የአንድ ኪሎ ሽንኩርት ዋጋ ከሥጋ ከሁለት እጥፍ በላይ የተወደደባት አገር

ሽንኩርት

የፎቶው ባለመብት, Thinkstock

ለምግብ ማጣፈጫነት ከሚውሉ አትክልቶች መካከል ሽንኩርት አንዱ ነው። ሽንኩርት በዓለም ዙሪያ መሠረታዊ የምግብ ግብአቶች ከሆኑት መካከል ይጠቀሳል።

በበርካታ አገራት ሽንኩርት በድሃውም ሆነ በሃብታሙም ቤት የሚገኝ የምግብ አካል ሲሆን፣ ሥጋ ደግሞ እንደ ቅንጦት ምግብ የሚታይ ነው።

በፊሊፒንስ ግን ይህ በተቃራኒ ሆኗል፤ የሽንኩርት ዋጋ የትኛውንም አይነት ሥጋ ለመግዛት ከሚወጣው ገንዘብ በበርካታ እጥፍ ይበልጣል።

ለፊሊፒን ዜጎች ባለፉት ሳምንታት ጊዜ ሽንኩርት መሸመት ቅንጦት ሆኗል። ዋጋው በማሻቀቡ የተነሳ የሽንኩርት መግዣ ከሥጋ መግዣ በእጅጉ ንሯል።

በዚህ ሳምንት ፊሊፒንስ ውስጥ አንድ ኪሎ ሽንኩርት 11 ዶላር (600 ብር ገደማ) ሲሆን፣ የአንድ ሙሉ ዶሮ ሥጋ ግን 4 ዶላር (220 ብር ገደማ) ብቻ ነው።

የሽንኩርት ዋጋ ንረት የፈጠረውን የገበያ ክፍተት ለመጠቀም ያለሙ ነጋዴዎች በሕገወጥ መንገድ ሽንኩርት ሲያስገቡ በአገሪቱ ባለሥልጣናት ተይዘዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ብቻ 310,000 ዶላር የሚያወጣ የሽንኩርት ጭነት፣ ልብስ ነው የሚል መለያ ተለጥፎበት ከቻይና በድብቅ ሲገባ ተይዟል።

በዋና ከተማዋ ማኒላ የሚገኙ ምግብ ቤቶች በሽንኩርት መጥፋት ምክንያት ሽንኩርት በርከት ብሎ የሚገባባቸው ምግቦችን ማቅረብ አቁመዋል። በተጨማሪም በርገር ላይ የሚጨመረው የሽንኩረት ለስሙ ጣል የሚደረግ ሲሆን፣ በአንዳንድ ቦታዎችም በርገር ከምግብ ከዝርዝራቸው ወጥቷል።

ይህንን የሽንኩርት መጥፋት ለማካካስ አንዳንዶች ሌሎች አማራጮችን እየተጠቀሙ ነው። ለዚህም ጣዕሙ የተለመደው አይነት ሽንኩርት ያልሆነ፣ መጠኑም በጣም ትንሽ የሆነውን በፊሊፒንስ ውስጥ የሚታወቅ የተለየ ሽንኩርት ዝርያ ለመጠቀም ተገደዋል።

ሽንኩርት

የፎቶው ባለመብት, Shutterstock

የፊሊፒንስ የግብርና መሥሪያ ቤት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ባወጣው መረጃ መሠረት በአገሪቱ ከሚፈለገው የሽንኩርት መጠን በታች ይመረታል ብሎ ገምቶ ነበር።

ፊሊፒንስ በነሐሴ እና በመስከረም ወራት ወጀብ በቀላቀለ በከባድ አውሎ በመመታቷ የሽንኩረት ምርቷ ከተጠበቀውም በታች አስቆልቁሏል።

ይህንን ተከትሎም ችግሩን ለመቅረፍ “ከውጭ አገር ሽንኩርት ማስገባት የተጀመረው ዋጋው በእጅጉ ከናረ በኋላ ነው” ሲሉ አንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ተናግረዋል።

ከሳምንታት በፊት የአገሪቱ መንግሥት አቅርቦቱን ለማረጋጋት እና ዋጋውን ለመቆጣጠር 22 ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ ሽንኩርት ከውጭ አገራት እንዲገባ ወስኗል።

ነገር ግን ባለሙያዎች ለሽንኩርት ዋጋው መናር መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋሉ። በፊሊፒንስ ግብርና መሥሪያ ቤት ባለሙያ የነበረው ፌርሚን አድሪያኖ፣ የአገሪቱ ምርት እንደሚቀንስ ሲታወቅ ያለውን ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል አቅርቦት በጊዜ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት ነበረበት ይላል።

ሌላው ለተፈጠረው የሽንኩርት እጥረት እንደምክንያት በፊሊፒሊስ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በግብርና ዘርፉ አመራር ውስጥ ያለ ብቃት ማነስ ነው ይላሉ።

ለዚህም ባለፈው ዓመት የተመረጡት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ፈርዲናንድ ማርቆስ ምንም ልምድ ሳይኖራቸው እራሳቸውን በተደራቢነት የግብርና ሚኒስትር አድርገው መሾማቸውን ይጠቅሳሉ።

ሽንኩርት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶች ባለሙያ የሆኑት ሲንዲ ራይስዊክ እንደሚሉት፣ እጥረት ከመከሰቱም በፊት ፊሊፒንስ ለውትሮው ከምታመርተው በላይ የምትጠቀም እና ሽንኩርትን ከውጭ የምታስገባ አገር ናት።

ይህ የፊሊፒናውያን የሽንኩርት ፍላጎትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ ነው። ለምሳሌም በ2011 (እአአ) 5 ሚሊዮን ኪሎ ግራም የነበረው፣ በ2016 ላይ ወደ 132 ሚሊዮን ኪሎ ግራም አድጓል።

ባለሙያዋ “እንደ ዋጋው እና አቅርቦቱ ሁኔታ ፊሊፒንስ ሽንኩርትን በአብዛኛው የምትገዛው ከሕንድ፣ ከቻይና እና ከሆላንድ ነው” ይላሉ።

ለዚህ ምክንያት ከሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ አገሪቱ ካላት የአየር ንብረት አንጻር እና ከምታበቅለው የሽንኩርት ዝርያ አንጻር አብዛኛው የሽንኩርት ምርቷ ከእርሻ ላይ ከተሰበሰበ በኋላ በአጭር ጊዜ የሚበላሽ መሆኑ ነው።

ይህም በሰሜን አሜሪካ እና በሰሜን አውሮፓ ውስጥ ከሚሆነው የተለየ ነው። በእነዚህ አካባቢዎች ሽንኩርትን በትክክለኛው ሁኔታ በማከማቸት አስከ አንድ ዓመት ድረስ ሳይበላሽ እንዲቆይ ማድረግ ይቻላል ይላሉ ባለሙያዋ።

በአብዛኛው የዓለም ክፍሎች ውስጥ ሽንኩርት በስፋት ጥቅም ላይ ከሚውሉ አትክልቶች መካከል አንዱ ነው። በዚህም ምክንያት በመጠን በስፋት ከሚመረቱት አትክልቶች መካከል ከቲማቲም እና ከኩከምበር ቀጥሎ ሦስተኛው ለመሆን ችሏል።

በአሁኑ ወቅት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በሌሎች አገራት ውስጥም የሽንኩርት ዋጋ ጨምሯል። ለምሳሌም ይፋዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ብራዚል ውስጥ የሽንኩርት ዋጋ ከ130 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል።

ለሽንኩርት ዋጋ መጨመር እንደምክንያት ከሚጠቀሱት መካከልም የሚመረትበት የመሬት ስፋት መቀነስ እና የዓለም አቀፍ የምንዛሬ ዋጋ መጨመር እንዲሁም በዩክሬን ጦርነት የተነሳ የምርት ግባቶች ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መናር ናቸው።