በወልዲያ ከተማ የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠሩ ሦስት የቦምብ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተነገረ

ወልዲያ ከተማ በከፊል

የፎቶው ባለመብት, WOLDIA COM.

*በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ በዚህ ሳምንት ብቻ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን እና ተቋምን ዒላማ ያደረጉ ሦስት የቦምብ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ጥቃቶቹ በዞኑ አስተዳደር ጽህፈት ቤት እና በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች መኖሪያ ቤት ላይ እንደተፈጸሙ አራት ነዋሪዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በከተማዋ የተለያዩ ቦታዎች በሰዓታት ልዩነት ተፈጽመዋል በተባሉት ሦስቱም ጥቃቶች የሰዎች ሕይወት እንዳላለፈ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የመጀመሪያው ጥቃት የሰሜን ወሎ ዞን ብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊ ሙጋድ በተባለ ሰፈር ተከራይተው በሚኖርበት ቤት ላይ እንደተፈጸመባቸው የተናገሩት ነዋሪዎች፤ በጥቃቱ ከንብረት ጉዳት ውጪ በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም።

ግንቦት 25/2016 ዓ.ም. እሁድ ምሽት ላይ ተፈጸመ በተባለው ጥቃት የገዢው ፓርቲ ኃላፊ ላይም ሆነ በቤተሰባቸው ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ ሁለት ነዋሪዎች ሰዎች ተናግረዋል።

ሌላ የአካባቢው ነዋሪ ግን በጥቃቱ የብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊው ሳይጎዱ አልቀረም ያሉ ሲሆን፤ ጥቃቱን ተከትሎ በአካባቢው የነዋሪዎች እንቅስቃሴ ታግዶ እንደነበር ገልጸዋል።

“ባጃጅ ወደ ጉባ ላፍቶ [ሰፈር] መሄድ አይችልም ነበር፤ ለአካባቢው ለቀናት ተዘግቶ ቆይቷል። ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ነው የተከፈተው” ሲሉ ከጥቃቱ በኋላ ስለነበረው ሁኔታ አስረድተዋል።

ባለሥልጣኑ ላይ የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን የገለጹት ነዋሪው፣ ከቀናት በፊት ጎማጣ በተባለ ሰፈር በሚገኘው የጽ/ቤት ኃላፊው ዋናው መኖሪያ ቤታቸው ሌላ ጥቃት ተፈጽሞ እንደነበር በከተማዋ የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑ አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ሰኞ ግንቦት 26/2016 ዓ.ም. ንጋት 11፡00 አካባቢ ላይ ደግሞ የወልዲያ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ኃላፊ ናቸው የተባሉ ኃላፊ መኖሪያ ቤት ላይም ማንነታቸው ባልተለዩ ሰዎች የቦምብ ጥቃት መፈጸሙን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

አንድ የወልዲያ ነዋሪ በዚህ ጥቃት ንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰ ተናግረው፤ “ሁለት ሠዎች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል” ብለዋል። የቆሰሉት ሠዎች ኃላፊው እና ቤተሰቦቻቸው ሳይሆኑ በአካባቢው የነበሩ ጎረቤቶች መሆናቸውን አመልክተዋል።

ይህንን ክስተት በከተማዋ ውስጥ ማጋጠሙን ለቢቢሲ ሌላ የከተማዋ ነዋሪ፤ ሁለቱ ሰዎች ህክምና እርዳታ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ግንቦት 26/2016 ዓ.ም. ሰኞ ምሽት 2፡00 ሰዓት አካባቢ ደግሞ መብራት ኃይል ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በሚገኘው የዞኑ አስተዳደር ጽ/ቤት ቅጥር ግቢ ላይም የቦምብ ጥቃት እንደደረሰ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በጥቃቱ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ የተናገሩ አንድ የወልዲያ ነዋሪ፤ ንብረትነታቸው የመንግሥት የሆኑ ተሽከርካሪዎች ላይ ግን ጉዳት ደርሶ እንደተመለከቱ ገልጸዋል።

“. . . እኔ እንኳ የቆጠርኳቸው ስድስት ሰባት በቦምብ የተበሳሱ መኪኖች አይቻለሁ። ከመኪኖች ባለፈ በሰው ወይም በሕንጻው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም” ብለዋል።

ስለ ጥቃቱ የተናገሩ ሌላ ነዋሪ በጥቃቱ በስፍራው የነበሩ ሦስት የዞኑ አስተዳደር ተሽከርካሪዎች “ጋይተዋል” ብለዋል።

ጥቃቶቹ ሲፈጸሙ የፍንዳታ ድምጽ መስማታቸውን የተናገሩ ሌላ ነዋሪ፤ በጽ/ቤቱ ከፍተኛ የመንግሥት እና የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊዎች ስብሰባ ላይ ነበሩ ብለዋል።

ቢቢሲ ስለ ጥቃቱ እና ስለደረሰ ጉዳት ከከተማው ከንቲባ እና ፖሊስ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ካለፈው ሳምንት መገባደጃ ጀምሮ በወልዲያ ከተማ “ዘላቂ ሰላምን በማጽናት እግር መትከል” በሚል መሪ ቃል የክልሉ የብልጽና ፓርቲ አመራሮች እና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ስለማካሄዳቸው የዞኑ መንግሥት ኮሚኒኬሽን በማኅበራዊ ገጹ አስታውቋል።

የቦምብ ጥቃቶቹን ማን እንደፈጸማቸው በቢቢሲ የተጠየቁት ነዋሪዎች፤ “ይሄ አካል ነው” ለማለት እንደሚቸገሩ ተናግረዋል።

ሆኖም በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው ፋኖ ሊሆን እንደሚችል ግን ነዋሪዎቹ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

“ጥቃቱን እስካሁን ኃላፊነት ወስዶ እኔ ነኝ ያለ የለም። ነገር ገን በከተማዋ ዙሪያ የሚንቀሳቀስ [የፋኖ ኃይል] አለ። ሰው ሊሆን ይችላል ብሎ እገመተ ያለው እሱን [ፋኖን] ነው” ብለዋል አንድ ነዋሪ።

ሌላ ነዋሪ ደግሞ ጥቃቶቹን ያደረሰው ይሄ አካል ነው ለማለት “ተጨባጭ ነገር የለም” ሲሉ “ግለሰቦችም” አድርሰውት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ሰሞን በከተማው ውስጥ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭት እንዳልነበር የተናገሩት ነዋሪዎች፤ ነገር ግን በከተማዋ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች ያዝ ለቀቅ የሚሉ ተኩስ ልውውጦች እንደነበሩ ጠቁመዋል።

በወልዲያ ከተማ የቦምብ ጥቃቶች በተደጋጋሚ እንደሚፈጸሙ ነዋሪዎች የተናገሩ ሲሆን፤ ጥቃቶቹ የመንግሥት የሥራ እና የፀጥታ ኃላፊዎችን ዒላማ ያደርጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንትም መቀመጫው ወልዲያ በሆነው የጉባ ላፍቶ ወረዳ አስተዳደር ጽ/ቤት እና በከተማው አንድ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ተመሳሳይ ጥቃቶች እንደተፈጸሙ ነዋሪዎች አስታውሰዋል።

“አሁን በተከታታይ አዘውትሮ እየደረሰ ነው ያለው። በየሳምንቱ ወይም በየአምስት ቀን፤ በየአራት ቀን [ልዩነት] እንደዚህ ዓይነት ጥቃት ይደርሳል” ሲሉ አንድ የከተማው ነዋሪ የቦምብ ጥቃት እየተደጋገመ ተናግረዋል።

የቦምብ ጥቃቶቹን ተከትሎ በከተማዋ ከባድ መሳሪያ የታጠቁ ተሽከርካሪዎች ሲዞሩ (ፓትሮል) እንደነበር የተናገሩት ነዋሪዎች በፀጥታ ኃይሎች የጅምላ እስሮች እንደነበሩም ገልጸዋል።

በከተማዋ አሁን ላይ ትራንስፖርትን ጨምሮ መደበኛ እንቅስቃሴዎች እንዳሉም ተናግረዋል።

አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበው በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በአማራ ክልል የሚካሄደው ግጭት የቀጠለ ሲሆን፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የአካባቢ አስተዳዳሪዎች በታጣቂዎቹ በተደጋጋሚ ዒላማ ሲደረጉ ቆይተዋል።

___

*ለዚህ ዘገባ ቢቢሲ ያናገራቸው የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ አልፈቀዱም።