አፍሪካውያን ሕጻናትን የሚያዋርድ ዘረኛ ቪዲዮዎችን የቀረጸው ቻይናዊ በቁጥጥር ሥር ዋለ

በዘረኝነት እና በሕጻናት ጉልበት ብዝበዛ ላይ ቢቢሲ አፍሪካ አይ የሰራውን የምርመራ ዘገባ ተከትሎ በማላዊ ሲፈለግ የነበረው ቻይናዊ የፊልም ባለሙያ በቁጥጥር ሥር ዋለ።
ሉ ኬ የተባለው ግለሰብ አፍሪካውያን ሕጻናትን በሚያዋርድ ሁኔታ በቀረጻቸው ቪዲዮዎች በቢቢሲ አፍሪካ አይ የምርመራ ዘገባ ሲጋለጥ ነዋሪነቱ በማላዊ ነበር።
በምርመራ ዘገባው እንደተጋለጠው፣ ቻይናዊው የተወሰኑት ዘረኛ ይዘት ያላቸውና ለግል የተሰናዱ የሰላምታ ቪዲዮዎችን ሲቀርጽ በአካባቢው ያሉ ክፉ ደጉን የማይለዩ ሕጻናትን ተጠቅሟል።
እነዚህ ቪዲዮዎች በቻይና የማኅበራዊ ሚዲያ እና የኢንተርኔት መድረኮች ላይ እስከ 70 ዶላር ድረስ ሊሸጡ የሚችሉ ናቸው።
ይሁን እንጂ ቻይናዊው እነዚህን አጸያፊ ቪዲዮዎች አልሰራሁም ብሏል። ቪዲዮዎቹን የሰራውም የቻይናን ባህል ለማስፋፋት በማሰብ እንደሆነ ተናግሯል።
ሆኖም ቢቢሲ በተመለከተው አንደኛው ቪዲዮ ላይ ታዳጊ ሕጻናቱ በቡድን ሆነው የቻይና ቋንቋ በሆነው ማንዳሪን“ እኔ ጥቁር ጭራቅ ነኝ! የአዕምሮ ምጥቀቴ (አይ ኪው) ዝቅተኛ ነው!” እያሉ እንዲዘምሩ ተደርገዋል። ሕጻናቱ ስለሚሉት ነገር ግንዛቤው አልነበራቸውም።
ቪዲዮም በአፍሪካውያን ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።
ሉ ኬ በድብቅ በሚስጢራዊ ጋዜጠኛ ሲጠየቅ ቪዲዮዎቹን ሊገዙት እንደሚችሉ አምኖ የነበረ ሲሆን ወዲያውኑ ግን ቪዲዮዎቹን መስራቱን ክዷል።
ባለፈው ሳምንት የማላዊ ፖሊስ ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ምርመራ የከፈተ ሲሆን ቻይናዊውን የፊልም ባለሙያ ግን ማግኘት አልቻለም ነበር።
የአገሪቷ ኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ፓስኳሊይ ዙሉ፣ ሉ ኬ በጎረቤት አገር ዛምቢያ ምሥራቃዊ ከተማ ቺፓታ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አረጋግጠዋል።
ቃል አቀባዩ እንዳሉት ባለሥልጣናት ምርመራቸውን እንዲቀጥሉ ሁለቱ አገራት የቻይና ዜግነት ያለው ይህ ግለሰ ለማላዊ ተላልፎ እንዲሰጥ እየተነጋገሩ ይገኛሉ።
ባለፈው ሳምንት አንድ ከፍተኛ የቻይና ዲፕሎማት ዉ ፔንግ በጉዳዩ ላይ ከማላዊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር መወያየታቸውን ተናግረዋል።
ዲፕሎማቱ አገራቸው እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ትቃወማለች ብለዋል።
“ ቻይና ባለፉት ዓመታት በእንዲህ ኣይነት መስመር ያለፉ ሕገ ወጥ ድርጊቶች ላይ እርምጃ ስትወስድ ቆይታለች” ሲሉም በትዊተር ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።
“ወደፊትም እንደዚህ ዓይነት የዘር መድልዎን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ለማስቆም መስራታችንን እንቀጥላለን” ሲሉም ዲፕሎማቱ አክለዋል።












