እስራኤል በጋዛ የመንግሥታቱ ድርጅት ትምህርት ቤት ላይ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 35 ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በማዕከላዊ ጋዛ በሚገኝ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች በተጠለሉበት አንድ የመንግሥታቱ ድርጅት ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ የእስራኤል የአየር ጥቃት ቢያንስ 35 ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።
በስፍራው የነበሩ ጋዜጠኞች ለቢቢሲ እንደተናገሩት አንድ የጦር አውሮፕላን ኑሴራት ውስጥ በሚገኝ ተፈናቃዮች በተጠለሉበት ትምህርት ቤት ህንጻ የመጨረሻ ፎቅ ላይ ሁለት ሚሳኤል ተኩሷል። ከስፍራው የወጡ ቪዲዮዎች የደረሰውን ውድመት እና የበርካታ ሰዎችን አስከሬኖች አሳይተዋል።
የእስራኤል ጦር “ኢላማ የለየውን ጥቃት የፈጸመው” በትምህርት ቤቱ ውስጥ በሚገኝ “የሐማስ ይዞታ ላይ” መሆኑን እና ከተገደሉት ከ20 እስከ 30 ከሚደርሱ ሰዎች ውስጥ አብዛኞቹ የቡድኑ ተዋጊዎች ናቸው ብሏል።
በሐማስ የሚመራው የጋዛ አስተዳደር የመገናኛ ብዙኃን ጽህፈት የእስራኤልን የጥቃት ምክንያት ውድቅ በማድረግ ጦሯ “አሰቃቂ ጭፍጨፋ” ፈጽሟል ሲል ከሷል።
ጥቃት የተፈጸመበትን ትምህርት ቤት የሚያስተዳድረው የተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም ስደተኞች ድርጅት ኃላፊ ክስተቱን “ዘግናኛ” በማለት ገልጸው፤ በመጠለያው ውስጥ የታጣቁ ቡድኖች ነበሩ የሚለውን ክስ “አስደንጋጭ” ብለውታል።
በጥቃቱ የሞቱ እና የቆሰሉ ሰዎች እስራኤል እያካሄደችው ባለው ወታደራዊ ዘመቻ በተፈናቃዮች ወደ ተጨናነቀው በአቅራቢያ በሚገኘው ዴር አል ባላህ ከተማ ውስጥ ወዳለው የአል አቅሳ ሰማዕታት ሆስፒታል ተወስደዋል።
በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የተለቀቁ ቪዲዮዎች የወደሙ የመማሪያ ክፍሎች እና በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎች አስክሬኖች ታይተዋል።
በአንድ ቪዲዮ ላይ በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባት እና ድምጿን ከፍ አድርጋ የምትናገር ሴት “ጦርነት ይበቃል! ብዙ ጊዜ ተፈናቅለናል። ልጆቻችንን በተኙበት ገድለዋቸዋል” ስትል ትደመጣለች።
የሐማስ የሚዲያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢስማኤል አል ታሃዋብታ እስራኤል በመንግሥታቱ ድርጅት ውስጥ በሚገኘው ትምህርት ቤት የሐሀማስ መደበቂያ ይገኛል ማለቷን ውድቅ አድርገዋል።
ኃላፊው “የፈጠራ ወሬ” ሲሉ ያጣጣሉት ሲሆን በተፈናቀሉ በርካታ ሰዎች ላይ የተፈጸመ “አረመኔያዊ ድርጊት” ብለውታል።
የእስራኤል ጦር በመንግሥታቱ ድርጅት ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት “ተሸሽጎ” በነበረ የሐማስ አባላት መሸሸጊያ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።
ጨምሮም በመስከረም 26/2016 በተጸመው “የአሸባሪዎች” ጥቃት ላይ ተሳትፎ የነበራቸውን የሐማስ እና የኢስላሚክ ጂሃድ አባላትን በፈጸመው ጥቃት “ማስወገዱን” ገልጿል።
የአስራኤል ጦር ሲቪል ሰዎች የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ቀደም ብሎ የጥንቃቄ እርምጃ መወሰዱንም ገልጿል።
ከዚህ ጥቃት ቀደም ብሎም የእስራኤል ጦር አደረኩት ባለው “ዘመቻ” በማዕከላዊ ጋዛ ሁለት ቦታዎች ላይ በርካታ ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተነግሯል።
ትላንት ረቡዕ ጠዋት የእስራኤል ጦር ባወጣው መግለጫ በአየር ኃይል ታግዞ በጀመረው ወታደራዊ ዘመቻ “አሸባሪዎችን እና የአሸባሪዎችን መሠረተ ልማቶችን በምድር ላይ እና ከምድር ስር” እያጠቃ እንደሆነ ገልጿል።
በዚህ ዘመቻ ከፍተኛ የቦምብ ድብደባ እየተፈጸመ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ሕጻናት እና ሴቶች የሆኑ ቢያንስ 70 ሰዎች መገደላቸውን አንድ የእርዳታ ድርጅት አስታውቋል።












