ትምኒት ገብሩ፡ "ጉግልም ሆነ ሌሎች ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እንደ ተቋም ዘረኞች ናቸው"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰው ሰራሽ ልህቀት ዘርፍ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆነቸው ትምኒት ገብሩ (ዶ/ር) "ጉግልም ሆነ ሌሎች ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እንደ ተቋም ዘረኞች ናቸው" አለች።
ትምኒት ይህ የሰው ጉለበትን በጊዜ ሂደት ይተካል ተብሎ የሚጠበቀው የሰው ሰራሽ ልህቀት ‹ጾተኛና ዘረኛ› እየሆነ ነው ትላለች።
ተመራማሪዋ ትምኒት ባለፈው ሳምንት ከጉግል ኩባንያ ከተሰናበተች በኋላ አነጋጋሪነቷ እንደቀጠለ ነው።
ትምኒት የሰው ሰራሽ ልህቀት ስነ ምግባር ላይ ጥናትና ምርምር ካደረገች በኋላ በይዘት ላይ በተፈጠረ አለመግባባት ከጉጉል ጋር እስከ ወዲያኛው ተለያይታለች።
ትምኒትና አጋሮቿ ለርሷ ከጉጉል መለያየት ዋናው ምክንያት ተቋማዊ ዘረኝነት በመንገሱ ነው ብለው ያምናሉ።
ጉግል በበኩሉ ትምኒት ትሳተፍበት የነበረው ጥናት ወሳኝ ርእሰ ጉዳዮችን አላካተተም ይላል።
ትምኒት ከጉግል ጋር ባለፈው ሳምንት የገባችበትን እሰጣገባ ተከትሎ በማይክሮሶፍት፣ አፕል፣ ፌስቡክ፣ አማዞንና ኔትፍሊክስ የሚሰሩ 6 ሺ ሰዎች የፈረሙበት ግልጽ የቅሬታ ደብዳቤ ለጉጉል ኩባንያ ደርሶታል።
ደብዳቤው በዋናነት እነ ትምኒት ይሰሩት የነበረው የጥናት ወረቀት ምን ጉድለት እንደነበረበት ጉጉል ይፋ እንዲያደርግ የሚጠይቅ ነው።
የጉግል ኩባንያ አለቃ ሱንዳር ፒቻይ እውቅ ጥቁር ሴት ሳይንቲስት ትምኒት በኩባንያቸው ቅሬታ ገብቷት ለመልቀቋ ኃላፊትን መውሰድ አለብን ብለዋል።
እሷ የለቀቀችበትን ሁኔታም እንደሚያጣሩ ገልጸው ሆኖም ግን በይፋ ትምኒትን ይቅርታ ከመጠየቅ ተቆጥበዋል።
አዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችው ትምኒት በጉጉል ሥራ አስፈጻሚ ምላሽ ብዙም አልረካችም። ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታም ይህንኑ ቅሬታዋን አንጸባርቃለች።

ቢቢሲ፡ ያለፉት ሳምንታት ላንቺ እንዴት ነበሩ?
ትምኒት፡ አድካሚ ነበሩ። የሚዲያዎች ሁሉ ትኩረት መሆን ደስ የሚል ነገር አይደለም። ወጀብ ውስጥ የተወረወርኩ ያህል ነው የተሰማኝ።
ቢቢሲ፡ የጥናት ወረቀትሽ ምን ላይ ነበር የሚያጠነጥነው?
ትምኒት፡ በፍጹም ይህን ያክል አነጋጋሪ ይሆናል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር። ጥናቱ ስለ መድሎና ሌሎች በሰው ሰራሽ ልኅቀት ላይ የነበሩ የሥነ ምግባር ጉዳዮች የሚዳስስ ነው።
ቢቢሲ፡ ጉግል ግን እያለሽ ያለው ጥናቱ አንኳር ጉዳዮችን ቸል ብሏል፣ በዘርፉ አሉ የሚባሉ የጥናት ዳሰሳዎችን ገሸሽ አድርጓል ነው።
ትምኒት፡ ሲጀመር ያ ውሸት ነው። ሁለተኛ እውነት ነው ብንል እንኳ የሆኑ የጥናት ዳሰሳዎች በወረቀቱ ላይ አልተካተቱም ብሎ እኔን በዚያ መንገድ ማንገላታቱ ስሜት ይሰጣል? ለማንኛውም ያቀረቡት ክስ ቅጥፈት ነው፡፡
ቢቢሲ፡ ነጭ ብትሆኚ ጉግል አሁን ያደረሰብሽ ነገር ላይኖር ይችል ነበር? በተለየ ሁኔታ ይንከባከቡኝ ነበር ብለሽ ታስቢያለሽ?
ትምኒት፡ ይሄ ምንም ጥርጥር የለውም። በተለየ መንገድ ነበር የሚይዙኝ። እስከዛሬ በነበረው ሁኔታ እንደተረዳሁት ጉጉል የኔ ጉዳይ ትኩረት እንዳይስብ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። አልተሳካላቸውም።
ብዙዎቹ አብረውኝ የነበሩት እስከመጨረሻው አብረውኝ ነው የቆሙት። እኔን ደግፈው ነው የቆሙት። አለቃዬ እንዲሁ። ያም ሆኖ ነው እርምጃውን ለመውሰድ የጨከኑት።
ለዚህም ነው፤ ምንም ጥያቄ የለውም፤ (ጥቁር ባልሆን ኖሮ) ሁኔታዎች መልካቸውን ይቀይሩ ነበር ብዬ የማምነው።
ቢቢሲ፡ በእርግጥም እንዲያ ከሆነ የምታስቢው፣ ቀጣዩ ጥያቄ የሚሆነው ጉጉል ኩባንያ እንደ ተቋም ዘረኛ ተቋም ነው ብለሽ ታስቢያለሽ ማለት ነው?
ትምኒት፡ አዎ! ጉጉል ዘረኛ ተቋም ነው፡፡
ቢቢሲ፡ እንዲያ ብለሽ መደምደምሽ ጠጠር ያለ ክስ ይመስላል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግን የነሱ ሰራተኛ ነበርሽ አኮ (አይከብድም ኩባንያው ዘረኛ ነው ማለትሽ?)
ትምኒት፡ እኔ እንደማስበው ከሆነ አብዛኛዎቹ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መዋቅራዊ ዘረኝነት ውስጥ ተነክረዋል። ይሄን እንዴት መካድ እችላለሁ።
ቢቢሲ፡ ለምን ይመስልሻል ጥቁር ሴቶች በነዚህ ኩባንያዎች ውስጥ ውክልናቸው የቀጨጨው?
ትምኒት፡ ለዚህም ነው ጉግልም ይሁን ሌሎች የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እልም ያሉ ዘረኞች ናቸው የምለው። ዘረኝነታቸውም መዋቅራዊና ተቋማዊ ነው።
ቢቢሲ፡ ጉጉል ግን የዘርና የጾታ ስብጥር ተቆርቋሪ ነኝ፤ ግድም ይለኛል ይላል በተደጋጋሚ።
ትምኒት፡ ውሸቱን ነው። ኩባንያው ይሄ በፍጹም አይጨንቀውም። ስለ ጥቁሮች፣ ስለ ሴቶች ግድ የለውም።
ማድረግ ያለባቸው ነገር ቢኖር ይህን ምቶች የሚነሳቸውን ርእሰ ጉዳይ ገሸሽ ማድረግ ማቆም ነው። ሰዎች አፋቸውን እንዲዘጉ ማድረግ መተው አለባቸው። ስለ እኩልነት የሚጮኹ ሰዎችን መበቀል ማቆም አለባቸው።
'በቃ ኮሚቴ እናቋቁማለን፣ በቃ የተወሰኑ ሚሊዮን ዶላሮችን በጉዳዩ ዙርያ ኢንቨስት እናደርጋለን' ይላሉ።
ነገር ግን ያለውን ተቋማዊ ዘረኝነት የሚነቀንቅ ጥያቄ የሚያነሳ ሰው ሲያጋጥማቸው ምን እንደሚፈጠር በኔ የተየ ነገር ነው።
ለዚህም ነው (ኩባንያዎቹ) ለጾታና ለቀለም ስብጥር ይጨነቃሉ ብዬ የማላምነው።
ቢቢሲ፡ የጉግል ኩባንያ አለቃ ሱንዳር ቢቻይ ባንቺ ዙርያ ስለሆነው ነገር ይቅርታ ጠይቋል፤ አንቺን በግል ግን ይቅርታ አልጠየቀም። ለምን ይመስልሻል?
ትምኒት፡ ምን ይሄ ብቻ፣ ኩባንያው ነገሩን ስለያዘበት መንገድ እንኳን ይቅርታ አልጠየቀም እኮ። እኔ ስለምንም ነገር ይቅርታ ጠይቋል ብዬ አላምንም።
ነገሩን የያዝንበት መንገድ ትክክል አልነበረም አላለም። ትምኒት ላይ ስለወሰድነው እርምጃ ይቅርታ አድርጉልን አላለም።
ብቻ ለማንኛውም ጉጉል ይቅርታ ጠይቋል ብዬ በፍጹም አላምንም።
የሥራ አስፈጻሚው ይቅርታ እንዲሁ ለወጉ ያህል የተባለ ነው። ለራሳቸው ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው፤ ሌሎች ስለነሱ ያላቸው ስሜት እንዳይዛባ ያህል ነው የጠየቁት።
ቢቢሲ፡ የሰው ሰራሽ ልህቀት እየሄደበት ያለው መንገድ እንዴት ታይዋለሽ፤ የዘር መድሎዎ ያስጨንቅሸል?
ይህ ምንም አጠያያቂ አይደለም፡፡ ቀጣዩ የዘረኝነት ግንባር የሚሆነው ሰው ሰራሽ ልህቀት ነው። በዚህም የተነሳ ነገሩ ያሳስበኛል።
እኔም ሆንኩ ሌሎች ባልደረቦቼ ስለዚሁ ነገር የምንጨነቀውና የምናስተምረውም ለዚሁ ነው።
በዚህ መድልዎ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች፣ (ውክልናቸው የሳሳ የኅብረተሰብ ክፍሎች) ጉዳዩ ላይ ገብተው ነገሮችን እንዲያቃኑ ዕድሉ እስካልተሰጣቸው ድረስ (ወደፊት ዓለምን የሚቆጣጠረው) የሰው ሰራሽ ልህቀት ከጥቅሙ ይልቅ የሚያመጣው ጉዳት እንደሚያይል ነው የማስበው።
ቢቢሲ፡ ከዚህ በኋላ ምን ለማድረግ እያሰብሽ ነው ታዲያ?
ትምኒት፡ በቀጣይነት ምን ማድረግ እንዳለብኝ ለመወሰን ጊዜ እፈልጋለሁ።
አሁን ቅድሚያ የምሰጠው እኔን በመደገፍ ከኔ ጋር በመቆም አጋርነታቸውን ላሳዩኝ ባልደቦቼ ጥንቃቄ ማድረግ ነው።
እውነት ለመናገር ኩባንያዎች በእነሱ ላይ የበቀል እርምጃ እንዳይወሰዱባቸው ስጋት አለኝ።
ማስታወሻ፡ ቢቢሲ ዶ/ር ትምኒት ባነሳቻቸው ክሶች ላይ የጉግልን ሐሳብ ለማካተት ሞክሮ ምላሽ አላገኘም።














