'ፊታችን የተገደሉ ሰዎችን አይተናል' - ከሱዳን አማፂያን ከበባ የተረፉ ሰዎች

ኢዘልዲን ሃሰን ሙሳ

ለብሶት የነበረውን ልብስ ብቻ ይዞ ለማምለጥ የቻለው ኢዘልዲን ሃሰን ሙሳ፤ የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) በዳርፉር ክልል የሚገኘውን የኤል-ፋሸር ከተማን ከተቆጣጠሩ በኋላ የፈጸሙትን ጭካኔ ገልጿል።

በርካታ ለመሸሽ የሞከሩ ሰዎችን አሰቃይተው ገድለዋል ብሏል።

አሁን ታዊላ ከተማ ደርሷል። ኢዘልዲን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት "አስፈሪ" ብሎ ከገለጸው ጥቃት ካመለጡ በኋላ አንጻራዊ ደህንነት ወዳለበት ስፍራ ከደረሱት በርካታ ሺህ ሰዎች አንዱ ነው።

ረቡዕ ዕለት የአርኤስኤፍ መሪ ጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ በኤል-ፋሸር "ጥሰቶች" መፈጸማቸውን አምነው ምርመራ እንደሚደረግባቸው ተናግረዋል።

ከአንድ ቀን በኋላ ደግሞ አንድ ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ባለስልጣን አርኤስኤፍ አንዳንድ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ማስታወቁን ተናግረዋል።

ከኤል-ፋሸር 80 ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምትገኘው ታዊላ የአርኤስኤፍ ተዋጊዎችን ለማምለጥ ዕድለኛ የሆኑ ሰዎች ከሚሸሹባቸው በርካታ ቦታዎች አንዱ ነው።

"ከአራት ቀናት በፊት ኤል-ፋሸርን ለቅቀን ወጥተናል። በመንገድ ላይ ያጋጠመን መከራ የማይታሰብ ነበር" ይላል ኢዘልዲን።

"በቡድን ተከፋፍለን ተደብድበናል። እጅግ በጣም ጨካኝ ነበሩ። ሰዎች ፊት ለፊታችን ሲገደሉ አይተናል። ሰዎች ሲደበደቡም አይተናል። በጣም አስፈሪ ነበር።"

"እኔም ጭንቅላቴ፣ ጀርባዬ እና እግሬ ላይ ተመትቻለሁ። በዱላ ደበደቡኝ። ሁላችንንም ሊገድሉን ፈለጉ። ነገር ግን ዕድሉ ሲፈጠር ሮጥን፤ ከፊት ለፊታችን የነበሩት ሌሎች ታሰሩ።"

ኢዘልዲን በአንድ ሕንፃ ውስጥ ተጠልለው በሌሊት እየተንቀሳቀሱ እና አንዳንድ ጊዜም ለመደበቅ ሲሉ መሬት ለመሬት እየተሳቡ ከስደተኞች ጋር እንደተቀላቀሉ ይናገራል።

"ንብረቶቻችን ተሰርቀዋል። ስልክ፣ ልብስ ሁሉም ነገር። ጫማዬ እንኳን ተሰርቋል። የተረፈ ነገር አልነበረም።"

"ለሦስት ቀናት ምግብ ሳንበላ ስንጓዝ ቆይተናል። በፈጣሪ ምሕረት አልፈናል።"

በታዊላ የሚገኙ ሰዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጉዞውን የሚያደርጉ በተለይም ወንዶች በተለይ በአርኤስኤፍ በቁጥጥር ስር የመዋል ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም ተዋጊ ወታደር እንደሆነ የሚጠረጠርን ማንኛውንም ሰው ዒላማ ያደርጋሉ።

እሑድ ዕለት ኤል-ፋሸር በአርኤስኤፍ ቁጥጥር ስር መዋሏን ተከትሎ ወደ ታውላ እንደደረሱ ከሚታሰቡት 5,000 ሰዎች አንዱ ኢዘልዲን ነው።

ብዙዎች ለሦስት ወይም ለአራት ቀናት በእግር ተጉዘው ከጥቃት ለመሸሽ ችለዋል።

በታዊላ የሚኖር እና ለቢቢሲ የሚሠራ ፍሪላንስ ጋዜጠኛ ጉዞው ካደረጉት መካከል አንዳንዶቹን ጠይቋል።

ስደተኞች

ከኢዘልዲን አቅራቢያ በበርካታ የሰውነት ክፍሉ ላይ በፋሻ የታሰረለት አህመድ ኢስማኤል ኢብራሂም ተቀምጧል።

ዓይኑ በጥይት ተመትቶ እንደነበር ተናግሯል። እሑድ ዕለት በሆስፒታል ሕክምና ከተደረገለት በኋላ ከተማዋን ለቋል።

እሱ እና ሌሎች ስድስት ሰዎች በአርኤስኤፍ ተዋጊዎች እንዲቆሙ መደረጋቸውን ተናግሯል።

"አራቱን ፊት ለፊታችን ገደሏቸው። ደበደቧቸውና ገደሏቸው" ከማለት ባለፈ ሦስት ጊዜ በጥይት እንደተመታ አክሏል።

ተዋጊዎቹ በሕይወት የቀሩትን የሦስቱን ስልኮች ለማየት እንዴት እንደጠየቁ እና መልዕክቶቻቸውን ለመመልከት መቻላቸውን አህመድ ይገልጻል።

በመጨረሻም አንደኛው ተዋጊ "እሺ፣ ተነሱ ሂዱ" እንዳላቸው ወደ ፍርስራሹ ሸሹ።

"ወንድሞቼ ብቻዬን አልተውኝም" ሲል አክሎ ተናግሯል።

"ለ10 ደቂቃ ያህል ተጓዝን፣ ከዚያም ለ10 ደቂቃ አረፍን። በኋላም አሁን ሠላም እስክናገኘንበት ድረስ ጉዞ ቀጠልን።"

አህመድ ኢስማኤል ኢብራሂም
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በሜዲሲን ሳንስ ፍሮንቲየርስ (ኤምኤስኤፍ) በሚተዳደረው ክሊኒክ ድንኳን ውስጥ ደግሞ የሱዳን ጦር ወታደር የሆነው ባለቤቷ ከተገደለ በኋላ ከከተማው ለመሸሽ መወሰኗን ዩስራ ኢብራሂም መሐመድ ገልጻለች።

"ባለቤቴ በጦሩ ውስጥ ነበር። ወደ ቤት ሲመለስ ነበር በጥቃቶቹ ወቅት የተገደለው" ትላለች።

"በትዕግስት ቆየን። ግጭቶቹ እና ጥቃቶቹ ቀጠሉ። በኋላም ለማምለጥ ችለናል።"

"ከሦስት ቀናት በፊት ወጣን። ከመድፍ መተኮሻ አካባቢዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች እየተንቀሳቀስን ነበር። የሚመሩን ሰዎች ምን እየተከሰተ እንዳለ አያውቁም ነበር።"

"አንድ ሰው ከተቃወመ ይደበደባል ወይም ይዘረፋል። ያለህን ሁሉ ይወስዱ ነበር። ሰዎችን ሊገደሉ ጭምር ይችላሉ። በጎዳናዎች ላይ የሞቱ ሰዎችን አስከሬኖችን አይቻለሁ።"

አልፋዲል ዱካን በኤምኤስኤፍ ክሊኒክ ውስጥ ይሠራል።

እሱ እና ባልደረቦቹ ድንገተኛ ሕክምና ሲሰጡ ቆይተዋል። ከመጡት መካከል 500 የሚሆኑት አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ናቸው ብሏል።

"አዲስ ከመጡት አብዛኛዎቹ አዛውንቶች፣ ሴቶች ወይም ልጆች ናቸው" ብሏል ሐኪሙ።

"የቆሰሉት እየተሰቃዩ ነው። አንዳንዶቹም ቀድሞውንም አካላቸው የተቆረጠ ነው።"

"ስለዚህ በጣም እየተሰቃዩ ነው። የተወሰነ ድጋፍ እና የሕክምና እንክብካቤ ለመስጠት እየሞከርን ነው።"

በዚህ ሳምንት ወደ ታውላ የደረሱት ቀደም ሲል በኤል-ፋሸር ከነበሩት ግጭቶች ሸሽተው የነበሩት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ተቀላቅለዋል።

እሑድ ዕለት በአርኤስኤፍ ኃይሎች ከመያዟ በፊት ከተማው ለ18 ወራት ተከብባ ነበር።

ከተማዋን ለመያዝ በተደረገ ውጊያ ለቀናት የአየር ጥቃትን ጨምሮ በርካታ ድብደባ ተፈጽሟል።

እናም በአርኤስኤፍ የአቅርቦቶች እና የእርዳታዎች እገዳ ምክንያት ከባድ የረሃብ ቀውስ ውስጥ ገብተዋል።

በሚያዝያ ወር አርኤስኤፍ በከተማው አቅራቢያ የሚገኘውን የዘምዘም ሰፈራ ጣቢያን ሲቆጣጠር በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ሰፈራ ጣብያው ከሌሎች ቦታዎች ለመሸሽ የተገደዱ ሰዎች ከሚኖሩባቸው ቦታዎች አንዱ ነበር።

ዩስራ ኢብራሂም መሐመድ

አንዳንድ ባለሙያዎች እንደ ታዊላ ባሉ ቦታዎች የሚደርሱ ቁጥሮች በአንጻራዊ ሁኔታ ዝቅተኛው መሆናቸው ስጋት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

"ይህ ለእኛ የጭንቅ ጊዜ ነው" ብላለች በጎረቤት ቻድ ከሚገኙ ስደተኞች ጋር የሚሠራው ሶሊዳሪቴስ ኢንተርናሽናል የተሰኘው የእርዳታ ኤጀንሲ ባልደረባዋ ካሮላይን ቡቮር።

"ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ወደ አምስት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ደርሰዋል። በከተማው ውስጥ ሩብ ሚሊዮን የሚያህሉ ሰዎች እንዳሉ እናምናለን። ከዚህ አንጻር ያን ያህል ብዙ አይደሉም" ትላለች።

"የደረሱት ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ እናያለን። የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አለባቸው፤ በጣም ተጎድተዋል ወይም ታመዋል ወይም ደግሞ ቆስለዋል። በከተማው ውስጥም ሆነ በመንገድ ላይ ባዩት ነገር በግልጽ ተጎድተዋል።"

"በአካላዊ ሁኔታቸው ወይም በመንገድ ላይ ባለው አለመረጋጋት ምክንያት ብዙ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በታዊላ እና በኤል-ፋሸር መካከል በተለያዩ ቦታዎች መፈናፈኛ አጥተው ወደፊት መሄድ እንዳልቻሉ እናምናለን።"

ለኢዘልዲን ደህንነት ማግኘቱ የሚሰጠውን እፎይታ ያህል አሁንም በጉዞው ላይ ከኋላ ያሉት ሰዎች ስለሚሰማቸው ፍርሃት ያስባል።

"መልዕክቴ መንገዶች ለዜጎች ደህንነት ወይም ለሚላኩ የሰብአዊ እርዳታዎች ሲባል መጠበቅ አለባቸው" ሲል ይማጸናል።

"ሰዎች በአስጊ ሁኔታ ላይ ናቸው መንቀሳቀስ፣ መናገር ወይም እርዳታ መጠየቅ አይችሉም።"

"ብዙዎች እየጠፉ እና እየተሰቃዩ ስለሆነ እርዳታ ሊደርስላቸው ይገባል" ብሏል