የሩሲያን ወረራ ተቃውመው ነበር የተባሉት ሩሲያዊ ሚሊየነር ሕይወታቸው አልፎ ተገኘ

ሚሊየነሩ ፓቬል አንቶቭ

የፎቶው ባለመብት, PAVEL ANTOV/VK

የምስሉ መግለጫ, ሚሊየነሩ ፓቬል አንቶቭ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን ጦርነት ተቃውመው ነበር ተብሏል

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን ጦርነት ተቃውመው ነበር የተባሉት ሚሊየነር ለጉብኝት በሄዱበት ሕንድ አገር በሚገኝ ሆቴል ሕይወታቸው አልፎ ተገኘ።

ሚሊየነሩ ፓቬል አንቶቭ በምስራቅ ሞስኮ በምትገኘው ቭላድሚር ከተማ በብዙዎች የሚታወቁ ፖለቲከኛ እና ነጋዴ ነበሩ።

በተመሳሳይ ጉዞ ከሚሊየነሩ ጋር አብረው ተጉዘው የነበሩት ጓደኛቸውም ከሁለት ቀናት በፊት እንዲሁ አጠራጣሪ በሆነ ሁኔታ ሕይወታቸው አልፏል።

አንቶቭ ከጥቂት ወራት በፊት የሩሲያን ወረራ የሚተች ጽሑፍ በዋትስአፕ አካውንታቸው ላይ ቢታይም ጦርነቱን አልተቃወምኩም ሲል አስተባብለው ነበር።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከከፈተች በኋላ አጠራጣሪ በሆነ ሁኔታ ሕይወታቸው የሚያልፍ ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። በተለይ ደግሞ ሕይወታቸው እያለፈ ያሉት ጦርነቱን የሚቃወሙት ናቸው።

ምንም እንኳ የሕንድ ፖሊስ ከግለሰቡ ሕይወት ማለፍ ጋር በተያያዘ የወንጀል ድርጊት ስለመኖሩ ምንም ማስረጃ አላገኘሁም ይበል እንጂ የሚሊየነሩ አሟሟት ግን ለበርካቶች አጠራጣሪ ሁኔታን ፈጥሯል።

የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን የ65 ዓመቱ አንቶቭ ከነበሩበት ሆቴል መስኮት ላይ ከወደቁ በኋላ ሕይወታቸው አልፏል ሲሉ ዘግበዋል።

ከዚህ ሚሊየነር ጋር አብረው በጉዞ ላይ የነበሩት ቭላድሚር ቡዳኖቭ ከሁለት ቀናት በፊት በዚሁ ሆቴል ሕይወታቸው አልፏል።

የሕንድ ፖሊስ ሱፐር ኢንቴንደን ቪቬካንናንዳ ሻርማ ሰለ ሁለቱ ግለሰቦች አሟሟት ሲናገሩ ቡዳኖቭ አርብ ዕለት ስትሮክ አጋጥሟቸው ሕይወታቸው ሲያፍ ጓደኛቸው አንቶቭ ደግሞ “በጓደኛው ሞት ጭንቀት ውስጥ ከገባ በኋላ እርሱም እሁድ ዕለት ሞቷል” ብለዋል።

በሕንድ ኮልካታ የሚገኝ የሩሲያ ቆንጽላ “በእነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች ውስጥ የወንጀል ድርጊት ስለመኖሩ ፖሊስ ማስረጃ አላገኝም” ብሏል።

አንድ የአስጎብኚ ድርጅት ባልደረባ የሆነ ግለሰብ ደግሞ ለቡድኖቭ ሞት ምክንያቱ አልኮል ሊሆን ይችላል ብሏል። ጂቴንደራ ሲንግሃ የተባለው ግለሰብ “የአልኮል መጠጦች ይዞ ስለነበረ ብዙ መጠጥ ጠጥቷል” ሲል ለሪፖርተሮች ተናግሯል።

ፓቬላ አንቶቭ የስጋ ማቀነባበሪ ተቋም ባለቤት ሲሆኑ ፎርብስ የተጣራ ሃብታቸው 140 ሚሊዮን ይጠጋል ሲል እአአ 2019 ላይ ግምቱን አስቀምጦ ነበር።

ከጥቂት ወራት በፊት የሩሲያ ሚሳኤል በዩክሬን መኖሪያ ቤትን አውድሞ አንድ አባትን ገድሎ፣ ልጅ እና እናት ከተጎዱ በኋላ በሚሊየነሩ የዋትስአፕ አካውንት ላይ “ይህን ሽብር ብሎ ከመጥራት ውጪ ሌላ ምንም ማለት አይቻልም” ሲሉ መግለጻቸው በስፋት ተዘግቦ ነበር።

ይህ መልዕክት የተሰረዘ ሲሆን አንቶቭ ወደ ማሕበራዊ ሚዲያ መጥተው አገራቸውን እንደሚወዱ እንዲሁም ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን እና ጦርነቱን እንደሚደግፉ በመግለጽ የተሰጠው አስተያየት የእርሳቸው እንዳልሆነ አስተባብለው ነበር።