የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መቀለ ገቡ

የፌደራሉ መንግሥት መቀለ ሲደርሱ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, DW

የምስሉ መግለጫ, የፌደራሉ መንግሥት ባለሥልጣናት መቀለ ሲደርሱ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የፌደራል መንግሥቱ የመከላከያ ሠራዊት መቀለን ለቆ ከወጣ ከአንድ ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ወደ ትግራይ ክልል መዲና መቀለ ገቡ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራው የመንግሥት ከፍተኛ የባለሥልጣናት ቡድን፣ ዛሬ ሰኞ ታኅሣሥ 17/2015 ዓ.ም. ጠዋት ወደ ትግራይ ማምራቱን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል የቴሌቪዥን ጣቢያ ደግሞ የፌደራል መንግሥት ልዑክ ቡድን መቀለ መድረሳቸውን በፎቶ አስደግፎ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አውጥቷል።

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየው የእርስ በርስ ጦርነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ውስጥ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. በተደረገ ስምምነት ነበር የቆመው።

ደም አፋሳሹ ጦርነት በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አፋር እና ወደ አማራ ክልሎች ተዛምቶ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳትን በማስከተል ከባድ ውድመትን ካስከተለ በኋላ በዘላቂነት ግጭትን ለማስቆም በተደረሰው ስምምነት ነው ጦርነት የቆመው።

በደቡብ አፍሪካ ከዚያም በኋላ ናይሮቢ ኬንያ ላይ ሁለቱ ወገኖች የስምምነቱን አፈጻጸም በተመለከተ በወታደራዊ አዛዦች አማካይነት የአፈጻጸም ስምምነት ተፈርሞ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።

ይህ በፌደራሉ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተደረገው ጉዞ በትግራይ የተካሄደውን ጦርነት ለማብቃት በተደረገው ስምምነት ውስጥ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ሰኞ አመሻሽ ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

በትግራይ በኩል ለሰላም ስምምነቱ ቁርጠኝነት መኖሩን በመግለጽ፣ በሁለቱም ወገኖች በኩል መተማመን መፈጠሩን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ ለዚህም ማሳያ የፌደራል መንግሥቱ ልዑካን ወደ ትግራይ ሲገቡ ጥብቅ የደኅንት ጥበቃ እንዲደረግላቸው አንዳቸውም አለመፈለጋቸውን ጠቅሰዋል።

የፌደራሉ መንግሥት ባለስልጣናት

የፎቶው ባለመብት, EBC

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ከፍተኛ የፌደራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት ወደ ትግራይ ሲያቀኑ ይህ የመጀመሪያው ሲሆን፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ግንኙነት መሻሻል እንደ አንድ ማሳያ ነው ተብሏል።

ጦርነቱ ተቀስቅሶ ከሳምንታት በኋላ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት መቀለን እና ሌሎች የትግራይ አካባቢዎችን ከተቆጣጠረ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ መቀለ ተጉዘው ከወታደራዊ አመራሮቻቸው ጋር መገናኘታቸው ይታወሳል።

ወደ ትግራይ ያመራው የልዑካን ቡድን ከአገሪቱ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በተጨማሪ፣ ከህወሓት ጋር በተደረገው ድርድር ላይ መንግሥትን ወክልው የተሳተፉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንንት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ይገኙበታል።

በልዑካን ቡድኑ ውስጥ የፌደራል መንግሥቱ ሚኒስትሮች፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የብሔራዊው ምክክር ኮሚሽን አባላት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች እና ሌሎችም እንደተካተቱበት ለማወቅ ተችሏል።

የልዑክ ቡድኑ መቀለ አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ ሲደርስ የህወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት ጌታቸው ረዳ እና የሃይማኖት አባቶች አቀባበል አድርገዋል።

ጦርነቱ እየተካሄደ በቆየበት አብዛኘውን ጊዜ ከቀሪው የአገሪቱ ክፍል ጋር ተቆራርጦ የቆየው የትግራይ ክልል በሁለቱ ወገኖች መካከል ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ባለፉት ሳምንታት የመብራት፣ የስልክ እና የባንክ አገለግሎቶች መልሰው እየተጀመሩ መሆናቸው ተነግሯል።

ይህ በፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አማካይነት ወዳደ ትግራይ የተደረገው የመጀመሪያው ጉዞ የተደረሰው የሰላም ስምምነት አፈጻጸምን ለመገምገም ያለመ መሆኑን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

እሁድ ታኅሣሥ 16/2015 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን ሁለተኛውን የናይሮቢ ውይይት ተከትሎ የሰላም ሂደቱን መገምገማቸውን ገልጸዋል።