በሴራሊዮን ኤምባሲ ተሽከርካሪ ውስጥ 'ኮኬይን' የያዙ ሰባት ሻንጣዎች ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኤምባሲዋ ተሽከርካሪ ውስጥ ኮኬይን እንደሆነ የተጠረጠረ አደንዛዥ ዕጽ በሰባት ሻንጣዎች ውስጥ ከተገኘ በኋላ ሴራሊዮን አምባሳደሯን ከጎረቤት አገር ጊኒ ጠራች።
ሰኞ ዕለት የጊኒ ባለሥልጣናት ንብረትነቱ የሴራሊዮን ኤምባሲ የሆነ ተሽከርካሪን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውንና ኮኬይን ተብለው የተጠረጠሩ ንጥረ ነገሮችን ማግኘታቸው ተገልጿል።
የሴራሊዮን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልሀጂ ሙሳ ቲሞቲ ካባ እንዳሉት በተሽከርካሪው ውስጥ የነበሩ ግለሰቦችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
ይህንን ተከትሎም የአገሪቷ መንግሥት በጊኒ የሴራሊዮን አምባሳደር የሆኑትን አምባሳደር አሊማሚይ ባንጉራ ስለ ክስተቱ እንዲያስረዱ ወደ ፍሪታውን ከተማ እንዲመጡ በአስቸኳይ ጠርቷል።
አምባሳደሩ በተሽከርካሪው ውስጥ ያልነበሩ ሲሆን በቁጥጥር ሥርም አለማዋላቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
" አምባሳደሩ በዚህ ድርጊት መሳተፋቸው አልተረጋጋጠም " ብለዋል ሚኒስትር ካባ።
ሚኒስትሩ ጨምረው እንደገለጹት የኮኬይን አደንዛዥ ዕፅ እንደያዙ ከተጠረጠሩ ሻንጣዎች አጠገብም 2 ሺህ ዶላር የሚሆን ጥሬ ገንዘብ ተገኝቷል።
ሚኒስትሩ የተጠረጠረው አደንዛዥ ዕጽ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ግን አልጠቀሱም።
ሁለቱ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ክስተቱን ለመመርመር በትብብር እየሰሩ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ ድርጊቱን የፈፀሙ ሰዎች ተጠያቂ ይደረጋሉ ብለዋል።
" የሴራ ሊዮንን እና ዓለም አቀፍ የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ሕጎችን የጣሰ ማንኛውም አካል ሙሉ በሙሉ በሕግ ተጠያቂ ይሆናል" ሲሉም አክለዋል።
ኮኬይን ከሚመረትባት ላቲን አሜሪካ ከፍተኛ የኮኬይን ገበያ ወዳለው አውሮፓ ለማስገባት ምዕራብ አፍሪካ ዋነኛ የማሻገሪያ መንገድ ነው። ሆኖም የተወሰኑ አደንዛዥ እፆችም እዚያው ጥቅም ላይ ይውላሉ።
ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር የሴራሊዮን ፕሬዚደንት ጁሊየስ ማዳ በአገሪቷ ያለው የአደንዛዥ ዕጽ አጠቃቀም ብሔራዊ አደጋ መሆኑን ማወጃቸው ይታወሳል።
ኩሽ የተባለውና ሱስ አስያዥ የንጥረ ነገሮች ድብልቅ በአገሪቱ ውስጥ ለዓመታት ተንሰራፍቶ ይገኛል። በዚህ አደንዛዥ እፅ ውስጥ ከሚጨመሩ ግብዓቶች መካከል አንዱ የተፈጨ የሰው አጥንት ነው።
የአገሬው ሰውም መንግሥት ይህንን እፅ እንዲከላከል እና የአደንዛዥ ዕፁ ተጠቂዎች እንዲረዳ ጠይቀዋል።












