የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በኤል-ፋሸር በሚገኝ ሆስፒታል 460 ሰዎችን መግደሉን የዓለም የጤና ድርጅት አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images
ከሱዳን ጦር ጋር ውጊያ ላይ ያለው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል፤ ከቀናት በፊት በተቆጣጠራት ኤል-ፋሸር ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹኃን ሰዎችን መግደሉን መረጃ እንደደረሰው የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የጤና ድርጅት አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም የሚመሩት ተቋም፤ ሆስፒታል ውስጥ 460 ሰዎች መገደላቸውን በሚያመለክቱት መረጃዎች "በእጅጉ መደንገጡን" ተናግረዋል።
ከዓለም የጤና ድርጅት አስቀድሞ ግድያው መፈጸሙን ይፋ ያደረገው፤ 'ሱዳን ዶክተርስ ኔትዎርክ' የተባለው የሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ነው። ማኅበሩ፤ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች ማክሰኞ ዕለት "ታካሚዎችን፣ አስታማሚዎቻቸው እና ሌሎችንም ጨምሮ በሳውዲ ሆስፒታል ውስጥ ያገኟቸውን ሰዎች በሙሉ ያለ ርሕራሄ ገድለዋል" ብሏል።
'ሱዳን ዶክተርስ ኔትዎርክ' በዚህ ጥቃት ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ አልጠቀሰም። ይሁን እንጂ በከተማው የሚገኛው የጤና ተቋም "ወደ የሰዎች ቄራነት ተቀይሯል" ሲል ሁኔታውን ገልጾታል።
በተጨማሪም ማኅበሩ፤ አራት ዶክተሮች፣ ፍርማሲስት እና ነርስ የሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች ታግተው መወሰዳቸውን አስታውቋል። የሕክምና ባለሙያዎቹን ለማስለቀቅ 150 ሺህ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ እንዲከፈል መጠየቁንም አክሏል።
የማኅበረሰብ አንቂዎች ስብስብ የሆነው 'ኤል-ፋሸር ሬዚስታንስ ኮሚቴ' ም በተመሳሳይ ማክሰኞ ዕለት በሳውዲ ሆስፒታል ጥቃት መፈጸሙን አስታውቋል። ከጥቃቱ በኋላ "አስፈሪ ዝምታ" እንደነበረም ገልጿል።
እሑድ ዕለት በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቁጥጥር ሥር የገባው ኤል-ፋሸር ከተማ በዳርፉር ክልል የሱዳን ጦር ጠንካራ ይዞታ ነበር። ከተማው በተዋጊዎቹ እጅ ከመግባቱ በፊት ረሃብ ያስከተለ የ18 ወራት ከበባ ውስጥ ቆይቷል፤ ከባድ ድብደባም ተፈጥሞበታል።
በሚያዝያ 2016 ዓ. ም. የሱዳኑ ጦርነት ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና አጋሩ የሆነው የዳርፉር የአረብ ሚሊሻ አረብ ያልሆኑ ብሔሮችን ዒላማ እያደረገ ጥቃት የይፈጽማል የሚሉ ክሶች ቀርበውበታል። ኃይሉ ግን እነዚህን ውንጀላዎች ውድቅ አድርጓል።
ኤል-ፋሸር በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እጅ መግባቱን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት፣ ማኅበረሰብ አንቂዎች እና የተራድኦ ድርጅቶች ከከተማው መውጫ ስላጡ 250 ሺህ ገደማ ሰዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል። ከእነዚህ ነዋሪዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ አረብ ካልሆኑ ማኅበረሰቦች የተገኙ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images
በከተማው የግንኙነት መስመሮች በሙሉ በመቋረጣቸው የተፈጠረውን ነገር ማረጋገጥ አልተቻለም።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለቀቁ እና 'ቢቢሲ ቬሪፋይ' የመረመራቸው አዲስ ቪዲዮዎች፤ ባለፉት ጥቂት ቀናት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች ያልታጠቁ ሰዎችን ሲገድሉ እንደነበር አሳይተዋል።
የእርዳታ ድርጅቶች በኤል-ፋሸር በአካባቢው የተፈጸመው ጥፋት መጠን ገና መውጣት ጀመረ እንጂ ሙሉ በሙሉ ይፋ አልሆነም የሚል እምነት አላቸው።
ከኤል-ፋሸር በስተምዕራብ 60 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው ታዊላ ከተማ ለመድረስ የሚደረገውን አደገኛ ጉዞ አልፈው የመጡ የተወሰኑ ሰዎች፤ ያጋጠማቸውን ከፍተኛ ጥቃት ገልጸዋል።
ቅዳሜ ዕለት ሲፈጸም በነበረው የከባድ መሣሪያ ድብደባ ምክንያት ከአካባቢው መውጣታቸውን የሚናገር አንድ ነዋሪ፤ መንገድ ላይ ያገኟቸው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች "እየደበደቧቸው እና እየሰደቧቸው ቪድዮ ሲቀርጹ" እንደነበር አስረድቷል። በርካታ ሰዎች ተይዘው ገንዘብ እንደተጠየቀባቸውም አክሏል።
"ከተወሰዱት መካከል የተወሰኑት በኋላ ላይ ተገድለዋል። ጉዞ ላይ እያለን ብዙ ሰዎች ታስረዋል። በረሃብ እና በውሃ ጥም እጅጉን ተሰቃይተናል" ሲል ያለፈበትን ገልጿል።















