ዋይት ሐውስ ትራምፕ ከሩሲያው እና ከዩክሬኑ መሪ ጋር ለመነጋገር "ዝግጁ" ናቸው አለ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ዶናልድ ትራምፕ መልዕክተኛቸው ከፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር "በጣም መልካም የሆነ ውይይት" ሲሉ የገለፁትን ውይይት ካደረጉ በኋላ ከሩሲያ እና ከዩክሬን መሪዎች ጋር ለመገናኘት "መልካም ዕድል" እንዳለ ተናገሩ።

በዋይት ሐውስ ሁለቱ መሪዎች ለእንዲህ ዓይነቱ የመሪዎች ጉባዔ ተስማምተው እንደሆን የተጠየቁት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት "በጣም ጥሩ ተስፋ አለ" ሲሉ ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ክሬምሊን ቀደም ሲል በፑቲን እና በስቲቭ ዊትኮፍ መካከል ስለተካሄደው ውይይት ግልጽ ያልሆነ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ረዳት ኃላፊው ሁለቱ ወገኖች በሞስኮ "ገንቢ" የሆነው ውይይት ማካሄዳቸውን እና "መልዕክቶችን" መለዋወጣቸውን ተናግረዋል።

የትራምፕ መልዕክተኛ ፕሬዚዳንት ፑቲንን አግኝተው ያናገሩት፣ ሩሲያ በዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ የተቀመጠላት ቀነ ገደብ ከማለቁ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ሲሆን ካልሆነ አዲስ ማዕቀብ ይጠብቃታል።

ትራምፕ ረቡዕ ዕለት በኦቫል ኦፊስ አስተያየት የሰጡት በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው ላይ ለአንዳንድ የአውሮፓ አጋሮቻቸው ውይይቱን በሚመለከት ማብራሪያ መስጠታቸውን የሚገልጽ ጽሑፍ ከለጠፉ በኋላ ነው።

ትራምፕ "ይህ ጦርነት ማብቃት እንዳለበት ሁሉም ይስማማሉ። እናም ለዚያ በሚቀጥሉት ቀናት እና ሳምንታት ውስጥ እንሰራለን" ብለዋል።

ዋይት ሐውስ ለቢቢሲ እንደገለፀው ሩሲያ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጋር የመገናኘት ፍላጎት እንዳላት እና "ከፕሬዚዳንት ፑቲን እና ከፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ጋር ለመገናኘት ዝግጁ ናቸው" ብሏል።

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በበኩላቸው ስለ ዊትኮፍ ጉብኝት ከትራምፕ ጋር መነጋገራቸውንና የአውሮፓ መሪዎችም በስልክ ውይይቱ ላይ እንደነበሩ ተናግረዋል።

ዜሌንስኪ ሩሲያ ገንዘብ ማጣት ከጀመረች ብቻ ወደ ሰላም እንደምትመጣ በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቁ ነበር።

ትራምፕ ሩሲያ ጦርነቱን ለማቆም እርምጃ ካልወሰደች ከባድ ማዕቀብ ሊጣልባት ወይም ከእርሷ ጋር የሚገበያዩ ላይ ሁሉ ሁለተኛ ደረጃ ማዕቀብ ሊጣልባቸው ይችላል ሲሉ አስፈራርተዋል።

ረቡዕ ዕለት በፑቲን እና በዊትኮፍ መካከል የተደረገው ውይይት፣ ምንም እንኳን ትራምፕ በሞስኮ እና በኪየቭ መካከል በተደረጉት ድርድሮች መሻሻል ባለማግኘቱ ብስጭታቸው እየጨመረ ቢመጣም ወዳጅነት የተሞላው ነበር ።

ቭላድሚር ፑቲን እና የአሜሪካ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ በክሬምሊን ተገናኝተው ሲጨባበጡ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካው መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ጋር በተደጋጋሚ ተገናኝተው ተወያይተዋል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዊትኮፍ ሞስኮን ለቅቀው ከወጡ በኋላ፣ ዋይት ሐውስ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሕንድ ከሩሲያ የነዳጅ ዘይት በመግዛቷ ተጨማሪ 25 በመቶ ታሪፍ እንዲጣልባት ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ መፈረማቸውን አስታውቋል።

ይህ ታሪፍ ከነሐሴ 27 ጀምሮ ተግባራዊ መሆን ይጀምራል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሕንድን "በሩሲያ የጦር መሳሪያ በዩክሬን ምን ያህል ሰዎች እየተገደሉ ስለመሆኑ" ደንታ የላትም ሲሉ ወቅሰዋል።

ምንም እንኳ አሜሪካ ማዕቀብ ለመጣል ደጋግማ ብትዝትም እንዲሁም ትራምፕ ያስቀመጡት ቀነ ገደብ አርብ ዕለት የሚያበቃ ቢሆንም፣ሩሲያ ግን በዩክሬን ከተሞች ላይ የምታካሄደውን መጠነ ሰፊ የአየር ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።

ትራምፕ በጥር ወር ሥልጣናቸውን በይፋ ከመረከባቸው በፊት በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለውን ጦርነት በአንድ ቀን ማቆም እንደሚችሉ ተናግረው ነበር።

ፕሬዝዳንቱ አሳካዋለሁ ያሉትን ከግብ ሳያደርሱ መቅረታቸውን ተከትሎ ትዕግስት እያጡ በመምጣታቸው ስለ ሩሲያ መረር እና ከረር ያሉ ንግግሮችን ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ባለፈው ወር "[ጦርነቱ] ብዙ ጊዜ የተፈታ መስሎን ነበር፤ ከዚያ በኋላ ግን ፕሬዝዳንት ፑቲን ወጥተው እንደ ኪየቭ ባሉ አንዳንድ ከተማዎች ሮኬቶችን ማስወንጨፍ ይጀምራሉ። በዚህም የተነሳ ብዙ ሰዎችን በአረጋውያን መንከባከቢያ ውስጥ የሚኖሩ ጭምር ተገድለዋል" ብለዋል።

ሞስኮ ዩክሬንን ከወረረች ሦስት ዓመት ተኩል የሆናት ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ በቱርክ ኢስታንቡል ሦስት ዙር የሰላም ድርድር ቢካሄድም ጦርነቱን ማስቆም አልተቻለም።

ሞስኮ የምታስቀምጣቸው ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ቅድመ ሁኔታዎች በኪየቭ እና በምዕራባውያን አጋሮቻቸው ዘንድ ተቀባይነት አላገኙም።

ዜሌንስኪ ከፑቲን ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ለመወያየት ያቀረቡትንም ጥያቄ ክሬምሊን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጓል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የትራምፕ አስተዳደር ማክሰኞ ዕለት ዜሌንስኪ እና ትራምፕ በስልክ ከተወያዩ በኋላ ለዩክሬን የ200 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የወታደራዊ መሳሪያዎች ሽያጭ አጽድቋል።

ሁለቱ መሪዎች በተጨማሪ በመከላከያ ትብብር እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ላይ መምከራቸው ተሰምቷል።

ዩክሬን የሩሲያ የነዳጅ ማምረቻዎችን እና የኃይል ማመንጫዎችን ለመምታት ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ስትጠቀም ሞስኮ ደግሞ የአየር ጥቃትዋን በዩክሬን ከተሞች ላይ አድርጋለች።

የኪየቭ ከተማ ወታደራዊ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት በከተማዋ ላይ በደረሰው ጥቃት አንድ ሰው ከተገደለ በኋላ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 32 መድረሱን ተናግሯል።

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ጀምሮ በኪየቭ ላይ ከፍተኛው ጉዳት ያደረሰ የአየር ድብደባ ነበር ተብሏል።

የዩክሬን ባለሥልጣናት ረቡዕ ዕለት እንደተናገሩት ሩሲያ በማዕከላዊ ዛፖሪዝሂያ በሚገኝ የመዝናኛ ካምፕ ላይ በፈፀመችው ጥቃት ሁለት ሰዎች ሲሞቱ 12 ቆስለዋል።

ዜሌንስኪ የአየር ድብደባውን ተከትሎ "በዚህ ጥቃት ውስጥ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ምክንያት የለም። ሰዎችን ማስፈራራት እና ጭካኔ ብቻ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።