የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነገ ጀምሮ ወደ መቀለ በረራ እንደሚጀምር አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Airlines
ለሁለት ዓመት ከዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት ጋር በተያያዘ የአየር ጉዞ ተቋርጦባት ወደ ነበረችው መቀለ ከተማ ነገ ታኅሣሥ 19/2015 ዓ.ም. መደበኛ በረራ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ።
አየር መንገዱ ይህንን ያስታወቀው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራው የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ መቀለ ካመሩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎም የአቪዬሽን ሠራተኞች በክልሉ ያለውን ሁኔታ ለመቃኘት ወደ መቀለ አቅንተው እንደነበር የአየር መንገዱን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰውን ዋቢ አድርገው የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ሠራተኞቹም በመቀለ ከተማ የሚገኘው የአሉላ አባ ነጋ ማረፊያ ለበረራ ምቹ መሆኑን የማረጋገጥ ተግባር እንዳከናወኑም ተገልጿል።
አሁን የሚጀመረው በረራ በቀን አንድ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፣ የደንበኞችንም ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ የበረራ ቁጥር ከፍ እንደሚልም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል ተብሏል።
ከመቀለ በተጨማሪ በሁሉም የትግራይ ክልል የበረራ መዳረሻዎች የአየር ትራንስፖርት ለመጀመር አስፈላጊው ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ተገልጿል።
ከሁለት ዓመት በላይ መሠረታዊ አገልግሎቶች ተቋርጠውባት በነበረችው የትግራይ ክልል፣ በተለያዩ ቦታዎች ተቆራርጦ የነበረው የትግራይ ሕዝብ እንዲገናኝም ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።
ስምምነቱን ተከትሎ ተቋርጠው የነበሩ የኤሌክትሪክ፣ የስልክና የባንክ አገልግሎቶች እየተመለሱ እንደሆነም ተገልጿል።
በቅርቡም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሽረ፣ በአላማጣና በኮረም ከተሞች የባንክ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታውቋል።
በእነዚህ ከተሞች የሚሰጠው አገልግሎት ከውጭ አገር እና ከአገር ውስጥ የሚላኩ ገንዘቦችን መቀበል እንደሆነና ከቁጠባ ገንዘብ ማውጣትም ሆነ ከሂሳብ ወደ ሂሳብ ማንቀሳቀስ እንደማይቻልም ተገልጿል።
በቅርቡ የትግራይ ርዕሰ መዲና መቀለ ከብሔራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆጣጠሪያ ማዕከል [ግሪድ] ጋር በመገናኘቷ ለረዥም ጊዜያት በጨለማ ተውጣ የነበረችው ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት አግኝታለች።
በተጨማሪም ከተጣለው እገዳ ጋር ተያይዞ በተፈጠው የሸቀጦች እና የሰብዓዊ እርዳታ እጥረትንም ለመቅረፍ እንዲሁም ተደራሽ ለማድረግ አስተዋጽኦ ያደርጋልም ተብሏል።
ከሁለት ዓመት በፊት ተከስቶ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ለቀጠፈውና በሚሊዮኖች ሕይወት ላይ የማይነገር ሰቆቃ ያደረሰው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በፌደራሉ መንግሥትና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት መደረሱ ይታወሳል።
ስምምነቱ ከተፈረመ ከስድስት ሳምንታት በላይ ቢሆነውም የኤርትራ ወታደሮች እና የፌደራሉ መንግሥት አጋር የሆኑት የአማራ ኃይሎች ከትግራይ ክልል የመውጣታቸው ጉዳይ አሁንም ስጋት እንደሆነ እየተነገረ ነው።
የሰላም ስምምነቱ ለትግራይ ያልተገደበና ያልተቆራረጠ ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ፣ በትግራይ ለሁለት ዓመት የተቋረጠው መሠረታዊ አገልግሎት እንዲመለስ እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች ትጥቃቸውን በመፍታት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ ያለመ ነው።
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትና በናይሮቢ የትግበራ ሰነድ መሠረት የትግራይ ኃይሎች የከባድ መሣሪያ ማውረድ የሚካሄደው የውጭ እና የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት ያልሆኑ የክልል ኃይላት ከትግራይ በተመሳሳይ ወቅት ሲወጡ እንደሆነ ተጠቅሷል።












