የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት እስከ ሐሙስ ወደ መቀለ እንደሚገባ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያ ፌደራል ሠራዊት እስከ መጪው ሐሙስ ድረስ ወደ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ በመግባት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንደሚጀምር ተነገረ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ እና ከህወሓት ሪዎች ጋር የተደረገውን ድርድር መንግሥትን በመወከል በመሪነት የተሳተፉት አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን እንዳሉት ሠራዊቱ በዚህ ሳምንት ወደ መቀለ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።
ለሁለተኛ ጊዜ ናይሮቢ ላይ በተደረሰው መግባባት መሠረትም የህወሓት ተዋጊዎች ከባድ መሳሪያዎቻቸውን የማስረከቡ ተግባር እንደሚጀመርም ሬድዋን ገልጸዋል።
ሰኞ ታኅሣሥ 17/2015 ዓ.ም. ከአንድ ዓመት ተኩል ከሚሆን ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ ተወካዮች አፈ ጉባኤ የተመራ የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ልዑካን ቡድን መቀለ ደርሶ ከተመለሰ በኋላ ነው አምባሳደር ሬድዋን በትዊተር ገጻቸው ላይ የሚጠበቁ ቀጣይ ጉዳዮችን ያመለከቱት።
የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና የግዙፎቹ የመንግሥት የመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅራቢ ተቋማት ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች የተካተቱበት የልዑካን ቡድን፣ ከትግራይ ክልል አመራሮች ጋር በሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ላይ መወያያታቸው ተዘግቧል።
አምባሳደር ሬድዋን በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳመለከቱት የልዑካን ቡድኑን ጉዞ በተመለከተ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ማብራሪያ መሰጠቱን ገልጸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በትግራይ ክልል የመሠረታዊ አግልግሎቶች የማስጀመሩ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አዘዋል ብለዋል።
በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከረቡዕ ታኅሣሥ 19/2015 ዓ.ም. ጀምሮ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አሳውቋል። ዋነኛው የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ መንግሥታዊው ኢትዮ ቴሌኮምም ሥራውን በሚመለከት መግለጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።
መቀለ ላይ በፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት እና በትግራይ አመራሮች መካከል በተካሄደው ውይይት ላይ ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ የተደረሰው የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲሆን የኤርትራ እና የአማራ ክልል ኃይሎች ከትግራይ እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ይህ በፌደራሉ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተደረገው ጉዞ በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት ለመቋጨት በተደረገው ስምምነት ውስጥ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ሰኞ አመሻሽ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
በትግራይ በኩል ለሰላም ስምምነቱ ቁርጠኝነት መኖሩን በመግለጽ፣ በሁለቱም ወገኖች በኩል መተማመን መፈጠሩን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ለዚህም ማሳያ የፌደራል መንግሥቱ ልዑካን ወደ ትግራይ ሲገቡ ጥብቅ የደኅነት ጥበቃ እንዲደረግላቸው አንዳቸውም አለመፈለጋቸውን ጠቅሰዋል።
ለሁለት ዓመታት የተካሄደውን ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ለማብቃት በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት የፌደራል መንግሥቱ እና የህወሓት አመራሮች ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ ጥቀምት 23/2015 ዓ.ም. ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት ካደረጉ በኋላ ጦርነት መቆሙ ይታወቃል።
ከዚያም በኋላ ሁለቱ ወገኖች የደረሱትን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ በወታደራዊ አዛዦቻቸው በኩል በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ላይ ለሁለት ጊዜ ተገናኝተው ተወያይተው ከመግባባት ላይ ደርሰዋል።












