የኢራን ፕሬዝዳንት አገሪቱ ያጋጠማትን ድርቅ ተከትሎ "ቴህራንን ለቀን መውጣት" ሳይኖርብን አይቀርም አሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ኢራን፣ በተለይም ዋና ከተማዋ ቴህራን ታይቶ የማይታወቅ ድርቅ ማጋጠሙን ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ "ቴህራንን ለቀን መውጣት" ሳይኖርብን አይቀርም አሉ።
በኢራን የጣለው ዝናብ መጠንም እጅግ ዝቅተኛ በመሆኑ የውሃ ማጠራቀሚያዎችም ባዶ ናቸው ተብሏል። ባለሥልጣናቱ ቀውሱ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ዜጎች ውሃ እንዲቆጥቡ ተማጽነዋል።
ፕሬዝደንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በቅርቡ በቂ ዝናብ ካልጣለ በቴህራን ውሃ ማከፋፈል እንደሚጀመር ተናግረው ነበር።
ነገር ግን የውሃ እጥረቱን ለመቅረፍ በተራ ማከፋፈል ብቻ በቂ ላይሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
ፔዝሽኪያን "ማከፋፈሉ ካልሰራ ቴህራንን መልቀቅ ሊኖርብን ይችላል" ሲሉ ተናግረዋል።
የፕሬዚዳንቱ አስተያየቶች በኢራን ጋዜጦች እና በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ትችትን አስተናግደዋል። የቀድሞው የቴህራን ከንቲባ ጎላምሆሴን ካርባሺ ሀሳቡን "ቀልድ" ሲሉ አጣጥለው "ቴህራንን ለቅቆ መሄድ ምንም ትርጉም የለውም" ብለዋል።
የኢራን የሚቲዎሮሎጂ ባለስልጣናት በሚቀጥሉት 10 ቀናት ውስጥ ምንም ዝናብ እንደማይጠበቅ ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የውሃ ችግር በዋና ከተማው የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው።
በቴህራን የምትኖር አንዲት ሴት ለቢቢሲ ፐርዢያ "ለመጸዳጃ ቤት እና ለሌሎች አስፈላጊ ነገሮች የሚያገለግል የውሃ ማጠራቀሚያዎችን ለመግዛት አቅጃለሁ።
ኢራናዊው ራፐር ቫፋ አህመድፑር ደግሞ በማብሰያ ክፍል ውስጥ የሚገኝ ቧንቧን በማሳየት ምንም ዓይነት ውሃ እንደሌለ የሚገልጽ ተንቀሳቃሽ ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አጋርቷል።
"አራት ወይም አምስት ሰዓት አልፏል" በማለት " ወደ መጸዳጃ ቤት ለመሄድ የታሸገ ውሃ ገዝቻለሁ።"
ከቴህራን ዋና የውሃ ምንጮች አንዱ የሆነው የላቲያን ግድብ ሥራ አስኪያጅ ግድቡ ካለው ውሃ የመያዝ አቅም ከ10 በመቶ በታች መያዙን ተናግረዋል።
በአቅራቢያው ያለው የካራጅ ግድብ ለቴህራን እና አልቦርዝ ከተሞች ውሃ የሚያቀርብ ሲሆን በተመሳሳይ አነስተኛ ውሃ ብቻ መያዙ ተነግሯል።
"ከተወለድኩበት ጊዜ ጀምሮ ይህ ግድብ ባዶ ሆኖ አይቼው አላውቅም" ሲሉ አንድ አዛውንት የአካባቢው ነዋሪ ለኢራን መንግሥት ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
የካራጅ ግድብ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት መሀመድ አሊ ሞአለም እንዳሉት የዝናብ መጠኑ በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል።
"የዝናብ መጠን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ92 በመቶ ቀንሷል" ብለዋል።
"በግድቡ ውስጥ ያለን ስምንት በመቶው ውሃ ብቻ ነው። እና አብዛኛው ጥቅም ላይ ሊውል የማይችል እና 'የሞተ ውሃ' ተብሎ የሚታሰብ ነው።"
መንግሥት አሁን ተስፋውን በበልግ መገባደጃ ላይ ዝናብ ሊጥል ይችላል የሚል ነው።
ነገር ግን የሚትዎሮሎጂ ትንበያዎች ያንን አያሳዩም።
የኢራን የኢነርጂ ሚኒስትር አባስ አሊ አባዲ ሁኔታው በቅርቡ የውሃ አቅርቦትን እንዲቋረጥ ሊያስገድድ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
"አንዳንድ ምሽቶች የውሃውን ፍሰት ወደ ዜሮ ልንቀንስ እንችላለን" ብለዋል።
ባለሥልጣናቱ ከመጠን በላይ ውሃን የሚጠቀሙ ቤተሰቦችን እና ንግድ ቤቶችን ለመቅጣት ማቀዱን አስታውቀዋል።
የኢራን የኢነርጂ ሚኒስትር አሊ አባዲ የቴህራን የውሃ ችግር በዝናብ እጥረት ብቻ የተከሰተ አይደለም ይላሉ። በመዲናዋ ለዘመናት በቆየው የውሃ መሠረተ ልማት ምክንያት የተከሰተውን የውሃ ፍሰትን እና በቅርቡ ከእስራኤል ጋር ለ12 ቀናት የዘለቀው ጦርነትን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
በዚያ ግጭት ወቅት፣ እስራኤል ሰኔ 15 ቀን በሰሜናዊ ቴህራን የታጅሪሽ ሰፈር ላይ ዒላማ አድርጋለች። ከዚያ በኋላ በአካባቢው ከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅ መከሰታቸውን የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ወጥተዋል።
በጥቃቱ ማግስት የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት የኢራንን ጦር "ማዘዣ ማዕከላት" ላይ ማነጣጠሩን አስታውቋል።
ነገር ግን ይህ የውሃ እጥረት ቀውስ ከዋና ከተማው የሰፋ ነው።
የኢራን ብሔራዊ የአየር ንብረት እና ድርቅ ቀውስ አስተዳደር ማዕከል ኃላፊ አህመድ ቫዚፈህ ከቴህራን በተጨማሪ በሌሎች በርካታ ግዛቶች ውስጥ ያሉ ግድቦች "አስጊ ሁኔታ" ውስጥ እንደሚገኙ አስጠንቅቀዋል።
በግድቦቹ ውስጥ ያለው የውሃ መጠን በመቶኛ ሲሰላ በነጠላ አሃዝ የሚቀመጥ ነው።
በኢራን ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ማሽሃድ ባለስልጣናትም እጥረት መከሰቱን እየገለፁ ነው።















