ፕሬዝዳንት ትራምፕ በተደረገላቸው ምርመራ ከኮሮናቫይረስ ነጻ ሆነው ተገኙ

ፕሬዝዳንት ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለኮሮናቫይረስ በተደረገላቸው ምርመራ ከበሽታው ነጻ ሆነው እንደተገኙ የጽህፈት ቤታቸው ሐኪም አስታወቁ።

ሾን ኮንሊይ ከሰዓታት በፊት ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቁት "ነጻ መሆናቸውን የሚያመለክተውን የፕሬዝዳናቱን የምርመራ ውጤት ቅዳሜ ምሽት ተቀብያለሁ" ሲሉ ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ምርመራ የተደረረገላቸው ከመካከላቸው የተወሰኑት የኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸው ከብራዚል ልኡካን ጋር ፍሎሪዳ ውስጥ ከተገናኙ በኋላ ነው።

በሽታው ከተገኘባቸው የልኡኩ አባላት መካከል የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ረዳት የሆኑ ግለሰብም ይገኙበታል ተብሏል።

"ትራምፕ ከብራዚል የልኡካን ቡድን ጋር ከነበራቸው የዕራት ፕሮግራም ከሳምንት በኋላ በተደረገላቸው ምርመራ ከበሽታውና ከበሽታው ምክልቶች ነጻ ሆነው ተገኝተዋል" ሾን ኮንሊይ ተናገረዋል።

የ73 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከልኡካን ቡድኑ ጋር ከተገናኙ በኋላ ምንም አይነት የበሽታው ምልክት አልታየብኝም በማለት እራሳቸውን ከሌሎች ለይተው አላቆዩም ነበር።

ነገር ግን ዋይት ሐውስ ውስጥ በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቀረበላቸውን ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ተከትሎ ምርመራ እንደሚያደርጉ ተናግረው ነበር።

የአሜሪካ መንግሥት እንደሚያዘው ከሆነ በሽታው ካለባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች ለ14 ቀናት እራሳቸውን ለይተው በቤታቸው ውስጥ መቆየት አለባቸው።

አሜሪካ ውስጥ እስካሁን ከ2,700 በላይ ሰዎች በወረርሽኙ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 54 ሰዎች ደግሞ በበሽታው ህይወታቸውን አጥተዋል።

አርብ ዕለት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሽታውን ለመዋጋት የሚያስችል የ50 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ለመፍቀድ የሚያስችላቸውን ብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግገዋል።

በዓለም ዙሪያ ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት በተጨማሪ ሌሎች መሪዎችና ፖለቲከኞችም በበሽታው ተይዘዋል የሚል ጥርጣሬ በመፈጠሩ ምርመራና እራስን ለይቶ የማቆየት እርምጃ እየወሰዱ ነው።

ባለፈው ሳምንት የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ባለቤታቸው በበሽታው ተይዘው በመገኘታቸው እራሳቸውን ለሁለት ሳምንታት ለይተው እንደሚያቆዩ አሳውቀዋል።

ስፔን ውስጥ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፔድሮ ሳንቼዝ ባለቤት በተደረገላቸው ምርመራ የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው የአገሪቱ መንግሥት አስታውቋል።

ባልና ሚስቱ ማድሪድ ውስጥ በሚገኘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መኖሪያ ቤት ውስጥ በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም ተገልጿል። ስፔን ከጣሊያን በመቀጠል አውሮፓ ውስጥ በሽታው ክፉኛ ያጠቃት አገር ናት።

በተጨማሪም የታላቋ ብሪታኒያ የጤና ሚኒሰትርና የወግ አጥባቂው ፓርቲ የፓርላማ አባል የሆኑት ናዲን ዶሪስ በተደረገላቸው ምርመራ ኮሮናቫይረሱ ስለተገኘባቸው በቤታቸው ውስጥ እራሳቸውን ለይተው ይገኛሉ።

ቀደም ሲልም የኢራን ምክትል የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የሆኑት ኢራጅ ሐሪርቺ በበሽታው እንደተያዙ ተረጋግጧል። ኢራን በቫይረሱ ክፉኛ ከተጠቁት አገራት መካከል የምትጠቀስ ስትሆን እስካሁን ከ600 በላይ ሰዎች በበሽታው ለሞት ተዳርገዋል።