ዶናልድ ትራምፕ፡ የአሜሪካ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ኃላፊነታቸውን ሊለቁ ነው

ዊሊያም ባር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዊሊያም ባር

የአሜሪካው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ቀድሞ ኃላፊነታቸውን እንደሚለቁ ፕሬዚደንት ትራምፕ አስታወቁ።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ዊሊያም ባር ለዶናልድ ትራምፕ ታማኝ ከሆኑ ግለሰቦች አንዱ ናቸው።

ይሁን እንጂ ዊሊያም ባር ኅዳር ላይ የተካሄደው ምርጫ ስለመጭበርበሩ ማረጋጋጫ እንደሌለ ከተናገሩ በኋላ በሁለቱ መካከል አለመግባባት ተፈጥሯል።

በሌላም በኩል የፍትህ መሥሪያ ቤቱ በምርጫ ዘመቻው ወቅት በተመራጩ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልጅ ላይ ምርመራ እያካሄደ እንደነበር ለሕዝብ ይፋ ባለማድረጋቸውም በትራምፕ ይተቻሉ።

የዊሊያምን ከኃላፊነት መልቀቅ በተመለከተ ግን ፕሬዚደንት ትራምፕ በትዊተር ገፃቸው "ግንኙነታችን በጣም ጥሩ ነበር። የላቀ ሥራም ሰርተዋል!" ሲሉ ገልፀዋቸዋል።

ዊሊያም ለፕሬዚደንቱ ባስገቡት የመልቀቂያ ደብዳቤም የሚጀምረው "ያለውን ሁኔታ ለማሳወቅ የተሰጠኝን እድል አደንቃለሁ" በማለት ነው።

ከዚያም የፍትሕ መሥሪያ ቤቱ ፕሬዚደንት በቅርቡ በተካሄደው ምርጫ የመራጮች ድምፅ ተጭበርብሯል በሚል የቀረበውን ክስና እነዚህ ክሶች እንዴት እንደሚቀጥሉ እየተመለከቱ መሆኑን ይገልፃል።

ይሁን እንጂ ስለ ክሱ ዝርዝር በደብዳቤያቸው ላይ ያሉት ነገር የለም።

ዊሊያም ታህሳስ 23 ከኃላፊነታቸው እንደሚለቁ በደብዳቤያቸው ላይ ከመግለፃቸው በፊትም ፕሬዚደንት ትራምፕ በሥልጣን ዘመናቸው ያስመዘገቡትን ስኬት አድንቀዋል።

የዊሊያም የሥልጣን ዘመን ትራምፕ ዋይት ሐውስን ለቀው ሲወጡ በፈረንጆቹ ጥር 20 ያበቃል።

ዐቃቤ ሕጉ ከሥልጣናቸው ሲለቁ ምክትል ዐቃቤ ሕግ የሆኑት ጄፍ ሮሰን እርሳቸውን ወክለው እንደሚሰሩ ትራምፕ አስታውቀዋል።