የሱዳን ቁልፍ ከተማ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እጅ ከወደቀች በኋላ የጅምላ ግድያ ተፈጽሟል የሚል ፍርሃት ነግሷል

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሱዳን ቁልፍ የሆነችው ከተማ ኤል ፋሸር በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ የጅምላ ግድያ ይጨምራል የሚል ፍርሃት ተቀስቅሷል።
የሱዳን መከላከያ አዛዥ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ሰኞ ምሽት ባደረጉት ንግግር ጦራቸው "ስልታዊ ውድመት እና የንፁኃንን መገደል" ተከትሎ እንዲወጣ ማዘዛቸውን ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ "የጅምላ ግድያ" ስለመኖሩ ተጨባጭ መረጃዎች አሉ ያለ ሲሆን፣ የል ዩኒቨርስቲ በበኩሉ የሳተላይት ምስሎችን በመጥቀስ "በጅምላ የተገደሉ ሰዎች አስከሬን ክምር" ይታያል ብሏል።
የፈጥኖ ደራሽ ጦሩ ሰላማዊ ዜጎችን እና አረብ ያልሆኑ ቡድኖች ላይ ግድያዎች መፈጸሙን የሚገልጽ ማስረጃ በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ቢቀርብም አስተባብሏል።
በዳርፉር ክልል የምትገኘው ኤል ፋሸር በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እጅ መውደቋ በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑ ተነግሯል።
እአአ በ2023 የተጀመረው የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ለሺህዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሲሆን 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ከቀያቸው አፈናቅሏል።
የፈጥኖ ደራሹ ተዋጊዎች ኤል ፋሸርን ለ18 ወራት ያህል በከበባ ውስጥ አቆይተው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች እንዳይንቀሳቀሱ በማድረግ የረሃብ ቀውስ እንዲከሰት አድርገዋል።
የጠል ዩኒቨርስቲ ሂውመኒቴሪያን ሪሰርች ላብ ለቢቢሲ እንደተናገረው ከተማዋ በአማፂያኑ እጅ ከገባችበት ጊዜ አንስቶ የሳተላይት ምስሎች "በጅምላ የተገደሉ ሰዎች ክምር ወይም ከተማዋን ዙሪያ ከታጠረው አጥር አምልጠው ለመውጣት ሲሉ በልሞ ተኳሾች የተመቱ ሰዎች አስከሬን" ያሳያል ብሏል።
የምርምር ቡድኑ ዳይሬክተር በኤክስ ገጻቸው ላይ በሳተላይት ምስሉ ላይ "ደም እንደ ውሃ ሲፈስ" ማየታቸው ድንጋጤን እንደፈጠረባቸው ጽፈዋል።
ናትናኤል ሬይመንድ "ግድያው የሚፈጸምበት ፍጥነት፣ መጠን እና ጭካኔ ባለፉት 25 ዓመታት ሥራዬን ስሰራ ካየሁት ሁሉ የከፋው ነው" ብለዋል።
በተመሳሳይም በሱዳን የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ቡድን "በጅምላ ግድያ" እንዲሁም ለማምለጥ በሚሞክሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች፣ ደፈራዎች እና ቤት ለቤት አሰሳዎች "መረበሹን" አስታውቋል።
ከሱዳን ጦር ጎን የተሰለፉት የዳርፉር ታጣቂ ቡድኖች ጥምረት፣ ከተማዋ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እጅ ከወደቀች በኋላ 2000 ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
ይህ መረጃ ከገለልተኛ ወገን አልተጣራም።
ከኤል ፋሸር አምልጦ የወጣ አንድ ግለሰብ ለቢቢሲ በከተማዋ የቀሩ ቤተሰቦቹን ማግኘት ባለመቻሉ ፍርሃት እና ተስፋ መቁረጥ እየተሰማው መሆኑን ተናግሯል።
ሌላ ግለሰብ ደግሞ በርካታ የቤተሰቦቹ አባላት "መገደላቸውን" ገልጾ፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አካባቢውን ከተቆጣጠረ በኋላ የስልክ መስመሮች በመቋረጣቸው በሕይወት የቀሩ የቤተሰብ አባላቱን ማግኘት አለመቻሉን ገልጿል።
"አንድ ቦታ ሰብሰብው ገደሏቸው። አሁን በሕይወት የተረፉት በምን ሁኔታ ውስጥ እንደሆኑ ማወቅ አልቻልንም" ሲል ተናግሯል።
ማክሰኞ ዕለት የአውሮፓ ኅብረት "ሁሉም ተዋጊ ኃይሎች ከግጭት እንዲታቀቡ" ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ የአፍሪካ ኅብረት ደግሞ "ተፈጽመዋል የተባሉ የጦር ወንጀሎች እና ሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ብሔር ተኮር ግድያዎችን" አውግዟል።
የዓለም ጤና ድርጅት በከተማዋ አገልግሎት ብቸኛ ሆስፒታል እሁድ ዕለት ጥቃት እንደደረሰበት አስታውቋል።
በጥቃቱ አንዲት ነርስ መገደሏን ጨምሮ ገልጿል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉታሬስ ከተማዋ ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ "ከፍተኛ ስፋት" እንደገባቸው ገልጸው የተጠቀሱ "የዓለም አቀፍ ሰብዓዎ ሕግ ጥሰቶችን" አውግዘዋል።
ሰኞ ዕለት የሱዳን ጦር ከኤል ፋሸር መውጣቱን ካረጋገጡ በኋላ ጄኔራል ቡርሃን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ግፍ ለማስቆም የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ምንም አይነት እርምጃ አለመውሰዱን አውግዘው "ይህች ምድር እስክትጸዳ ድረስ" ለመዋጋት ቃል ገብተዋል።
"በየጊዜው ሁኔታዎችን መቀየር እንችላለን፤ እናም በእነዚህ ከዳተኞች የረከሰውን መሬት ሁሉ ወደ አገሪቱ ግዛት እንመልሰዋለን" ብለዋል።















