ዩኬ፤ "ዜጎቼ ፈረንሳይ ውስጥ ለምን እንደተበደሉ ይመርመርልኝ" ስትል ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የዩናይትድ ኪንግደም የባሕል ሚኒስትር ዜጎቼ ፈረንሳይ ውስጥ ለምን መጎሳቆል እንደደረሰባቸው ይጣራልኝ ሲሉ የአውሮፓ እግር ኳስ ማሕበርን ጠየቁ።
በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ የተፈጠረውን ነገር "አጅግ አሳሳቢ" ነው ብለዋል ሚኒስትሯ።
ባለፈው ቅዳሜ በተካሄደው የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ጨዋታ የእንግሊዝ ክለብ እግር ኳስ ደጋፊዎች በፈረንሳይ ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ተተኩሶባቸዋል ተብሎ ነበር።
ሚኒስትሯ ናዲን ዶሪስ ሁሉም ሰው የተፈጠረው ነገር ምን እንደሆነ ማወቅ ይፈልጋል ብለዋል።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማሕበር በቅዳሜው ጨዋታ የተፈጠረውን "በፍጥነት እመረምራለሁ" ብሏል።
የፈረንሳይ ስፖርት ሚኒስትር ከአውሮፓ እግር ኳስ ማሕበር እንዲሁም ከስታድየሙ ኃላፊዎችና ፖሊስ ስብሰባ ጠርተዋል።
በሌላ በኩል የፈረንሳይ ሃገር ውስጥ ሚኒስትር ጄራልድ ዳርማኒን ደግሞ እንግሊዛዊያን ደጋፊዎችን ወቅሰዋል።
ቅዳሜ ዕለት በርካታ ብሪታኒያዊያን ደጋፊዎች ሕጋዊ ያልሆነ መግቢያ ይዘው ለመግባት ሞክረዋል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ጠባቂዎችን አጥቅተዋል ሲሉ ትዊተር ገፃቸው ላይ ለጥፈዋል።
ቅዳሜ ዕለት የነበረው የቻምፒዮንስ ሊግ ፋፃሜ ከታቀደለት ሰዓት 36 ደቂቃዎች ዘግይቶ ነው የጀመረው።
የአሕጉሪቱ እግር ኳስ ማሕበር ለዚህ ምክንያቱ ደጋፊዎች አርፍደው መድረሳቸው ነው ብሏል።
ነገር ግን በርካታ የሊቨርፑል ደጋፊዎች ያረፈድነው የነበረው ሰልፍ እጅጉን ረዥም ስለነበርና ፖሊስ ደጋፊዎችንበማጎሳቆሉ ነው ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማሕበሩ ዘግይቶ መጓተቱ የተፈጠረው በደኅንነት ጉዳዮች ምክንያት እንዲሁም በርካታ የሊቨርፑል ደጋፊዎች "ፎርጅድ" ቲኬት መያዛቸው ነው ብሏል።
በፍፃሜው ሪያል ማድሪድ ሊቨርፑልን 1 ለምንም ረትቶ ዋንጫ ማንሳቱ ይታወሳል።
የአካል ጉዳት ያለበትን ልጁን ወደ ፓሪሱ ግዙፍ ስታድዬም ይዞ ያቀናው የሊቨርፑል ደጋፊው ቶም ዋይትኸርስት፤ ማሕበሩና ፖሊስ ደጋፊዎችን ያስተናገዱበት መንገድ "አሳፋሪ" ነው ብሏል።
የሊቨርፑል ግዛት የሆነው መርሲሳይድ ፖሊስ ጨዋታውን ለመመልከት የሄዱ መኮንኖቼ የሊቨርፑል ደጋፊዎችሥርዓታቸውን ጠብቀው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ታዝበዋል ብሏል።
የፓሪስ ፖሊስ ከግርግሩ ጋር በተያያዘ 105 በቁጥጥር ሥር አውሎ እንደነበርና አሁንም 39 ሰዎች በፖሊስ እጅእንዳሉ አሳውቋል።
ሊቨርፑል የእግር ኳስ ክለብም ደጋፊዎች ለምን እንደተጎሳቆሉ ይጣራልኝ ሲል መግለጫ አውጥቷል።
የሊቨርፑል የግራ መስመር ተመላላሽ አንዲ ሮበርትሰን ለአንድ ጓደኛው ቲኬት ቢሰጥም ጓደኛው ግን መግባትእንዳልቻለ ከጨዋታው በኋላ ተናግሯል።
ጨዋታው ከተጀመረም በኋላ ከስታዲየም ውጭ የነበሩ ደጋፊዎች ቁጥር መበራከቱ የቀጠለ ሲሆን ፖሊሶች አስለቃሽ ጭስ በመጠቀም ከስታዲየሙ እንዲርቁም እንደተደረገ ተዘግቧል።
የፈረንሳይ ፖሊስ በበኩሉ ሃሰተኛ ትኬቶችን የያዙ ደጋፊዎች በግድ ወደ ስታዲየሙ ለመግባት እንደሞከሩና "ፖሊስ በሰጠው ፈጣን ምላሽ ሁኔታው እንደተረጋጋ" ገልጧል።












