በየመን ጀልባ ተገልብጣ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የሆኑ ከ60 በላይ ስደተኞች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን የሆኑ150 ስደተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ በየመን የባህር ዳርቻ ሰጥማ ከ60 በላይ ሰዎች ህይወት አለፈ።
ጀልባዋ እሁድ፣ ሐምሌ 27/ 2017 ዓ.ም መጥፎ የአየር ጠባይ ገጥሟት የተገለበጠች ሲሆን፤አብዛኞቹ ሟቾችም ኢትዮጵያውያን ናቸው ተብሎ እንደሚታመን የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ገልጿል።
ጀልባዋ የተገለበጠችው በደቡባዊቷ የመን አብያን ግዛት ሲሆን እስካሁን የ68 ስደተኞች አስክሬን መገኘቱን የአለም አቀፉ የስደተኞችን ድርጅት የየመን ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እስካሁን ድረስ 12 ሰዎችን መታደግ ቢቻልም፤ ቀሪዎቹ ደብዛቸው እንደጠፋ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።
አብዛኛዎቹ ተጎጂዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው ተብሎ እንደሚታመን የገለጸው አይኦኤም ክስተቱን "ልብ የሚሰብር" ሲል ገልጾታል።
ለተሻለ ህይወት በሚል ወደ ባህረ ሰላጤው አረብ አገራት ለሚያቀኑ የአፍሪካ ቀንድ ስደተኞች የመን ዋና መሸጋገሪያ ሆና ቆይታለች።
የመን በተለይም ወደ ሰሜን ሳዑዲ አረቢያ ለሚያቀኑ በርካታ ተስፋ የቆረጡ ስደተኞች መሸጋገሪያነቷ ቀጥሏል።
የነገ ኑሯቸውን እናቃለን ብለው በዚህ መንገድ ካቀኑትም መካከል በቅርብ ወራት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ በጀልባ አደጋ ህይወታቸውን አጥተዋል ወይም እንደጠፉ ከአይኦኤም የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ጀልባዋ ወደ 157 በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን አሳፍራ በአብዛኛው ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች የሚጠቀሙበትን አደገኛና ሰፊውን የባህር ዳርቻ መስመርን እየተጠቀመች እንደነበር የአይኦኤም የየመን ኃላፊ አብዱሳቶር ኢሶቭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የ54ቱ ስደተኞች አስክሬን በደቡባዊቷ የመን ካንፋር ግዛት ዳርቻ የተገኘ ሲሆን የሌሎች 14 ስደተኞች ደግሞ በአብያን ግዛት ዋና ከተማ ዚንጅባር በሚገኝ ሆሰፒታል አስክሬን ማስቀመጫ መወሰዱን አሶሺዬትድ ፕሬስ ዘግቧል።
የአቢያን የጸጥታ ዳይሬክቶሬት በርካታ አስክሬኖች በሰፊው የባህር ዳርቻ ላይዘ መገኘቱን ገልጾ ከፍተኛ ፍለጋ እና ህይወታቸውን የመታደግ ተልዕኮ መቀጠሉን በመግለጫው ማተቱን አሶሺየትድ ፕሬስ በዘገባው አስነብቧል።
በደረሰው አደጋ "በሚያሳዝን መልኩ የሰዎች ህይወት መቀጠፍ፤ በጥልቅ እንዳሳዘናቸው" የአይኦኤም ቃለ አቀባይ ተናግረዋል።
"ይህ ልብ የሚሰብር ክስተት የስደተኞቹን ተስፋ መቁረጥ እና ተጋላጭነትን በመጠቀም አጭበርባሪ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች በሚያሳልጧቸው አደገኛ ጉዞዎችን ለሚያደርጉ ስደተኞች የተጠናከረ የጥበቃ ዘዴ መሰረታዊ መሆኑን የሚያመላክት ነው" ብለዋል።
አብዱሳቶር ኢሶቭ በበኩላቸው ስደተኞች በህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች እንዳይበዘበዙ ለመከላከል ህጋዊ ጥበቃን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
"ሰዎች በህወጥ የሰዎች አዘዋሪዎች ተታልለው ወይም ወጥመድ ውስጥ ገብተው አደገኛ ጉዞዎችን እንዳያደርጉ እና ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲመጡ ሁሉም አገራት መደበኛ የስደት መንገዶችን እንዲያሰፉ እንሞግታለን" ብለዋል።
አይኦኤም ከአፍሪካ ቀንድ ወደ የመን የሚደረገው ጉዞ በጣም የተጨናነቀ እንዲሁም እጅግ አደገኛ ከሆኑ የስደት መንገዶች አንዱ" ሲል ገልጾት ነበር።
በመጋቢት ወር ከ180 በላይ ስደተኞችን አሳፍረው የነበሩ ሁለት ጀልባዎች በየመን ድሁባብ ግዛት የባህር ዳርቻ ሰጥማ ሁለት የበረራ ሰራተኞች ሲተርፉ ሌሎቹ ተሳፋሪዎች እንደጠፉ ሲሆን ሞተዋል ተብሎም ይፈራል።
በየመን የስደተኞች ምላሽ መስጫ ማዕከል የደረሱ ፍልሰተኞች ህገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎች ከባህር ዳርቻ ጠባቂዎች ለማምለጥ በሚል እያወቁ በግድየለሽነት ስደተኞችን በአደገኛ መንገዶች እንደሚልኩ መናገራቸውን አይኦኤም በሪፖርቱ አስፍሯል።
የከፋ አደጋ ባለው በዚህ መስመር ስደተኞች አሁንም መጓዛቸውን የቀጠሉ ሲሆን በባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ብቻ 60 ሺህ ስደተኞች ደርሰዋል።
ባለፈው አስር ዓመት የአይኦኤም የጠፉ ስደተኞች ፕሮጀክት በዚህ የጉዞ መስመር ከ3ሺህ 400 በላይ ስደተኞች መሞታቸውን እና መጥፋታቸውን የመዘገበ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ 1 ሺህ 400 ሞቶች የተከሰቱት በመስመጥ ነው።















