የባሕር በር ባላቸው አገራት እየተስፋፋ የመጣው የባሕር ውሃን አጣርቶ የመጠቀም አማራጭ

የተጣራ ጨዋማ ውሃ እና ከእርሱ የተገኘ ተረፈ ምርትን የያዙ ወንዶች

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እአአ በ2022 የፈረንሣይ አነስተኛ ከተሞች ከንቲባዎች ጨዋማ ውሃ ማጣሪያዎች ፊት ለፊት ቆመው

ከጥቂት ዓመታት በፊት መሐመድ ያቆብ ባሎክ እና ቤተሰቦቹ ወንዞች እና የውሃ ጉድጓዶች በመድረቃቸው የተነሳ በደቡብ ፓኪስታን የሚገኘውን ቤታቸውን ጣጥለው ለመሄድ ተገድደዋል።

የሚጠጡት ውሃ ማግኘት አስቸጋሪ ሆነባቸው፤ ሰብሎች በውሃ እጦት በተደጋጋሚ ከሰሙ።

አርሶ አደሩ ባሎክ "ከሕንድ እና ከቻይና የእኛን ሩዝ፣ ስንዴ እና አትክልቶች ለመግዛት ሰዎች ይመጡ ነበር" ሲል 'ደጉን ጊዜ' ያስታውሳል።

"ነገር ግን ከ50,000 ሄክታር በላይ መሬታችን የማይታረስ ባድማ ሆነ።"

ብዙ ሰዎች የአያት ቅድመ አያቶቻቸውን መሬት ጥለው ሄደዋል። እና ባሎክ መንግሥት የውሃ ማጣሪያ ጣቢያ እስኪገነባ እና ከአረብ ባሕር የመጠጥ ውሃ ማግኘት እስኪቻል ድረስ ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ ቋፍ ላይ ደርሶ ነበር።

በአካባቢው የቀሩት አብዛኞቹ አርሶ አደሮች አሁን አቅማቸው የፈቀደውን እያደረጉ በጨዋማ ውሃ በተሞሉ የመስኖ ቦዮች ውስጥ ትንንሽ ዓሳዎችን በመሰብሰብ ኑሮአቸውን ይደጉማሉ።

የዓለም ሙቀት መጨመር የንፁህ ውሃ እጥረት እንዲፈጠር በማድረጉ በዓለም ላይ ካሉ በርካታ አገራት መካከል ጨዋማ የባሕር ውሃን በማጣራት ፓኪስታን አንዷ ናት።

በአብዛኛው በመካከለኛው ምሥራቅ እና በረሃማ አገራት የሚገኙ ሀብታሞች ብቻ ይጠቀሙት የነበረውን ይህንን ጨዋማ የባሐር ውሃ የማጣራት ዘዴ አሁን የዓለም ሙቀት መጨመርን ተከትሎ ሌሎችም ተቀላቅለውታል።

ግሎባል ዋተር ኢንተለጀንስ (GWI) ከአምስት አገራት መካከል አራቱ ጨዋማ የሆነን የባሕር ውሃ በማጣራት ለመጠጥ እና ለሌላ አገልግሎቶች ያውላሉ። የእነዚህ አገራት ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እየሄደ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኩዌት፣ ኦማን እና ሳዑዲ አረቢያ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የውሃ አቅርቦት የሚመጣው ከጨዋማ ባሕር ወይም ከጥልቅ የከርሰ ምድር ውሃ አቅርቦት ነው።

በቅርቡ እስራኤል እና አሜሪካ የኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ ባደረሱት ጥቃት የኳታር ባለሥልጣናት አሁን ለአገራቸው፣ ለተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እና ኩዌት ዋና የውሃ ምንጭ የሆነው የፋርስ ባሕረ ሰላጤ የመበከል ስጋት እንዳጋጠመው ገልፀው ነበር።

በኦማን ውስጥ የሚገኝ ጨዋማ የባህር ውሃ ማጣሪያ

የፎቶው ባለመብት, Veolia

የምስሉ መግለጫ, የውሃ አቅራቢ ኩባንያዎች ባለፉት ዓመታት ትላልቅ ጨዋማ ውሃ ማጣሪያዎችን ለመገንባት የሚያስፈልገው ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን ይናገራሉ

ለምን በቂ ንጹህ ውሃ የለም?

የዓለማችን ሁለት ሦስተኛው አካል የተሸፈነው በውሃ ነው።

ሆኖም ከአጠቃላዩ የምድራችን ውሃ 0.5 በመቶው ብቻ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ንጹህ ውሃ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል። እንዲሁም ይህ ትንሽ መጠን ያለው ጠቃሚ የውሃ ይዞታ በከፍተኛ ሙቀት እና ድርቅ ምክንያት በፍጥነት እየቀነሰ መሆኑን አስታውቋል።

በአውሮፓውያኑ 2023 በውሃ ላይ የሚሠራው ግሎባል ኮሚሽን ኦን ዘ ኢኮኖሚክስ ኦፍ ዋተር የተባለው ተቋም ባወጣው ሪፖርት በ2030 በዓለም ላይ የ40 በመቶ የውሃ አቅርቦት እጥረት ሊኖር እንደሚችል አስጠንቅቆ፣ የዓለም ሕዝብ በ2050 ወደ 9.7 ቢሊዮን እንደሚያድግ አመልክቷል።

የውሃ ሀብት ላይ የሚታየው ብልሹ አሠራር እና ሙስና በብዙ አገራት ለተከሰተው የአጣዳፊ የውሃ እጥረት አስተዋጽኦ አድርጓል።

ውቅያኖሶች ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነውን የዓለም ውሃ ስለሚይዙ ብዙዎች እምብዛም ጥቅም ላይ ያልዋለው የባሕር ውሃን መጠቀም መፍትሄ ነው ብለው ይከራከራሉ።

ዓለም አቀፍ መስፋፋት

በዓለም ዙሪያ ከ20 ሺህ በሚበልጡ ቦታዎች ጨዋማ የባሕር ውሃን የሚያጣሩ ፋብሪካዎች ተገንበተዋል።

ይህም ከአስር ዓመት በፊት ከነበረው በእጥፍ የሚበልጥ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።

ቬዮሊያ የተሰኘው እና ጨዋማ ውሃን በማጣራት ላይ ልምድ ያለው ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት ኢስቴል ብራችሊያኖፍ "በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ጨዋማ ውሃን የማጣራት ገበያ ዕድገት በእጅጉ ይፋጠናል። ይህም በዋናነት የሚመራው በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሰሜን አፍሪካ፣ በእሲያ ፓሲፊክ እና በተወሰኑ የአውሮፓ አገራት ነው" ብለዋል።

በግሎባል ዋተር ኢንተለጀንስ (GWI) የተሰበሰበው መረጃ እንደሚያሳየው በአሁኑ ጊዜ ወደ 160 የሚጠጉ አገራት ጨዋማ የባሕር ውሃን የሚያጣሩበት ፋብሪዎች አሏቸው።

አክሎም በአማካይ 60 በመቶው የሚመረተው ውሃ ለሕዝብ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ይውላል ብሏል።

በውሃ ደኅንነት ላይ ያተኮረው የምርምር ድርጅት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ራቼል ማክዶኔል "ጨዋማ ውሃን ማጣራት ብዙ አገራት ያለባቸውን ሥር የሰደደ የውሃ እጥረት እንዲቋቋሙ እየረዳቸው ነው" ብለዋል።

"ለድርቅ ተጋላጭ ለሆኑ አካባቢዎች ሁሉ ጨዋማ ውሃን ማጣራት ምላሽ ባይሆንም፤ በርካታ አገራት ድርቅን እና የፍላጎት መጨመርን በመጋፈጥ የውሃ ደኅንነታቸውን እንዲያሳድጉ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል" ሲሉም ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ።

ሥዕል

ግሎባል ዋተር ኢንተለጀንስ ዘርፉ በየዓመቱ ከ10 በመቶ በላይ እያደገ እንደሆነ ይገምታል።

ባለፉት15 ዓመታት ውስጥ በሁሉም የዓለም ክልሎች ከ60 በላይ አገራት ጨዋማ ከሆነ የባሕር ውሃ ከፍተኛ መጠን ያለው የመጠጥ ውሃ እያገኙ ነው።

ይህ የሚያሳየው ብዙዎቹ በእጥፍ፣ በሦስት እጥፍ እና በአራት እጥፍ ጭማሪ ሲያዩ (ለምሳሌ ሲንጋፖር 467 በመቶ) አንዳንዶቹ ከ10 እስከ 50 እጥፍ ጭማሪ አስመዝግበዋል።

ግሎባል ዋተር ኢንተለጀንስ እንዳለው ሳዑዲ አረቢያ ጨዋማ የሆነውን የባሕር ውሃ በከፍተኛ ሁኔታ ታጣራለች።

ይህም ማለት በቀን 13 ቢሊዮን ሊትር ውሃ፣ ለ5,200 የኦሊምፒክ መጠን ላላቸው የመዋኛ ገንዳዎች የሚበቃ ታጣራለች።

ባንግላዲሽ፣ ሕንድ እና ፓኪስታን ጨዋማ የባሕር ውሃን ብቻ ሳይሆን የተበከለ የከርሰ ምድር ውሃንም ጨዋማነት አጣርተው ይጠቀማሉ።

አፍጋኒስታን በሌሎች ምክንያቶች ጨዋማ የሆነውን የከርሰ ምድር ውሃ በማጣራት እየተጠቀመች ነው።

ጨዋማ ውሃን እንዴት ማጣራት ይቻላል?

ጨዋማ ውሃን ማጣራት በዋናነት በሁለት መንገዶች ይካሄዳል።

የመጀመሪያው በጣም የተለመደው እና ኃይል ቆጣቢው 'ሪቨርስ ኦስሞሲስ' ይባላል።

ጨዋማውን ውሃ ጨው እና ሌሎች ኬሚካሎችን እንዳያልፉ ወደ ሚከላከለው ልዩ ማጣሪያው በመግፋት ውሃውን የማጣራት ዘዴ ነው።

ሁለተኛው ስልት ደግሞ 'ተርማል ዲሳሊኔሽን' ይባላል። ይህ የሚሠራው ውሃው ወደ ተንነት እስኪቀየር ድረስ ማፍላት ነው። ከዚያም እንፋሎቱ ሲቀዘቅዝ ወደ ንፁህ ውሃነት ይቀየራል።

አዋጭነት

ጨዋማ ውሃን ማጣራት በተለምዶ ውድ ቴክኖሎጂ ነው።

ነገር ግን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ርካሽ ታዳሽ ኃይልን በማቅረብ እና ቅልጥፍናን በመጨመር ዋጋው ዝቅ እንዲል ተደርጓል።

ባለሙያዎች ከአውሮፓውያኑ 1970 ጀምሮ ጨዋማ የሆነን ውሃ የማጣራት ወጪ እስከ 90 በመቶ ቀንሷል ሲሉ ይናገራሉ።

በዓለም አቀፉ የውሃ አስተዳደር ተቋም የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው ጨዋማ ውሃን ማጣራትን ከፀሐይ ኃይል ጋር በማጣመር በ2040 በብዙ የባሕር ዳርቻ አካባቢዎች የበለጠ ወጪ ቆጣቢ ማድረግ ይቻላል።

ይሁን እንጂ ቬዮሊያ በቀን 500 ሚሊዮን ሊትር ውሃ የሚያመርት ትልቅ የጨዋማ ውሃን ማጣሪያ ፋብሪካ ወደ 500 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ መዋዕለ ንዋይ ያስፈልገዋል ይላል።

የተጣራ ውሃ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ማጓጓዝ ሌላው ሊታሰብበት የሚገባ ትልቅ ወጪ ነው።

"በታዳጊ አገራት ወጪዎች እንቅፋት ሆነው ይቆያሉ" ሲል በዋተር ኤይድ ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ውሃ፣ የአካባቢ ጽዳት እና የግል ንፅህና ባለሙያ የሆነው ሻኬል ሃያት ይናገራል።

ወተር ኤይድ በደቡብ እስያ ወደ 100 አነስተኛ የጨዋማ ውሃ ማጣሪያዎችን ለመገንባት እገዛ ያደረገ ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎት ድርጅት ነው።

"ለብዙዎቹ አገራት ትናንሽ እና በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ ማጣሪያዎች ጨዋማ የጉድጓድ ውሃን ወደ መጠጥ ውሃ ለመቀየር የበለጠ አዋጭ ናቸው።"

የተጣራውን ዝቃጭ የማስወገድ ጫና

ጨዋማ ውሃን በማጣራት ሂደት ውስጥ ካሉት ትላልቅ ፈተናዎች አንዱ ከተጣራ በኋላ የሚቀረውን ጨዋማ ዝቃጭ ማስወገድ ነው።

ይህንን ጨዋማ ዝቃጭ መልሶ ወደ ባሕር ማስገባት የውሃውን ጨዋማነት እና የሙቀት መጠን የበለጠ ይጨምረዋል።

እናም የባሕርን ሥነ ምኅዳር በእጅጉ የሚጎዳ ሲሆን፣ ምንም ዓይነት ሕይወት የማይኖርበት አካባቢም ይፈጥራል።

የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም "በአብዛኞቹ ጨዋማ ውሃ የማጣራት ሂደቶች ውስጥ፣ ለእያንዳንዱ ሊትር ንፁህ የመጠጥ ውሃ፣ 1.5 ሊትር በክሎሪን እና በመዳብ የተበከለ ፈሳሽ ይፈጠራል" ብሏል።

"በአግባቡ ካልሟሟ እና ካልተወገደ የባሕር ዳርቻዎችን እና የባሕር ውስጥ ሥነ ምኅዳሮችን ሊያበላሽ የሚችል መርዛማ ዝቃጭ ሊፈጥር ይችላል።"

ሳይንቲስቶች ግብፅን እና ሳዑዲ አረቢያን በሚለያየው በአቃባ ባሕረ ሰላጤ ላይ በሚገኙ ኮራል እና አልጌዎች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖን ተመልክተዋል።

ነገር ግን ያ የሥነ ምኅዳር ዋጋ በፍጥነት እየሞቀች እና እየተጠማች ባለች ዓለም ውስጥ ለሚኖሩ ሁሉም አገራት እየጨመረ የመጣውን ጨዋማ ውሃን የማጣራት ማዕበል የሚገታ አይመስልም።