ዩክሬን ኤፍ-16 የተባሉትን ተዋጊ ጄቶች በድጋፍ እንዳገኘች ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ ተናገሩ

ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ

የፎቶው ባለመብት, Ukrainian presidency

ዩክሬን የመጀመሪያዎቹን አሜሪካ ሰራሽ ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶች መቀበሏን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ተናገሩ።

አድራሻው ካልታወቀ አየር ማረፊያ መግለጫ የሰጡት ፕሬዝደንቱ በሁለት ተዋጊ ጄቶች ታጅበው “ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶች ዩክሬን ገብተዋል። ተሳክቶልናል” ብለዋል።

አንድ ሰሞን ድጋፍ ለማቅረብ ዳተኛ ሆነዋል ያሏቸውን ምዕራባዊያን ወዳጆቻቸውን ያመሰገኑት ዜሌንስኪ ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያሻቸው አሳውቀዋል።

በሶቪዬት ዘመን ጄቶች ይጠቀም የነበረው የዩክሬን ጦር አዳዲስና ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች ማግኘቱ እጅጉን ይጠቅመዋል ተብሎ ይገመታል።

በሚቀጥሉት ወራት ሌሎች ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶች ወደ ዩክሬን እንደሚገቡ የሚጠበቅ ቢሆንም ዩክሬን እኒህን ጄቶች የሚያበሩ በቂ የሰለጠኑ አብራሪዎች እንደሌሏት ዜሌንስኪ አልካዱም።

ለጊዜው ምን ያክል ተዋጊ ጄቶች ወደ ዩክሬን እንደመጡ ያልገለጡት ፕሬዝደንቱ ድጋፉን ያደረገችው ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድስ ወይስ ዩናይትድ ስቴትስ የሚለውንም መናገር አልሻቱም። ነገር ግን በምስጋናቸውን የአሜሪካን ስም በተለይ ነጥለው ሲያወድሱ ነበር።

ባለፈው ዓመት ነሐሤ የዩኤስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን፤ ፈቃደኛ የሆኑ የአውሮፓ አጋር ሀገራገት ተዋጊ ጄት መላክ ይችላሉ ማለታቸውን ተከትሎ የኔቶ አባል ሀገራት 65 ኤፍ-16 ጄቶችን ለመላክ ቃል ገብተው ነበር።

ኤፍ-16 የተባለው ተዋጊ ጄቶች የተፈበረከው በአውሮፓውያኑ 1978 ሲሆን በርካታ ምዕራባዊያን ሀገራት ይህን ጄት ከአገልግሎት አስወጥተው የ2015 ስሪት በሆነው የአሜሪካው ኤፍ-35 ሊተኩት አስበዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዩናይትድ ኪንግደም ምንም ዓይነት ኤፍ-16 ጄቶች ባይኖሯትም ስቶርም ሻዶው የተባሉ ለዚህ ተዋጊ ጄቶ የሚሆኑ ሚሳዔሎችን ለዩክሬን እያቀረበች ነው።

አሁን ዩክሬን ያገኘቻቸው ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶች ከተወሰኑ የምዕራባዊያን ሚሳዔሎች “ሲስተሞች” ጋር መሥራት የሚችሉ ናቸው። ከእነዚህ መካከል ፓትሪዮት እና ናስማስ የተባሉት ከምድር የሚወነጨፉ የሚሳዔል ሲስተሞች በዩክሬን ጥቅም ላይ ይውላሉ።

ሮኬቶች፣ ቦምብ እና ሚሳዔል መሸከም የሚችሉት ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶች በፅንሰ-ሐሳብ ደረጃ ለዩክሬን የተሻለ ጥንካሬ የሚሰጧት ሲሆኑ በሩሲያ የተያዙ ግዛቶች እና ሩሲያ ውስጥ ጭምር ጥቃት ለማድረስ የሚያስችሉ ናቸው።

እኒህ ጄቶች የሩሲያው ‘ግላይድ ቦምብ’ የተሰኘውን መሣሪያ ለመመከትም ይጠቅማሉ ተብሎ ይጠበቃል። የሩሲያው ‘ግላይድ ቦምብ’ ክንፎች ያሉት እና በአቅጣጫ የሚመራ፤ ዒላማውን ጠብቆ የሚመታ ቦምብ ነው። አሜሪካ ጄዳም የተሰኘ ከዚህ ቦምብ ጋር ተመሳሳይነት ያለው የጦር መሣሪያ አላት።

ባለፈው መጋቢት ብቻ 3 ሺህ ቦምቦች የተወረወሩ ሲሆን አብዛኛዎቹ ቦምቦች ሱ-34 ከተባለው ተዋጊ ጄት የተጣሉ ናቸው።

ዩክሬን መሬት ላይ ያሏትን ኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶች መጠበቅ ከቻለች ወደፊት ጥቃትን ከመከላከል አልፋ የሩሲያ ወታደሮች ወደኋላ አፈግፍገው እንዲመለሱ ልታስገድድ ትችላለች ተብሎ ተገምቷል።

ተንታኞች እንደሚሉት የኤፍ-16 ተዋጊ ጄት አብራሪዎች በምድር የሚካሄደውን ጦርነት የሚያግዙ ይሆናሉ። በቅርብ ወራት በተለይ በምስራቃዊው ዶንባስ ግዛት የዩክሬን እግረኛ ጦር ከፍተኛ ጉዳት አስተናግዷል።

ኪዬቭ እኒህን ተዋጊ ጄቶች ከዩክሬን ውጭ ባሉ የጦር አየር ማረፊያዎች ልታቆም እንደምትችል የጠቆመች ቢሆንም የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የትኛውም የዩክሬንን ተዋጊ ጄቶች የሚያቆም የምዕራባዊያን አየር ማረፊያ ዒላማ ይሆናል ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ከዚህ ቀደም ሲናገሩ ለዩክሬን የሚያገለግሉ የትኛውም ኤፍ-16 ጄቶች ተመትተው ይጣላሉ ብለው ነበር።