ለህክምና 560 ሺህ ዶላር ተዋጥቶለት የነበረው ኤርትራዊ ህይወቱ አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Henpas Entertainment
በደም ካንሰር ተይዞ ለህክምና ባቀረበው ተማጽኖ በውጪ በሚኖሩ ኤርትራውያን ገንዘብ የተዋጣለት ኤርትራዊ በቱርክ ኢስታንቡል በህክምና ላይ ሳለ ህይወቱ ማለፉ ተሰምቷል።
ዮናስ ጸጋዬ ከህመሙ ለማገገም ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ተማጽኖ አቅርቦ የነበረ ሲሆን ‘ጎፈንድ ሚ’ በተሰኘው የገንዘብ ማሰባሰቢያ 560 ሺህ ዶላር ተዋጥቶለት ነበር።
ይህ ‘ጎፈንድሚ’ አካውንት የተከፈተው ካናዳ በሚኖር መበርሃቱ ህድራይ በተባለ ኤርትራዊ ነው።
ዮናስ ከጥቂት ቀናት በፊት ህይወቱ ማለፉን እና ቀብሩም በቀጣዮቹ ቀናት እንደሚፈጸም ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዮናስ ‘ሆድኪንግ ሊፎማ’ በተባለ እና የዩኬ ብሄራዊ የጤና አገልግሎት ያልተለመደ ብሎ በሚገልጸው የደም ካንሰር ዓይነት ነበር የታመመው።
እንደ ጤና ተቋሙ ገለጻ ከሆነ በኬሞቴራፒ ብቻ ወይም በጨረር ህክምና በታገዘ ኬሞ ቴራፒ ውጤታማ በሆነ መንገድ ሊድን የሚችል ነው።
እጅግ የተለመደው የህመሙ ምልክት ደግሞ ህመም የሌለው እጢ በአንገት፥ በታፋ ወይም ብብት አከባቢ ከእብጠት ጋር መከሰት ነው።
ህክምናውን በውጪ እንዲከታተል ተፈቅዶለት የነበረ ቢሆንም ያንን የሚሸፍን ገንዘብ እሱም ሆነ ቤተሰቡም አልነበረውም።
ታዲያ በኤርትራ የሚገኝ ‘ሄንፓስ’ የተባለ የመዝናኛ ቲዩብ ቻናል በፈጠረው ዕድል ቤተሰቡ ‘ጎፈንድ ሚ አማካኝነት የህክምና ገንዘብ ለማግኘት ተማጽኖ ካቀረቡ በኃላ በውጪ የሚኖሩ ኤርትራውያን ፈጣኝ ምላሽ ሰጥተዋል።












