ትራምፕ፤ ኦባማ የሾሟቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መርማሪ ስቲቭ ሊኒክን አባረሩ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መርማሪ ስቲቭ ሊኒክ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና መርማሪ የሆኑት ስቲቭ ሊኒክ በዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከተባረሩ በርካታ ከፍተኛ የመንግሥት ሠራተኞች አንዱ ሆነዋል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ፤ ስቲቭ ሊኒክ በራስ መተማመናቸውን አጥተዋል፤ በሚቀጥሉት 30 ቀናት ሥራቸውን ይለቃሉ ብለዋል።

ዋና መርማሪ ሊኒክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክ ፓምፔዮን ሥልጣናቸውን ያለአግባብ ተጠቅመዋል በሚል እየመረመሯቸው ነበር።

ዴሞክራቶች፤ ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደራቸው የሚፈፅመውን አግባብነት የሌለው ተግባር የሚጠይቁ ሰዎችን እያባረሩ ነው ሲሉ ይተቻሉ።

ዶናልትድ ትራምፕ፤ ለዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ዴሞክራቷ ናንሲ ፔሎሲ በላኩት ደብዳቤ 'ምንም እንኳ ዋና መርማሪ መሾሙ ቅር ባይለኝም፤ በመርማሪው ላይ ያለኝ በራስ መተማመን ቀንሷል' ሲሉ ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል።

መርማሪው በማይክ ፖምፔዮ ላይ ምርመራ መጀመራቸው የታወቀው ከሥራቸው እንደተባረሩ ከተነገረ በኋላ ነው።

'ይህ ፕሬዝደንቱ ከታማኝ አገልጋዮቻቸው መካከል አንዱ የሆነቱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላይ ምርመራ በመከፈቱ ሆነ ብለው ያደረጉት ነገር ነው' ይላሉ ዴሞክራቱ ኤሊየት ኤንጅል።

ዴሞክራቱ ኤሊየት፤ ማይክ ፖምፔዮ ላይ የተከፈተው ክስ ዝርዝር ምን እንደሆነ ከመናገር ተቆጥበዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኮንገግረሱ አማካሪዎች፤ ፖምፔዮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኞችን ለግል ሥራቸው አዘዋቸዋል የሚል ክስ ቀርቦ መርማሪ ሊኒክ ይህንን ሲመለከቱ ነበር ይላሉ።

የሕግ ባለሙያው ሊኒክ በቀድሞው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ሲሆን የተሾሙት፤ ኃላፊነታቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አግባብነት የሌለው ተግባር ሲፈፅም ማጋለጥ እንዲሁም አላስፈላጊ ወጪዎችን መመዝገብ ነበር።

አፈ-ጉባዔ ናንሲ ፔሎሲ፤ ሰውዬው ኃላፊነታቸውን በሕጉ መሠረት እየተወጡ የነበሩ ናቸው። ሕገ-መንግሥቱን በመጠበቃቸው ነው የተቀጡት ሲሉ የትራምፕን ውሳኔ ነቅፈዋል።

አልፎም ፕሬዝደንቱ ኃላፊነታቸውን በሕጉ መሠረት እየተወጠ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞችን ከማባረር እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

ሌሎችም ዴሞክራቶች የሰውዬው መባረር እንዳላስደሰታቸው እየገለፁ ይገኛሉ።

ትራምፕ፤ ባለፈው ወር የደኅንነት ኮሚቴውን መርማሪ ሚካኤል አትኪንሰንን ማበረራቸው አይዘነጋም።