምላሽ አላገኝም።

ስምረት ፓርቲ መጀመሪያ ላይ ክሱን ሲያቀርብ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ ከሥልጣኑ ውጪ የሆነ እና "ሌላ ግጭት የሚቀሰቅስ፣ በሕገመንግሥት የተሰጠውን ሥልጣን የጣሰ ስለሆነ ትክክል አይደለም" በሚል እንደነበር አብራርተዋል።

አቶ ነጋ ፓርቲው ክሱን መሥርቶ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ እንዲታገድ ካደረገ በኋላ "ወደ ማጣራት ስንሄድ ውሳኔውን ምክር ቤቱ አለመወሰኑን ነው ያጣራነው" ብለዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ አካሄድ አለው ያሉት አቶ ነጋ "አባላቱ ተጠርተው፤ ሁሉም ተገኝተው ተወያይተውበት የሚወስኑት፣ ስህተትም ቢሆን ትክክል በምልዓተ ጉባዔ መጽደቅ ነበረበት" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"አሁን ስናረጋግጥ አፈ ጉባዔው ለብቻቸው የወሰኑት ውሳኔ በመሆኑ እንደዚህ ዓይነት ውሳኔ ደግሞ የሕግ መሠረት ስለሌለው" በማለት ክሳቸውን ማቋረጣቸውን አስረድረተዋል።

"ይህ ፖለቲካዊ ጉዳይ ነው፤ ከአሁን በኋላ መታየት እና መመለስ ያለበት በፖለቲካዊ መልኩ ነው" በሚል ክሳቸውን ማቋረጣቸውን ጨምረው አስረድተዋል።

ስምረት ፓርቲ መጀመሪያ ውሳኔውን ያሳለፈው የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለምን በቀጥታ እንዳልከሰሰ የተጠየቁት አቶ ነጋ፣ የመጀመሪያ ክሳቸው "ምክር ቤቱ ያለ ሥልጣኑ ነው የወሰነው" ብለውን ክስ መመሥረታቸውን አብራርተዋል።

"ክሱ ምርጫ ቦርድ ተሳስተሃል ሳይሆን ውሳኔውን ያቀረበው አካል ፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው።. . . [የምክር ቤቱ] ውሳኔ ስህተት ነው። በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣን ተላልፎ . . . ሌላ ክልል የማዋቀር ሥራ ነው የሠራው እና ያ የሠራው ሥራ ትክክል ስላልሆነ ፍርድ ቤቱ ይህንን እንዲያግድልን. . . ነበር ክስ ያቀረብነው" ብለዋል።

በተጨማሪም የፌዴሬሽን ምክር ቤቱን ተጠሪ ያላደረጉበት ምክንያት ሲያብራሩ ውሳኔው የወጣው በምርጫ ቦርድ በኩል በመሆኑ እንደሆነ አክለው ተናግረዋል።

"ምርጫ ቦርድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይህንን ውሳኔ ሰጥቶኛል ብሎ ስላቀረበ እርሱን ጠይቀናል" ያሉት አቶ ነጋ "ውሳኔውን አሁን ስናጣራ ግን ምክር ቤቱም አልወሰነም" ብለዋል።

አቶ ነጋ በመጀመሪያም ምክር ቤቱ ውስጥ የትግራይ ውክልና የለም ያሉ ሲሆን፣ ውሳኔውንም የወሰነው በሕገ መንግሥት የተሰጠውን ሥልጣን ተጠቅሞ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል።

ከሥልጣኑ ውጪ ወስኗል ብለን እያሰብን ሳለ አሁን አጣርተን እንዳደረስንበት ምክር ቤቱ ሳይሆን "በግለሰብ ደረጃ" የተወሰነ መሆኑን ነው ብለዋል።

ውሳኔው በግለሰብ ደረጃ ለመወሰን የሕጋዊ መሠረት የለውም ያሉት አቶ ነጋ፣ በጉዳዩ ላይ ጊዜ ማጥፋት እንደማያስፈልግ እና "ይህ ፖለቲካዊ ጉዳይ ስለሆነ በፖለቲካዊ ውሳኔ ነው መመለስ ያለበት ብለን ክሳችንን አንስተናል" ሲሉ አስረድተዋል።

ስምረት ፓርቲ ክሱን ማንሳቱን ተከትሎ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰጥቶት የነበረው ዕግድ ከተነሳ ምርጫ አወዛጋቢ በሆኑት በአምስቱ የምርጫ ክልሎች ይካሄድ እንደሆን የተጠየቁት አቶ ነጋ "አይካሄድም" ብለዋል።

"ውሳኔው የግለሰብ ውሳኔ ስለሆነ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው። የሕግ መሠረት ያለው ውሳኔ አይደለም፤ የሕግ መሠረት ያለው ቢሆን በሕግ ተከራክረን እንድናሸንፍ ነበር ሃሳባችን፤ ኋላ ስናየው ግን የሕግ መሠረት የለውም የግለሰብ ውሳኔ ነው።"

ውሳኔው ፖለቲካዊ ስለሆነ በፖለቲካዊ ንግግር እና ድርድር ጥያቄያቸው ምላሽ እንደዲያገኝ እንደሚያደርጉ የስምረት ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ነጋ ተናግረዋል።

ምርጫ ቦርድ ምርጫን የሚያካሄደው "አንድ ሰው በወሰነው ውሳኔ መሠረት ሳይሆን በሕገመንግሥቱ ነው" ያሉት አቶ ነጋ "ሕገ መንግሥቱ ደግሞ እነዚያ ስፍራዎች እስካሁን ባለው የትግራይ ሉዓላዊ ግዛቶች ናቸው" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በተካሄዱት ስድስት ምርጫዎች በእነዚህ አካባቢዎች ምርጫ የተካሄደው በትግራይ ክልል ውስጥ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ነጋ "አሁን እንደ አዲስ በግለሰብ ደረጃ አዲስ የምርጫ ክልል ማዋቀር ስለማይቻል ወደነበረበት ይመለሳል የሚል እምነት ነው ያለን" ብለዋል።

ስምረት ፓርቲ የእነዚህ አወዛጋቢ የምርጫ ክልሎችን በተመለከተ ሕገመንግሥቱን እና የፕሪቶሪያው ስምምነትን መሠረት በማድረግ "እንወያያለን፣ እንከራከራለን አናስመልሰዋለን" ሲሉ ተናግረዋል።

የወልቃይት ጠገዴ አማራ የማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ እንዲሁም አብንን ጨምሮ ሌሎች አካላት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአከራካሪ የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ እንዲያካሄድ ባሳለፈው ጊዜያዊ ዕግድ ውስጥ ገብቶ ለመከራከር አቤቱታ አቀረበው ነበር።

ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአወዛጋቢ የምርጫ ክልሎች ላይ የሰጠው ውሳኔ የማይስተካከል ከሆነ በምርጫ እንደማይሳተፍ ማስታወቁ ይታወሳል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የምርጫ ቦርድ ውሳኔ መሰማቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫም የቦርዱ ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር እና ግጭትን የሚቀሰቅስ ነው በማለት ተቃውሞታል።

በተቃራኒው የአማራ ክልል ፖለቲከኞች የምርጫ ቦርድ ውሳኔን በመደገፍ መግለጫዎች አውጥተዋል።