የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶሃን የአደጋ ምላሽ በመስጠት ረገድ ክፍተት እንደነበረ አመኑ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቱርኩ ፕሬዝዳንት ራሲብ ጣይብ ኤርዶሃን በአገራቸው ያጋጠመውን ርዕደ መሬት ተከትሎ የተሰጠው ምላሽ ክፍተት እንደነበረበት አመኑ።
ኤርዶሃን ክፍተት እንደነበረ ቢያምኑም እንዲህ ዓይነት መጠነ ሰፊ አደጋ ይኖራል ብሎ መዘጋጀት አስቸጋሪ ነው ሲሉ መንግሥታቸውን ተከላክለዋል።
በሁለቱ ርዕደ መሬቶች የሶሪያን ጨምሮ የሟቾች ቁጥር 15ሺህ አልፏል።
ተቺዎች እንደሚሉት የአደጋ ምላሹ በጣም ቀርፋፋ ነበር፤ መንግሥትም በቂ ዝግጅት አልነበረውም።
ኤርዶሃን መንግሥታቸው የነበረበትን ክፍተት ካስረዱ በኋላ አሁን ግን ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ እንደማይወጡ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
በቱርክ የዋንኛው ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ከማል ኩሉቺተሮሉ በዚህ አይስማሙም።
“ለዚህ ቀወስ አንድ ሰው ተጠያቂ ይሆናል ካልን ያ ሰው ኤርዶሃን ነው” ሲሉ ጠንከር ያለ ትችት ሰንዝረዋል።
ኤርዶሃን በበኩላቸው ይህን የከማል ኩሉቺተሮሉን ትችት እንደማይቀበሉት ነገር ግን ከእንዲህ ዓይነት አደጋዎች በኋላ አንድነት እንጂ የፖለቲካ ልዩነቶች ደግ እንዳይደሉ ተናግረዋል።
ይሁንና የሕዝብ ስቃይን ተገን አድርገው የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ አሉታዊ አስተያየት የሚሰጡ ሰዎችን እንደማይታገሱም አስጠንቀቀዋል።
በሺህ የሚቆጠሩ ከርዕደ መሬቱ አደጋ የተረፉ ዜጎች ለሦስተኛ ሌሊት ከባድ ቅዝቃዛ ባለበት ሁኔታ ጎዳና ላይ እያደሩ ነው።
ከፍርስራሹ ውስጥ ከዚህ በኋላ በሕይወት የሚኖሩ ይኖራሉ ወይ የሚለው ተስፋም እየከሰመ መጥቷል።
የዓለም ጤና ድርጅት በከፍተኛ ቅዝቃዜው የተነሳ የጤና ችግር የሚያጋጥማቸው በርካታ ከአደጋው የተረፉ ሰዎች እንደሚኖረ የተነበየ ሲሆን ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ ድጋፉን እንዲቀጥል ተማጽኗል።
በሶሪያ ሁኔታዎች ከቱርክ የከፉ ሲሆን በጦርነቱ በርካታ መሠረተ ልማቶች መውደማቸውን ተከትሎ ያለውን እርዳታም በበቂ ለማድረስ ፈተና ሆኗል።
የአውሮፓ ኅብረት ሦስት ሚሊዮን ዩሮ ገደማ ለሶሪያ የአደጋ ጊዜ ምላሽ የለገሰ ሲሆን እርዳታው በአማጺዎች ለተያዙ አካባቢዎችም በመንግሥት እጅ ላሉትም እኩል እንዲደርስ አሳስቧል።
በሶሪያ የኢድሊብ ክፍለ ግዛት ብቻ 1ሺህ 500 ሰዎች ሞተዋል።
በሶሪያው አምባገነን ባሸር አልአሳድና መንግሥታቸው በኩል የተጣለው ማዕቀብ በቂ እርዳታ ወደ አገሪቱ እንዳይደርስ ምክንያት ሆኗል።












