የፋርስ ባሕረ ሰላጤው ጦርነት ከነዳጅ ዋጋ በተጨማሪ የሚያስከትላቸው ሦስት ወሳኝ ተጽዕኖዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እስራኤል እና አሜሪካ በኢራን ላይ የጀመሩት ጦርነት አንድ ሳምንት እንደሞላው ተጽዕኖው ከመካከለኛው ምሥራቅ አልፎ በዓለም ምጣኔ ሀብት ላይ መሰማት ጀምሯል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ዋጋ በበርሜል ከ100 የአሜሪካ ዶላር በላይ ያለፈ ሲሆን፣ ይህም ከ2022 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ሆኖ ተመዝግቧል።
ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ 70 የአሜሪካ ዶላር ነበር።
የዓለም የነዳጅ ዋጋ መጨመር የተከሰተው የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋትን ተከትሎ የመጣ ሲሆን፣ የኢራን መንግሥት በወሽመጡ የሚንቀሳቀሱ የንግድ መርከቦችን ዒላማ እነደሚያደርግ አስጠንቅቋል።
የዓለም 20 በመቶ ነዳጅ የሚተላለፍበት ይህ የባሕር አካል ወደ እስያ እና አውሮፓ አገራት ነዳጅ የሚጓጓዝበት ዋነኛ መስመር ነው።
በፋርስ ባህረ ሰላጤ የሚካሄደው ጦርነት በቀጥታ የዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ቢያሳይም ባለሙያዎች ግን ሌሎችንም የምጣኔ ሀብት ዘርፎችን እንደሚጎዱ ይናገራሉ።
1. የምግብ ዋጋ መናር
በፋርስ ባሕረ ሰላጤ የተቀሰቀሰው ጦርነት በዋናነት የአፈር ማዳበሪያ አምራቾችን ይጎዳል።
ኦማን፣ ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ዋነኛ የናይትሮጅን ማዳበሪያ ላኪ አገራት ናቸው።
ይህን የአፈር ማዳበሪያ ለማምረት በዋናነት በግብዓትነት የሚውለው የተፈጥሮ ጋዝ ሲሆን፣ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ አርሶ አደሮች ግማሽ ያህሉ ይጠቀሙታል።
ምንም እንኳ የቀጣናው የማዳበሪያ አምራቾች ሥራቸውን የቀጠሉ ቢሆንም ዋነኛው የዩሪያ አምራች የሆነው ኳታር ኢነርጂ ባለፈው ሳምንት በኢራን የድሮን እና ሚሳዔል ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ሥራውን አቁሟል።
እነዚህ የአፈር ማዳበሪያ አምራች ፋብሪካዎች ምርታቸውን ቢቀጥሉ እንኳ የሆርሙዝ የባሕር ወሽመጥ በመዘጋቱ የተነሳ የምርት መስተጓጎል በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ መፈጠሩ አይቀርም።
ብሉምበርግ የዓለም አንድ ሦስተኛው የአፈር ማዳበሪያ ምርት በሆርሙዝ ሰርጥ በኩል እንደሚያልፍ ዘግቧል።
እንደ ኦብዘርቫቶሪ ኦፍ ኢኮኖሚክ ኮምፕሌክሲቲ መረጃ ከሆነ ቻይና የዓለም ቀዳሚ የናይትሮጅን ማዳበሪያ ላኪ አገር ናት።
በዚህም የተነሳ የዓለም የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምር ይጠበቃል። ጦርነቱ በጀመረበት በመጀመሪያ ሳምንት ብቻ በአሜሪካ ገበያ የአንድ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ዋጋ ከ516 ዶላር ወደ 613 ዶላር ከፍ ብሏል።
ይህ ደግሞ በተለይ አርሶ አደሮች ሰብላቸውን የሚዘሩበት ወራት እየተቃረበ በመጣበት ወቅት መሆኑ የበለጠ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል።
ተንታኞች ጦርነቱ የሚቀጥል ከሆነ ሸማቾች የዋጋ ጭማሪውን ከአንድ ወር እስከ ሦስት ወር ባሉት ጊዜያት ውስጥ ጫናው በቀጥታ ይሰማቸዋል ሲሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
ይህም ዋጋ ጭማሪ ከማሳየት እስከ የምርት እጥረት መፈጠር ሊሆን አንደሚችል ጨምረው ገለጸዋል።
ይህ ደግሞ በተለይ በደሃ አገራት ረሃብ እንዲከሰት ምክንያት ሊሆን ይችላል ሲሉ ይናገራሉ።
የመንግሥታቱ ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሰጠው መግለጫ "በመካከለኛው ምሥራቅ እየተባባሰ ባለው ግጭት ምክንያት የምግብ እና የነዳጅ ዋጋ በድንገት መጨመር ተያያዥነት ያለው ተፅእኖ ሊፈጥር ይችላል። ይህም በአካባቢው እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ያሉ ተጋላጭ ሕዝቦችን ረሃብ ያባብሳል" ብሏል።

የመድኃኒት አቅርቦት መስተጓጎል
በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በዓለም አቀፍ የመድኃኒት እና ፋርማሲውቲካል ምርቶች አቅርቦት ላይ መስተጓጎልን ይፈጥራል።
ይህ በተለይ የዓለም አቀፉ የፋርማሲውቲካል ሎጀስቲክ መናኽሪያ በሆነችው በዱባይ ላይ በተፈጸመው ጥቃት የተነሳ የሚመጣ ነው።
ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ በዓለማችን እጅግ በመንገደኞች የሚጨናነቁ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ያሏት ሲሆን፣ በ2025 ብቻ በግምት 95 ሚሊዮን መንገደኞችን አስተናግዳለች ተብሎ ይገመታል።
የአውሮፕላን ማረፊያዎቹ በተለይ ቅዝቃዜ የሚፈልጉ የመድኃኒቶች እና ሌሎች የፋርማሲውቲካል ምርቶች ጭነቶችን ያስተናግዳሉ።
አውሮፕላን ማረፊያዎቹ በተለይ ለሕንድ የፋርማሲውቲካል ኩባንያዎች ቁልፍ መዳረሻ ናቸው።
ሕንድ የመድኃኒት አምራቾች የዓለም 60 በመቶ ክትባትን የሚያመርቱ ሲሆን፣ የዓለም ርካሽ መድኃኒት ምርቶች ግዙፍ አቅራቢ ናቸው።
የኤሚሬትስ አየር መንገድ እንዲሁ ከአገሪቱ ስካይፋርማ የተሰኘ የጭነት አገልግሎት የሚሰጥ ክፍል ያለው ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ ቅዝቃዜ የሚፈልጉ የመድኃኒት ምርቶችን ያጓጉዛል።
በመካከለኛው ምሥራቅ በርካታ ጭነቶችን በማስተናገድ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ጀበል አሊ ወደብ በዱባይ ባለቤትነት የተያዘነው።
የጀበል አሊ የወደብ ባለሥልጣን በ60 አገራት ከሚገኙ ከ400 የፋርማሲውቲካል እና የጤና ኩባንያዎች ጋር ይሠራል።
በ2020 50 በመቶ የሚሆነው እና 21.8 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣው የዱባይ ፋርማሲውቲካል እና የጤና መጠበቂያ ምርቶች የተጓጓዙት በዚህ ወደብ በኩል ነው።
የሕንድ ፋርማሲውቲካል ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ፣ አፍሪካ፣ አውሮፓ እና ሌሎች መዳረሻዎች የሚልኳቸው የፋርማሲውቲካል ምርቶች በዚህ ወደብ በኩል የሚያልፉ ናቸው።
ለፋርማሲውቲካል ኩባንያዎች የአየር ትራንስፖርት ወሳኝ ሲሆን በተለይ ማቀዝቀዣ የሚፈልጉ፣ በፍጥነት መድረስ ያለባቸው ምረቶች ይህንን መጓጓዣ ይጠቀማሉ።
በቀጣናው ምንም እንኳ ሌሎች አማራጭ የማጓጓዣ መንገዶች ቢኖሩም አቅማቸው ግን አነስተኛ ነው። በዚህም የተነሳ ተጨማሪ የጉዞ ቀናት፣ እንዲሁም ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቁ ናቸው።
የሕንድ ንግድ ሚኒስቴር የአገሪቱ የፋርማሲውቲካል ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ወደ 200 አገራት አንደሚልኩ አስታውቆ በተለይ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ብራዚል፣ ፈረንሳይ እና ደቡብ አፍሪካ ዋነኛ መዳረሻዎች መሆናቸውን ገልጿል።
የዱባይ አውሮፕላን ማረፊያ እና በስሩ ያሉ ተቋማት ለመድኃኒቶች ማከማቻ ማዕከል ያለው በመሆኑ ለዓለም የፋርማሲውቲካል ገበያ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
ማዕድናት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ጦርነት ከፍተኛ ተጽእኖ ከሚደርስባቸው የማዕድን ዘርፎች መካከል ሰልፈር አንዱ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ለተለያዩ ኢንዱስትሪ ምርቶች በግብዓትነት የሚያገለግሉ እንደ አልሙኒየም ያሉ ማዕድናት መስተጓጎል ይገጥማቸዋል ተብሎ ተሰግቷል።
ሳዑዲ አረቢያ፣ ዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ፣ ኳታር፣ ኩዌት እና ኢራን ከነዳጅ እና ከጋዝ ተረፈ ምርት የሚመረተው ሰልፈር ዋነኛ አምራች እና ላኪ አገራት ናቸው።
እንደ ዩኤስ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ መረጃ ከሆነ 24 በመቶ የሚሆነው የዓለም የሰልፈር ምርት የሚመጣው ከመካከለኛው ምሥራቅ ነው።
አብዛኛው ይህ ምርት ለአፈር ማዳበሪያ ቢያገለግለም ማዕድናትን ለማውጣትም ጥቅም ላይ ይውላል።
በተለይ ደግሞ እንደ መዳብ እና ኒኬል ያሉ ማዕድናትን ለማውጣት ሰልፈር አስፈላጊ ነው።
ሰልፈር ለተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ጥቅም ላይ የሚውለውን ሰልፈሪክ አሲድ ለማምረት በግብዓትነት ያገለግላል።
እነዚህ ማዕድናት ደግሞ ስማርት ስልኮች፣ ተሽከርካሪዎች፣ ኮምፒውተሮች፣ በከፊል ኤሌትሪክ አስተላላፊ የሆኑ ገመዶችን፣ ባትሪዎችን ለማምረት ጥቅም ላይ ይውላሉ።
በዚህ ዘርፍ የጦርነቱ ዳፋ መሰማት የጀመረው ወዲያውኑ ነው።
በጦርነቱ የመጀመሪያ ሳምንት ብቻ በኢንዶኔዢያ የሚገኙ የኒኬል አምራቾች በባሕረ ሰላጤው አገራት የግብዓት አቅርቦት እጥረት ስለገጠማቸው የምርት መቋረጥ እንደሚኖር ተናግረዋል።
እነዚህ የዓለም 50 በመቶ ኒኬልን የሚያመርቱ ኩባንያዎች የሚጠቀሙትን 75 በመቶ ሰልፈር የሚያገኙት ከመካከለኛው ምሥራቅ ነው።
ሮይተርስ የዜና ወኪል በአፍሪካ የሚገኙ የመዳብ አምራቾች ተመሳሳይ ችግር ገጥሟቸዋል ሲል ዘግቧል።















