ቻይና መገንባት የጀመረችው የዓለማችን ትልቁ ግድብ በሕንድ ላይ የፈጠረው ስጋት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቻይና ባለሥልጣናት ሕንድን እና ባንግላዲሽን ስጋት ላይ የጣለውን በዓለም ትልቁን የውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ በቲቤት ግዛት መገንባት ጀምረዋል።
የቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪያንግ ቅዳሜ ዕለት በያርንግ ቻንግፖ ወንዝ ላይ ግንባታው መጀመሩን በማስመልከት በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ወንዙ በቲቤት ምድር ውስጥ ይፈስሳል።
ፕሮጀክቱ በወንዙ ዳርቻ የሚኖሩ በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሕንዳውያን እና ባንግላዲሽያውያን፣ እንዲሁም በቲቤት ተወላጆች ላይ እና በአካበቢው ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽዕኖን በመጥቀስ ትችቶች እየቀረቡበት ነው።
ቤይጂንግ በበኩሏ የግድቡ ግንባታ 167 ቢሊዮን ዶላር እንደሚፈጅ እና ለሥነ ምኅዳር ጥበቃ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ለአካባቢውም ብልጽግናን እንደሚያመጣ ገልጻለች።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ፣ ሞቱኦ የውሃ ኃይል ማመንጫ ተብሎ የተሰየመው ይህ ግድብ ከሦስቱ ሸለቆዎች ግድብ በሦስት እጥፍ ተጨማሪ ኃይል በማመንጨት የዓለማችን ግዙፍ ግድብ ይሆናል።
ባለሙያዎች እና ባለሥልጣናት አዲሱ ግድብ ወደ ሕንድ እንዲሁም ወደ ባንግላዲሽ ወንዞች የሚወስደውን ድንበር ተሻጋሪውን ያርሎንግ ቻንግፖን ቻይና እንድትቆጣጠር ወይም አቅጣጫውን እንድትቀይር ያስችላታል ሲሉ ስጋታቸውን ጠቁመዋል።
በ2020 መቀመጫውን አውስትራሊያ ያደረገው 'ላውይ ኢንስቲትዩት' ያወጣው ሪፖርት "እነዚህን ወንዞች መቆጣጠር ቻይናን የሕንድን ኢኮኖሚ ፈጥርቆ በመያዝ ውጤታማ እንድትሆን አድርጓታል" ብሏል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የባንግላዲሽ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ፔማ ካንዱ ከፒቲአይ የዜና ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ግድቡ ሲጠናቀቅ ሲያንግ እና ብራህማፑትራ የተባሉት ወንዞች "በከፍተኛ ደረጃ ሊደርቁ ይችላሉ" ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
አክለውም ግድቡ "በጎሳዎቻችን እና በኑሯችን ላይ የኅልውና ስጋት ይፈጥራል። ቻይና ይህንን እንደ 'የውሃ ቦምብ' ልትጠቀም ስለምትችል በጣም ከባድ ነው" ብለዋል።
"ግድቡ ተገንብቶ በድንገት ውሃ ቢለቁብን የሲያንግ አካባቢ በሙሉ ይወድማል። በተለይ የአዲ ጎሳ እና መሰል ቡድኖች...ንብረታቸው፣ መሬታቸው እና በተለይም የሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል።"
በጥር ወር የሕንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለቻይና ስለ ግዙፉ ግድብ ተፅዕኖ ስጋታቸውን እንደገለፁ እና ቤይጂንግ "የታችኛው ተፋሰስ አገራት ጥቅምን እንዳትጎዳ" አሳስበዋል።
በተጨማሪም "ከታችኛው ተፋሰስ አገራት ጋር ግልጽ ምክክር ስለማድረግ አስፈላጊነት" ላይ አጽንዖት ሰጥተዋል።
ሕንድ በሲያንግ ወንዝ ላይ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ለመሥራት አቅዳለች፤ ይህም ከቻይና ግድብ በድንገት የሚለቀቅን ውሃ ለመከላከል እና በአካባቢው የሚደርስ የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችል ነው።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ለሕንድ ምላሽ ሲሰጥ ቻይና ወንዙን የመገደብ "ሕጋዊ መብት" እንዳላት እና የታችኛው ተፋሰስ ተፅዕኖዎችን ከግምት ማስገባቷን ተናግሯል።
ባንግላዲሽ እንዲሁ ለቻይና በፕሮጀክቱ ላይ ያላትን ስጋት ስትገልጽ በየካቲት ወር ለቤይጂንግ በግድቡ ላይ ተጨማሪ መረጃ የሚጠይቅ ደብዳቤ ልካለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቻይና ባለሥልጣናት ግድቡ በቲቤት ራስ ገዝ ክልል ውስጥ የሚገኘውን የውሃ ኃይል አቅም ለረዥም ጊዜ ሲመለከቱ ቆይተዋል።
የያርሎንግ ቻንግፖ፣ የቲቤት ረዥሙ ወንዝ፣ በናምቻ ባዋ ተራራ እየተጥመዘመዘ ይፈሳል።
ይህም በዓለም ላይ በጣም ጥልቅ እና ረጅሙ ነው በሚባለው ግዙፍ ሸለቆ ውስጥ ወንዙን እንዲፈስ አድርጎታል።
ወንዙ በተራራዎች መካከል ታጥፎ የሚፈስበት መንገድ "ታላቁ እጥፋት" (the Great Bend) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ከዚያ በኋላም በመቶዎች ከሚቆጠሩ ሜትሮች ከፍታ ላይ እየተምዘገዘገ ይወርዳል።
ከዚህ ቀደም የወጡ መረጃዎች ባለሥልጣናቱ የወንዙን የተወሰነ ክፍል አቅጣጫ ለማስቀየር 20 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ ዋሻዎችን በናምቻ ባርዋ ተራራ በኩል ለመቆፈር አቅደዋል።
በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የሺንዋ የሊ ኪያንግን ጉብኝት አስመልክቶ የወጣው ዘገባ እንዳመለከተው መሐንዲሶች ወንዙ በቀጥታ እንዲፈስ ለማድረግ ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ እና "ውሃን በዋሻዎች ውስጥ በማሳለፍ" አምስት የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ይገነባሉ።
በተጨማሪም ዢንዋ እንደዘገበው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቡ በዋናነት የቲቤትን የኃይል አቅርቦት ካሟላ በኋላ ከክልሉ ውጪ ላሉ አካባቢዎች ይዳረሳል።
ቻይና በምዕራብ ገጠራማ አካባቢዎች፣ የቲቤት ግዛቶች የሚገኙትን ገደላማ ሸለቆዎችን እና ግዙፍ ወንዞችን፣ ግዙፍ ግድቦች እና የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን በመገንባት በአገሪቱን ምሥራቃዊ ክፍል የሚገኙ ትልልቅ ከተሞችን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ለማሟላት አቅዳለች።
ዢ ጂንፒንግ በግላቸው "የምዕራቡን ኤሌክትሪክ ወደ ምሥራቅ መላክ" በተሰኘ ፖሊሲያቸው በኩል እየገፉ መሆኑ ተገልጿል።
የቻይና መንግሥት እና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን እነዚህን ግድቦች የገጠር ቲቤት ነዋሪዎችን ሕይወት በማሻሻል፣ ብክለትን የሚቀንስ እና ንጹህ ኃይል የሚያመነጩ አድርገው አቅርበዋል።
ነገር ግን ማኅበራዊ አንቂዎች ግድቦቹ ቤይጂንግ በቲቤት እና በመሬታቸው ላይ የምትፈጽመው ምዝበራ ማሳያ ነው ይላሉ።
ከዚህ በፊት የነበሩ ተቃውሞዎች በመንግሥት ጠንካራ እርምጃ እንዳያሰሙ ታፍነዋል።
ባለፈው ዓመት የቻይና መንግሥት በሌላ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙ የነበሩትን በመቶዎች የሚቆጠሩ የቲቤት ተወላጆችን በቁጥጥር ስር አውሏል።
በዚህም ወቅት አንዳንዶች ሲታሰሩ፣ የተደበደቡ እና የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መኖራቸውን ቢቢሲ ከምንጮቹ ማረጋገጥ ችሏል።
በብዝኃ ሕይወታቸው የሚታወቁት የቲቤት ሸለቆዎች ጎርፍ እና የመሬት መንቀጥቀጥ የሚደጋገምባቸው ሲሆኑ፣ በዚህ ክልል ውስጥ ግድቦችን መገንባት ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በተመለከተ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ስጋት ነው።















