ህጻን ሲሰርቅ በቢቢሲ የተጋለጠው ኬንያዊ 25 ዓመት ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, BRIAN INGANGA/ BBC
ህጻን ሊሸጥ ሲል በቢቢሲ የተጋለጠው ኬንያዊ የሆስፒታል ሠራተኛ የ25 ዓመት እስራት ተፈረደበት።
በናይሮቢው ማማ ሉሲ ኪባኪ ሆስፒታል ይሠራ የነበረው ፍሬድ ሌፓራን አንድን ወንድ ህጻን ለመሸጥ 2 ሺህ 500 ዶላር ሲቀበል ተቀርጿል።
እአአ በ2020 በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ህጻናትን በማዘዋወር፣ በቸልተኝነት እና ህጻናት ላይ ወንጀል ለመፈጸም በማሴር ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል።
ተባባሪው ሴሊና አዱንዶ በበኩሏ የስድስት ዓመት እስራት ወይም 2 ሺህ ዶላር ቅጣት ተወስኖባታል።
የአፍሪካ አይ ዘጋቢ መረጃውን ከምንጩ ካገኘ በኋላ በሆስፒታሉ ከፍተኛ ማህበራዊ ሠራተኛ በመሆን ሲያገለግል ነበረውን ሊፓራንን የቀረበው ገዢ በመምሰል ነበር።
ሌፓራን ህፃኑን ለመሸጥ ከመስማማቱ በፊት እሷ እና ባለቤቷ ለመውለድ እንዳልቻሉ የገለጸችለትን ጋዜጠኛ ስለ ሁኔታቸው አስገራሚ ጥያቄዎችን ብቻ ጠይቆ ለመሸጥ ተስማምቷል።
ሊሸጠው ያሰበው ልጅ እና ሌሎች ሁለት ልጆች ከሆስፒታል ወደ መንግሥታዊ የህጻናት ማቆያ እንዲዘዋወሩ በተፈቀደበት ዕለት ሌፓራን የዝውውር ወረቀቱ ላይ የህጻናቱን ቁጥር ከሦስት ወደ ሁለት ሲቀንስ ተቀርጿል።
የቢቢሲ ዘጋቢዎች ቡድን ሦስቱም ልጆች በቀጥታ ወደ ማቆያ ቤት መወሰዳቸውን አረጋግጧል።
ሌፓራን ግን ወረቀቱን ሲያስተካክል እና ልጁ መውሰድ እንደሚችሉ አሳውቋል።
የኬንያ ፍርድ ቤት ሌፓራን 25 ዓመታት በእስር እንዲቆይ እና 10 ዓመታት በአመክሮ እንዲያሳልፍ ረቡዕ ዕለት ወስኗል።
በሆስፒታሉ ውስጥም ትሠራ የነበረው አዱንዶ ህጻናትን በቸልተኝነት በመያዝ ሦስት ክሶች ጥፋተኛ ብትባልም ከህገ-ወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል ነጻ ተብላለች።
ፍርድ ቤቱ ሌፓራን እና አዱንዶ ከልጆች ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በፍፁም እንዲቆጣጠሩ መፈቀድ እንደሌለበትም አስጠንቅቋል።
በሌፓራ ላይ ጠንካራ ማስረጃ ቢቀርብም ጉዳዩ ከሁለት ዓመት በላይ ተጓቷል።
በኬንያ ካሉት ምርጥ የህግ መከላከያ ጠበቆች አንዱን ማቆም ቢችልም ቢቢሲ በምስጢር የቀረጻው እሱን መሆኑን በኋላ ላይ አምኗል።
በኬንያ ህገወጥ የሕጻናት ዝውውር ስፋት ላይ ጥቂት ኦፊሴላዊ አኃዛዊ መረጃዎች ብቻ አሉ።
የሃገሪቱ የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጥበቃ ሚኒስትር ፍሎረንስ ቦሬ እንዳሉት ከሰኔ 2022 እስከ ግንቦት 2023 ባለው ጊዜ ውስጥ ከ6 ሺህ በላይ ህጻናት ጠፍተዋል።
ቦሬ አክለውም መንግሥት በሚቀጥሉት ስምንት ዓመታት ውስጥ ሁሉንም በግል ይዞታ ስር የሚተዳደሩ አሳዳጊ የሌላቸው ህጻናት መኖሪያዎችን እና የህጻናትን ማቆያዎችን እንደሚዘጋ ተናግረዋል።
እርምጃው ህገወጥ የህፃናትን ዝውውርን ለማስቆም ያለመ ነው።












