መስክ ማንቸስተር ዩናይትድን እገዛለሁ ያልኩት ‘ስቀልድ’ ነው አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለማችን ቁጥር አንድ ባለጸጋ ኤሎን መስክ የማንቸስተር ዩናይትድ እግር ኳስ ክለብን እገዛለሁ ያልኩት ‘ስቀልድ’ ነው አለ።
የቴስላ ኤሌክትሪክ መኪና እና የስፔስ ኤክስ ባለቤት ኤሎን መስክ ቀደም ሲል ዩናይትድን እገዛለሁ ማለቱ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ቢሊየነሩ ብዙ አነጋጋሪ ሃሳቦችን ወደ ሚያካፍለበት ትዊተር በማቅናት “ማንቸስተር ዩናትድን እገዛለሁ” ሲል አጭር መልዕክቱን አስፍሮ ነበር።
መስክ ዩናይትድን እገዛለሁ ማለቱ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች ያስደስተ ጉዳይ ሆኖ ነበር።
ክለባቸው ባለፉት ዓመታት በውጤት ቀውስ ውስጥ የገባባቸው ደጋፊዎች፤ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መስክ ዩናይትድን እንዲረከብ ያላቸውን ፍላጎት ሲገልጹ ነበር።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ይሁን እንጂ መስክ ዩናይትድን እገዛለሁ ካለ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ “የትኛውንም አይነት የስፖርት ቡድን” አልገዛም ካለ በኋላ፤ ማንቸስተርን እገዛለሁ ያልኩት “ስቀልድ ነው” ብሏል።
መስክ ጨምሮ የስፖርት ቡድን ብገዛ ኖሮ “ልጅ ሳለሁ ምርጫዬ የነበረውን” ማንቸስተር ዩናይትድን ነበር የምገዛው ሲል በትዊተር ገጹ ላይ አስተያየቱን አስፍሯል።
አነጋጋሪው ግለሰብ መስክ
መስክ በተለይ በትዊተር ገጹ ላይ የሚሰጣቸው አስተያየት አጋጋሪ ግለሰብ አድርገውታል።
ከወራት በፊት 44 ቢሊዮን ዶላር በመክፈል ትዊተርን ለመግዛት ከግዙፉ የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር መድረክ ቦርድ ጋር ስምምነት ላይ ደርሶ ነበር።
ሆኖም በርካታ የግዢ ስምምነቶች አልተከበሩም በማለት ትዊተርን ለመግዛት ደርሶት የነበረውን ስምምነት መሰረዙን አስታውቋል።
መስክ ከትዊተር ግዢ ራሱን ያገለለው የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያው ትክክለኛ የሆኑ የትዊተር አካውንቶች ምን ያህል እንደሆኑ በቂ መረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ ነው ብሏል።
መስክ ከክሪፕቶከረንሲ ጋርም ስሙ ይያያዛል።
ትልቅ ስም ካላቸው የክሪፕቶከረንሲ ወዳጆች መካከል የቴስላ ኩባንያ ባለቤት ኤሎን መስክ ተጠቃሽ ነው።
ከአንድ ዓመት በፊት በክሪፕቶከረንሲ ላይ ብዙ ኢንቨስት አድርጎ የነበረው የኤሎን መስክ ተቋም ቴስላ፤ ገዝቶት የነበረውን አብዛኛውን ቢትኮይን መልሶ ሽጧል።
የውጤት ቀውስ ውስጥ ያለው ዩናይትድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማንችስተር ዩናይትድ የባለፈው ዓመት የፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዓመት ስድስተኛ ሆነው ማጠናቀቁ ይታወሳል።
ቡድኑ ለዘንድሮው የውድድር ዓመት ኤሪክ ቴን ሃግንን የቡድኑ አሰልጣኝ አድርጎ ቢሾምም በመጀመሪያዎቹ የሊጉ ሁለት ጨዋታዎች አሳፋሪ የተባሉ ሽንፈቶችን ተከናንበዋል።
በቀጣይ ሳምንት ደግሞ ዩናይትዶች ጠንካራውን ሊቨርፑል በሜዳቸው ያስተናግዳሉ።
መስክ ዩናይትድን እገዛለሁ ያለው የቡድኑ ውጤት ማሽቆልቆልን ተከትሎ የክለቡ ባለቤት የሆኑት የግሌዘር ቤተሰቦች ቡድኑን ለሌላ ገዢ አሳልፈው እንዲሰጡ የሚጠይቁ ድምጾች በተበራከቱበት ወቅት ነበር።
የዘንድሮው ውድድር ዓመት ሲጀመርም ተቃውሞው ቀጥሏል።
ክለቡ በመጀመሪያ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ውጤት ማጣቱን ተከትሎ በሚቀጥለው ሰኞ ከሊቨርፑል ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ከፍተኛ ተቃውሞ ባለቤቶቹ ላይ ለመሰንዘር ደጋፊዎች እየመከሩ ነው።
ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ባለመግባት ቁጣቸውን ለማሳየት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።












