ቻድ ውስጥ በሁለት ግለሰቦች መካከል የተከሰተን ፀብ ተከትሎ 100 ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Thinkstock
በሰሜናዊ ቻድ ውስጥ ባሉ ባህላዊ የወርቅ ማዕድን አውጪዎች መካከል በተከሰተ ግጭት አንድ መቶ የሚሆኑት ሲሞቱ በርካቶች መቁሰላቸውን የአገሪቱ መንግሥት አስታወቀ።
ከቀናት በፊት በሁለት ግለሰቦች መካከል የተከሰተ ፀብ ተስፋፍቶ ነው 100 ለሚደርሱ ሰዎች ሞትና ለ40 ሰዎች ደግሞ በተለያየ ደረጃ የአካል ጉዳት ምክንያት ሆኗል።
በወርቅ ማዕድን ማውጫው አካባቢ በግለሰቦቹ መካከል የተከሰተው ፀብ ከቁጥጥር ወጥቶ ለዚህ ሁሉ ሞትና ጉዳት ምክንያት መሆኑን የቻድ የመከላከያ ሚኒስትር ዳውድ ያያ ብራሂም ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።
ይህ ከባድ ግጭት የተከሰተበት ቻድን ከሊቢያ ጋር የሚያዋስነው ተራራማው ኩቲ ቡጉዲ የተባለው አካባቢ ባለው የወርቅ ማዕድን የተነሳ ከመላዋ ቻድና ከጎረቤት አገራት ባህላዊ ወርቅ አውጪዎች ይሰባሰቡበታል።
ይህ ደም አፋሳሽ ግጭት የተከሰተው ባለፈው ሳምንት ቢሆንም ስፍራው ከዋና ከተማዋ ርቆ በድንበር አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ ዜናው የተሰማው አሁን ዘግይቶ ነው።
ስለግጭቱና ስለደረሰው ጉዳት መጀመሪያ በተሰማበት ጊዜ የቻድ መንግሥት ከዋና ከተማዋ ኒጃሚና ሰሜን ምሥራቅ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው አካባቢ አንድ ወታደራዊ ቡድን መላኩ ተሰምቷል።
ወደ አካባቢው የተላከው ግዙፍ ወታደራዊ ቡድን ከደረሰ በኋላ መረጋጋት መፈጠሩን የመከላከያ ሚኒስትሩ ለዜና ወኪሉ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ጨምረውም አንድ መቶ ያህል ሰዎች የሞቱበት ግጭት የተከሰተው የቻድ አጎራባች ከሆኑት ሞሪታኒያ እና ሊቢያ በመጡ የማዕድን አውጪዎች መካከል ነው።
ደም አፋሳሽ ግጭቱን ተከትሎ ኩሪ ቡጉዲ በተባለው አካባቢ የሚካሄድ ሁሉም አይነት የወርቅ ማዕድን ማውጣት ሥራ መቋረጡም ተገልጿል።












