የሴኔጋሉ የተቃዋሚ መሪ በርሃብ አድማ ክፉኛ ተጎድቶ ጽኑ ሕሙማን ክፍል መግባቱ ተነገረ

Ousmene Sonko

የፎቶው ባለመብት, AFP

የሴኔጋሉ ታዋቂ የተቃዋሚ ፖለቲከኛ ኦስማኔ ሶንኮ በእስር ቤት እያለ ባደረገው የረሃብ አድማ ክፉኛ በመጎዳቱ በሆስፒታል የጽኑ ሕሙማን መከታተያ ክፍል መግባቱ ተነገረ።

የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ ሶንኮ መታሰሩን በመቃወም ባለፉት ሁለት ሳምንታት ለረሃብ አድማ በማድረጉ ነው የጤናው ሁኔታ አሽቆልቁሎ ሆስፒታል የገባው።

በሴኔጋል ባለሥልጣናት እንዳይንቀሳቀስ የታገደው ፓስቴፍ ፓርቲ አባል የሆኑት እና የሶንኮ የትግል አጋር ኦሴየኑ ሊ “ሶንኮ ረቡዕ ሌሊት ነው ሕመም ያጋጠመው” ብለዋል።

ቢቢሲ ባደረገው ማጣራት ሶንኮ ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍል መወሰዱን በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር ውስጥ የሚገኝ የሆስፒታል ምንጭ አረጋግጧል።

የፓስቴፍ ፓርቲ፣ ሶንኮ ለገጠመው የጤና እክል የመንግሥት ባለሥልጣናት ኃላፊነቱን ይወስዳሉ ሲል ከሷል።

ሶንኮ በመንግሥት ላይ አመጽ በመቀስቀስ፣ በማሴር እና በሌሎች ወንጀሎች ተከሶ ነው ለእስራት የተዳረገው። ነገር ግን ፓርቲው የመንግሥት ባለሥልጣናትን ቢያስጠነቅቅም ከባለሥልጣናቱ ዘንድ የተሰጠ ምንም አይነት ምላሽ የለም።

ሶንኮ በሚቀጥለው ዓመት የካቲት ላይ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር ዕቅድ የነበረው ሲሆን፣ ሥነ ምግባራዊ ሙስና ፈጽሟል በሚል በመንግሥት ምርመራ ስለተጀመረበት ከባለሥልጣናት ጋር ውዝግብ ውስጥ ነው የቆየው።

የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጥምረት ፕሬዝዳንት የሆኑት የዊ አስካን ዊ “እኛ ከሴኔጋል መንግሥት ብዙ ነገር አንጠይቅም፣ የምንጠይቀው የኦስማኔ ሶንኮን መብት እና ነጻነት እንዲያከብር ብቻ ነው” ብለዋል።

ባለፈው ሰኔ ወር ሶንኮ በሌለበት የሁለት ወር እስራት የተፈረደበት ሲሆን፣ የተላለፈበትን የእስር ቅጣትም “ፖለቲካዊ ነው” በማለት አጣጥሎት ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ደጋፊዎቹ ዋና ከተማዋን ጨምሮ በአገሪቱ ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደው፣ በተፈጠረው ግርግር ቢያንስ 24 ሰዎች መሞታቸውን አምኒስት ኢንተርናሽናል ገልጿል።

በሐምሌ ወር ደግሞ ወደ እስር ቤት ተወስዶ አመጽ በመቀስቀስ እና መንግሥትን በኃይል ለመጣል በማሴር የሚል ክስ ባለፈው ሳምንት ተመስርቶበታል።

የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ ለክስ እና ለእስር የተዳረገው በቀጣዩ ምርጫ ተገዳዳሪ በመሆን ለገዢው ፓርቲ ስጋት እንዳይሆን ለማድረግ ነው ሲሉ ተቃዋሚዎች ይከሳሉ።

ይህንን ቀውስ ተከትሎ ሴኔጋል ባለፉት ወራት መረጋጋት ርቋት የቆየ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳልም ሕግ እንዲከበር ሲጠይቁ ነበር።