ከ25 ዓመት በፊት ከተፈጸመው ከቱፓክ ግድያ ጋር በተያያዘ ፖሊስ በአንድ ቤት ላይ ብርበራ አካሄደ

ቱፓክ ሲገደል የ25 ዓመት ወጣት ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ቱፓክ ሲገደል የ25 ዓመት ወጣት ነበር።

የአሜሪካ ፖሊስ በኔቫዳ ግዛት ውስጥ ከ25 ዓመታት በፊት ከተፈጸመው ከአቀንቃኙ ቱፓክ ሻኩር ግድያ ጋር በተያያዘ በአንድ መኖሪያ ቤት ላይ ፍተሻ አደረገ።

ዝነኛ የራፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ የነበረው ቱፓክ በጥይት ተመትቶ የተገደለው እአአ 1996 ላይ ቢሆንም ከግድያው ጋር ተያይዞ በጥርጣሬ እንኳ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሰው የለም።

መርማሪዎች በኔቫዳ ግዛት ከላስ ቬጋስ ከተማ አቅራቢያ ቱፓክ ከተገደለበት ስፍራ አቅራቢያ ያለ መኖሪያ ቤት ላይ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ብርበራ ማድረጋቸውን ከመግለጽ ውጪ ስለፍተሻው ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በወቅቱ ዝነኛ የነበረው ራፐር ቱፓክ ሲገደል ገና የ25 ዓመት ወጣት ነበር።

የላስ ቬጋስ ፖሊስ በመኖሪያ ቤቱ ላይ ፍተሻ ማድረጉን ይፋ ባደረገበት መግለጫው ከቱፓክ ሻኩር ግድያ ጋር ተያይዞ እየተደረገ ባለው ምርመራ ፖሊስ ባለፈው ሰኞ ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም. ፍተሻ ማድረጉን ገልጾ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

ጄሰን ዮሃንሰን የተባሉ የላስ ቬጋስ ፖሊስ አባል ላስ ቬጋስ ሪቪው ጆርናል ለተባለ ጋዜጣ ሲናገሩ፣ ፖሊስ በቱፓክ የግድያ ወንጀል ዙሪያ እንደ አዲስ ምርመራ ጀምሯል ብለዋል።

“መዝገቡ ያልተዘጋ የወንጀል ምርመራ ነው። ይህን አንድ ቀን እንቀይረዋለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል የፖሊስ አባሉ።

ቱፓክ በሚለው የመድረክ ስሙ እጅግ ዝነኛ የነበረው ራፐር የመጀመሪያ አልበሙን እአአ 1991 ላይ ከለቀቀ በኋላ በስፋት ታዋቂ ሆኖ ነበር።

ካሊፎርኒያ ላቭ፣ ኦል አይዝ ኦን ሚ፣ ቼንጅስ እንዲሁም አም ኖት ማድ አት ቻ የሚሉ የሙዚቃ ሥራዎቹ ከፍተኛ ዝናን አስገኝተውለታል።

ቱፓክ ሻኩር መኪናው ውስጥ ሆኖ የትራፊክ መብራት ይዞት ሳለ ነበር አራት ጊዜ በጥይት ተመትቶ ከሳምንት በኋላ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጥር 1996 ሕይወቱ አልፏል።