በሶማሊያ ወጣት ሴቶችን በሱስ እያማቀቀ ያለው መድኃኒት

አሚኖ አብዲ

የፎቶው ባለመብት, FATHI MOHAMED AHMED

የምስሉ መግለጫ, አሚኖ አብዲ በሱስ ጉዳይ ላይ በግልጽ መነጋገር እንደ ነውር መቆጠሩ ይቀንሳል ብላ ተስፋ በማድረግ ታሪኳን ለቢቢሲ አጋርታለች።

በሞቃዲሹ ወጣት ሴቶችን ለሱስ የዳረገው አደገኛ መድኃኒት በይበልጥ የታወቀው ባለፈው ዓመት የ22 ዓመት ሴት አስክሬን በከተማዋ መንገድ ላይ ከተገኘ በኋላ ነበር።

የወጣቷ ሕይወት ያለፈው ኦፒኦይድ የተባለ መድኃኒት ከልክ በላይ በመውሰዷ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ተናግረዋል።

ኦፒኦይድ በተለይም በቀዶ ሕክምና ጊዜ ለህመም ማስታገሻ በሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጥ መድኃኒት ነው። ያለአግባብ ለዚያውም ከልክ በላይ ሲወሰድ ለሱስ ይዳርጋል።

ወጣቷ በማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪ ነበረች።

ጓደኞቿ እንደሚሉት ወጣቷ ለረዥም ጊዜ መድኃኒት ትወስድ ነበር።

በጣም ታዋቂ የሆኑ የተወሰኑ የቲክቶክ ቪዲዮዎችን ስትቀርጽም በመድኃኒቱ አማካይነት ከፍ ባለስሜት ሆና ነበር ይላሉ።

ፖሊስም በሞቃዲሹ እና በሌሎች የሶማሊያ አካባቢዎች ሴቶችን ጨምሮ መድኃኒቱን የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር እየተበራከተ መሆኑን ገልጿል። ፖሊስ እንደሚለው ሰዎች አዲስ ወደሆነው ሱስ አስያዥ መድኃኒት ፊታቸውን አዙረዋል።

ነዋሪዎች ሕገ ወጥ ተብለው ያልተለዩትን ጫት ይቅማሉ፣ አልኮል መጠጦችን ይጠጣሉ፣ ማስቲሽ ይስባሉ፣ ሃሺሽ ያጨሳሉ። በርካታ ሰዎችም ሞርፊን፣ ትራማዶል፣ ፔቲዲን እና ኮዴይንን ጨምሮ ኦፒኦይድ የተባለውን መድኃኒት በመርፌ መልክ ይወስዳሉ።

በታኅሣሥ ወር መጀመሪያ ላይ ፖሊስ በሐኪም ትዕዛዝ ብቻ የሚሸጡ መድኃኒቶችን በሞቃዲሹ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ይዟል። ከእነዚህ መድኃኒቶች ውስጥ አብዛኞቹ ኦፒኦይድ ነው። መድኃኒቶቹን ወደ አገር ውስጥ ያስገቡ አስመጪዎችንም ፖሊስ በቁጥጥሩ ሥር አውሏል።

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ በሞቃዲሹ የሚገኝ ዶክተር እንደሚለው እንክብሎች እና በመርፌ የሚወሰዱ መድኃኒቶች በወጣት ሴቶች እና ልጃገረዶች ዘንድ የተለመዱ ናቸው።

“አብዛኞቹ መድኃኒቶች ሱስ የሚያስይዙ ሲሆኑ፣ ያለ ሐኪም ትዕዛዝ በከተማዋ በሚገኙ መድኃኒት ቤቶች ይገኛሉ” ይላል።

መኪና ውስጥ መተኛት ጀመርኩ

ሌላኛው በወጣት ሴቶች ዘንድ ታዋቂ የሆነው ዕፅ 'ታቡ' በመባል የሚታወቅ የሚታኘክ ትንባሆ ዓይነት ዕፅ ነው።

የ23 ዓመቷ አሚኖ አብዲ ባለፉት አምስት ዓመታት ዕጽ ተጠቅማለች። በሶማሊያ ሴቶች ሱሰኛ መሆናቸው እንደ ነውር የሚቆጠር ቢሆንም ዝምታውን ለመስበር ስትል ለቢቢሲ ስለ ጉዳዩ በግልጽ ለማስረዳት ወስናለች።

አሚኖ 'ታቡ' መቃም የጀመረችው አብራቸው ትኖር ከነበረው ሴቶች ጋር መሆኑን ትናገራለች።

“በጣም ተፅዕኖ ያደርሱብኝ ነበር። ከዚያም የትምባሆ ሱሰኛ ሆንኩ። ከዚያም አደገኛ እና ከባድ የሆኑ በተለይም በመርፌ የሚወሰዱ በአብዛኛው ትራማዶል እና ፔቲዲን መድኃኒቶችን መጠቀም ጀመርኩ። በተለይም የሚወጉ መድኃኒቶችን” ትላለች አሚኖ።

አሚኖ ከባለቤቷ ጋር አለመግባባት ከተፈጠረ በኋላ የምትወስደው መድኃኒት እንደጨመረ ትናገራለች። አሁን ላይ ከባለቤቷ ጋር ተለያይተዋል። ከሴት ልጇ ጋር ነው አብራ የምትኖረው።

መድሃኒት

የፎቶው ባለመብት, FATHI MOHAMED AHMED

የምስሉ መግለጫ, ሶማሊያ ውስጥ ከሱስ የሚወጡ ሰዎችን የሚረዳ የማገገሚያ ማዕከላት የሉም።

“ሱሰኛ እንድሆን ያደረገኝ የቀድሞ ፍቅረኛዬ ነው። ኃይለኛ ሱስ ነበር የነበረብኝ። አዕምሮዬን እስከምስት ድረስ። መኪና ውስጥ እና መንገድ ላይ መተኛት ጀመርኩ” ትላለች አሚኖ ያሳለፈችውን ከባድ ጊዜ ስታስታውስ።

አሚኖ ከገባችበት ሱስ መላቀቅ ትፈልጋለች። ነገር ግን በሶማሊያ የተሟሉ የማገገሚያ ማዕከላት ስለሌሉ አስቸጋሪ ሆኖባታል።

እሷ እንደምትለው ሁሉንም ሱስ በአንድ ጊዜ ማቆም የማይቻል ነው። በመርፌ የምትወስደውን ኦፒኦይድ መድኃኒት መቀነስ የቻለች ቢሆንም አሁንም ትምባሆ ትቅማለች፣ ሺሻም ታጨሳለች።

ወላጆች በተለይም እናቶች እየጨመረ የመጣውና ሴት ልጆቻቸው እየገቡበት ባለው ሱስ ክፉኛ ተጨንቀዋል።

ካዲጆ አዳን የ14 ዓመት ሴት ልጇ ከተለመደው የወጣ ባህርይ ስታሳይ ታዝባታለች። “ባልተለመደ ሰዓት ትተኛለች። ወጣ ያለ ባህርይም ታሳያለች” ትላለች።

“አንድ ቀን ቦርሳ ውስጥ ትራማዶል ክኒን እና የሚቃም ትንባሆ አገኘሁ። ጠየቅኳት። እርሷም በጓደኞቿ ግፊት መድኃኒት መውሰድ መጀመሯን ነገረችኝ” ትላለች ካዲጆ።

ጎዳና ላይ ያሉ ሕጻናት አደጋ ላይ ናቸው

ሶማሊያ ባለፉት አርባ ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ እንዲሁም ለሦስት አስርታት ከቆየ ግጭት ለመላቀቅ እየታገለች ቢሆንም፣ ከዕፅ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ቀርቶ መሠረታዊ የሆኑ የሰው ልጅ ፍላጎቶችን ለማሟላት በቂ አቅም የላትም።

ጥቂት አነስተኛ ድርጅቶች ስለዕፆቹ እና መድኃኒቶቹ አደገኛነት ግንዛቤ በመፍጠር ክፍተቱን ለመሙላት እየሞከሩ ነው።

ዘ ግሪን ክረሰንት ሶሳይቲ የተባለው ድርጅት ቁማርን፣ ጌሞችን እና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ጨምሮ ስለተለያዩ ሱሶች ለማስጠንቀቅ ትምህርት ቤቶችን እና ዩኒቨርሲቲዎችን ይጎበኛሉ።

ሲራድ ሞሐመድ ኑር በወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ስለሱስ የሚሰራው ማማ ኡጋሶ ፋውንዴሽንን ይመራል።

“ወጣቶች ዕፅ እንዳይወስዱ ግንዛቤ ለመፍጠር የተቻለንን እየሰራን ነው” ይላል።

ከዚህም በተጨማሪ ሲራድ፣ “መንግሥት አንድ እርምጃ እንዲወስድ እየሰራን ነው። ይህ ግን በቂ አይደለም። ጉዳዩ ከቁጥጥር ውጭ ሳይወጣ ወሳኝ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል” ብሏል።

ጫት የሚሸጡ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP

እንደ ሴቶች እና ሰብዓዊ መብቶች ልማት ሚኒስቴር ከሆነ ከ40 በመቶ በላይ የሚሆኑ ጎዳና ላይ ያሉ ሕጻናት ዕፅ ይወስዳሉ።

አንድ አምስተኛ የሆኑት ጎዳና ላይ ያሉ ሕጻናት ሴቶች ናቸው። ከእነዚህ መካከል 10 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከስድስት ዓመት በታች ናቸው። የተወሰኑት ከሦስት ዓመት ያንሳሉ።

ምንም እንኳን ጫት፣ ማስቲሽ እና ትንባሆ መጠቀም በጎዳና ላይ ባሉ ሕጻናት ዘንድ የተለመዱ ቢሆኑም በሚኒስቴሩ በተሰራው ጥናት መሠረት ግን 10 በመቶ የሚሆኑት ኦፒኦይድ እና 17 በመቶ የሚጠጉት የእንቅልፍ መድኃኒት ይወስዳሉ።

በሱስ የሚጠመዱ ወጣቶች ቁጥርም መጨመርም በሴቶች እና በልጃገረዶች ላይ የሚፈፀም ጥቃትን ጨምሮ ሌሎች ወንጀሎች እንዲበራከቱ ምክንያት ሆኗል።

እንደ የጥናት እና ምርምር ተቋሙ ሶማሊ ፐብሊክ አጀንዳ ከሆነ ሱስ በከተማዋ መንገዶች ላይ “ሲያል ዌሮ” የሚባሉ በሞቃዲሾ ሽብር የሚፈጥሩ አደገኛ ወንበዴዎች እንዲፈጠርም አድርጓል።

ሴቶች ላይ ጥቃት ለመፈፀምም እየተጠቀሙበት ነው። በደቡብ ምዕራቧ ከተማ ባይዶዋ አንድት ሴት ኦፒኦይድ መድኃኒት ከተሰጣት በኋላ እንደተደፈረች ተሰምቷል።

ከዚህም ባሻገር በኤችአይቪ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ዝቅተኛ በሆነባት ሶማሊያ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር ይጨምራል የሚል ስጋት አለ።

በሶማሊያ ጤና ሚኒስቴር የኤችአይቪ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ የሆኑት ዶክተር ሳዲያ አብዲሳማድ አብዱላሂ “ዕፅ በተለይም ኦፒኦይድን በመርፌ የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱ፣ በቫይረሱ የመያዝ አደጋን እየጨመረ ነው” ብለዋል።

በመድኃኒት ሻጮች ላይ እርምጃ

የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት የኦፒኦይድ መድኃኒት ችግርን ለማስወገድ ኢላማ መደረግ ያለበት መድኃኒት ሻጮች ላይ ነው ይላሉ። ፖሊስም በእነርሱ ላይ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል።

ስሙን መግለፅ ያልፈለገ መድኃኒት ሻጭ ግን እርሱ እና ባልደረቦቹ ፖሊስ እየወሰደ ባለው እርምጃ ደስተኛ እንዳልሆኑ ይናገራል።

“በሞቃዲሹ ለዓመታት መድኃኒት ቤት እያስተዳደርኩ ነው። ለወጣቶች መድኃኒት መሸጥ በጣም ቀላል ነበር። ምክንያቱም መድኃኒቶቹ በእነርሱ ላይ ስለሚያደርሰው ተፅዕኖ የሚያውቅ አልነበረም። በመሆኑም ለማንኛውም ሰው እየሸጥን ጥሩ ገንዘብ እናገኝ ነበር” ይላል።

“አሁን ላይ ወላጆች ከፖሊስ ጋር እየሰሩ ነው። ፖሊስ ቁጥጥር ማድረግ፣ አንዳንዴም እኛን ማሰር ጀምሯል። አሁን ላይ መድኃኒቶችን ለወጣቶች መሸጥ እንፈራለን። በመሆኑም ገቢያችንን እያጣን ነው” ይላል።

ሴቶች ስለሚጠቀሙት መድኃኒት አሚኖ አብዲ እና እናት ካዲጆ አዳን ጉዳዩን ወደ አደባባይ ይዘው በመውጣት አንድ እርምጃ ተራምደዋል።

የፖሊስ ቁጥጥር እንዲሁም መድኃኒቶች እና ዕጾች ላይ ግንዛቤ መፍጠር ችግሩን ለማቃለል የሚረዳ ቢሆንም ይበልጥ ትኩረት ካልተሰጠው ግን ችግሩ በቅርብ ጊዜ ማስወገድ አይቻልም።