አውስትራሊያዊው ገበሬ ሊበላው የነበረን አዞ በጥርሱ ነክሶ ነፍሱን አተረፈ

በአውስትራሊያ አዞዎች በሕግ ጥበቃ ይደረግላቸዋል

የፎቶው ባለመብት, PA MEDIA

የምስሉ መግለጫ, በአውስትራሊያ አዞዎች በሕግ ጥበቃ ይደረግላቸዋል

አንድ የአውስትራሊያ ገበሬ ሊበላው የነበረን አዞ በደመ ነፍስ ዞሮ በመንከስ ነፍሱን አተረፈ።

ከብት በማደለብ የሚተዳደረው ይህ ገበሬ ስሙ ኮሊን ዴቬ ይባላል።

በአዞ ከመበላት የተረፈው በደመ ነፍስ በወሰደው ቅጽበታዊ እርምጃ መሆኑን ተናግሯል።

ግለሰቡ ጥቃት የደረሰበት ከሦስት ሜትር በላይ በሚረዝም ግዙፍ አዞ ነው።

ከጥቃቱ በኋላ ለአንድ ወር ሆስፒታል ቆይቶ አሁን በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛል።

ከአዞ ጋር የተናነቀው ኮሊን ለኤቢሲ ቴሌዚዥን ጣቢያ እንደተናገረው አዞውን በንክሻ ያቆሰለው የአዞው የዐይኑ ቆብ ላይ ነው።

“ይህን ያደረኩት በሕይወት ለመኖር ትንቅንቅ ላይ ስለነበርኩ ብቻ ነው” ብሏል።

ነገሩ የተከሰተው ከወር በፊት ሲሆን ኮሊን በሐይቅ ዳርቻ በኩል ሲያልፍ ወደ ሐይቁ ዳርቻ እየወጣ በነበረ ውሃ ውስጥ ዓሣ ሲዋኝ የተመለከተ ይመስለዋል።

ኮሊን በዚያ ያልፍ ከነበረው ፊኒስ ወንዝ በኩል አጥር ለማጠር በተነሳበት ጊዜ ነበረ።

ከሐይቁ ዳርቻ እንደቆመ ባልጠበቀው ፍጥነት ግዙፉ አዞ የኮሊንን ቀኝ እግሩን ጎትቶ ወደ ውሃው ይከተዋል።

ኮሊን በዚህን ጊዜ የሞት ሽረት ትግል ይጀምራል። መጀመሪያ የአዞውን ጎን ደጋግሞ በግራ እግሩ እንደነረተው ተናግሯል።

ከዚያ ግን አዞው እያየለ ሲመጣ ገበሬው ኮሊን የሞት ሞቱን የአዞውን የዐይን ቆብ በጥርሱ ቦጭቆታል።

“እርምጃ ለመውሰድ ምቹ ሁኔታ ላይ አልነበርኩም፤ ዝም ብዬ በደመ ነፍስ ስነክሰው ነው የዐይን ቆቡን ያገኘሁት፤ እንጂ አስቤው አይደለም። ቆቡ ወፍራም ነው፤ ልክ ቆዳ የመንከስ ያህል ነው። ደጋግሜ በጥርሴ ስቦጭቀው ለቀቀኝ” ብሏል።

አዞው ገበሬውን ኮሊንን ከለቀቀው በኋላም ቢሆን ለጥቂት ሜትሮች ያህል በድጋሚ ተከትሎት የነበረ ቢሆንም ኮሊን እግሩን እየጎተተ ማምለጥ ችሏል።

ከዚያ በኋላ መኪናውን ወዳቆመበት ቦታ በመሄድ እየደማ የነበረውን ቀኝ እግሩን በፎጣ እና በገመድ ጠፍንጎ በማሰር ሆስፒታል ለመድረስ ችሏል።

“አዞው ሌላ ቦታ ቦጭቆኝ ቢሆን ኖሮ አልቆልኝ ነበር” ይላል ገበሬው ኮሊን።

በአውስትራሊያ አብዛኛው አካባቢ አዞዎች ለምርምር፣ ለቱሪዝም እንዲሁም ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ስለሚታመን በሕግ ጥበቃ ይደረግላቸዋል።

ከዚህ ቀደም ለመጨረሻ ጊዜ አዞ በሰው ላይ ከባድ ጥቃት ያደረሰው ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ በኩዊንስላንድ ግዛት ውስጥ ነበረ።